Sunday, October 27, 2013

በደቡብ ክልል የመምህራን ተቃውሞ እየተስፋፋ ነው

መምህራን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በሚል  የመስከረም ወር ደሞዛቸው ያለፈቃዳቸው ተቀንሶ ከተሰጣቸው በሁዋላ የጀመሩት ተቃውሞ እየተስፋፋ መሆኑን ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የጨንጫ ወረዳ 7 ትምህርት ቤቶች መምህራን የተቆረጠው ደሞዛችን ካልተመለሰ ስራ አንሰራም በሚል አድማ ከመቱ በሁዋላ፣ በዛሬው እለት ደግሞ በጋሞጎፋ ዞን በምእራብ አባያ ወረዳ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ” የተቆረጠብን ደመወዝ የማይመለስ ከሆነ ስራ አንሰራም በሚል ” በስፍራው ለተገኙት ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ፣ የወረዳው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የወረዳው የመምህራን ማህበር ተወካይ በስፍራው ተገኝተው መምህሩን ለማወያየት የሞከሩ ሲሆን፣ መምህራኑ ግን ደሞዛችን ተመልሶ እስካልተሰጠን ድረስ ከእናንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ አይደለንም የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ባለስልጣናትም መምህራኑ ” አመጹን እንዲያቆሙ፣ የተቆረጠባቸው የመስከረም ወር ደሞዝ እንደሚመለስና በጥቅምት ወርም ያለ ፈቃዳችሁ እንደማይቆረጥባቸው”  ቃል ገብተው ለማረጋጋት ሞክረዋል።
ባለስልጣናቱ መምህራኑን ይቅርታ በመጠየቅ ለማረጋጋት ቢሞክሩም፣ መምህራኑ ይቅርታውንም ለመቀበል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል ። ስለአባይ ግድብ ከእናንተ የተሻለ  በቂ መረጃ አለን በማለትም መምህራኑ በባለስልጣናቱ የቀረበውን ልመና ውድቅ አድርገዋል።
በዚሁ ወረዳ የአይዶ አንደኛ ደረጃ፣ ወሌ አንደኛ ደረጃ፣ ምእራብ አንደኛ ደረጃ፣ ገልዶ አንደኛ ደረጃ እና የሌሎችም ትምህርት ቤቶች መምህራን የተቃውሞ ፊርማ አሰባስበው ለወረዳው ትምህርት ቤት ጽህፈት ቤት አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከምእራብ አባያ መሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 15 የኢህአዴግ አባላት የሆኑ መምህራን ከድርጅት አባልነት ለመሰናበት የመልቀቂያ  ደብዳቤ አስገብተዋል። መምህራኑ ድርጅቱን ለመልቀቅ  ካቀረቡዋቸው መክንያቶች መካከል፣ “የኢኮኖሚ ችግር፣ የድርጅቱ ኢ- ዲሞክራሲያዊ ባህሪና በየጊዜው የሚፈጠርውን ጫና  ለመቋቋም አለመቻል” የሚሉ ይገኙበታል።
ቀድም ብሎ በመሰናዶ ትምህርት ቤቱ ውስጥ 75 የኢህአዴግ አባላት መምህራን የነበሩ ሲሆን፣ 47 መምህራን ድርጅቱን በመልቀቃቸው 28 አባላት ብቻ ቀርተው ነበር። ከ28ቱ መምህራን መካከል ደግሞ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ 15ቱ መምህራን የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል።

No comments:

Post a Comment