Wednesday, October 23, 2013

የገቢዎችና ጉምሩክ ተከሳሾች ክስ መሰማት ጀመረ



የገቢዎችና ጉምሩክ ተከሳሾች ክስ መሰማት ጀመረ
  • የቀድሞ ኤርፖርት ጉምሩክ ሃላፊ በዋስ ተለቀዋል 
  • በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ላይ የቀረበው ክስ ሠኞ እና ማክሰኞ ይሰማል
          በከባድ የሙስና ወንጀል በተከሰሱት የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት የተለያዩ ሃላፊዎች እና ሠራተኞች እንዲሁም ታዋቂ ባለሃብቶች ላይ በፌደራል የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ የቀረበው ክስ፣ ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት መሠማት የጀመረ ሲሆን በባለሀብቱ አቶ ማሞ ኪሮስ እና በገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን የቦሌ አየር ማረፊያ ጉምሩክ የፍተሻ የስራ ሂደት መሪ በነበሩት በአቶ ዮሴፍ አዳዩ ላይ የቀረበው ክስ ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡
ተከሳሾችም በክሱ ላይ ያላቸውን የመቃወሚያ ነጥብ ያስመዘገቡ ሲሆን አቶ ዮሴፍ አዳዩ የተከሰሱበት የወንጀል አንቀጽ ከ10 አመት በታች የሚያስቀጣ በመሆኑ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸዋል፡፡
አቃቤ ህግ በአቶ ማሞ ኪሮስ ላይ ያቀረበው ክስ ተከሳሹ በ1998 ዓ.ም “ከተማ ኮንስትራክሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ”ን በስራ አስኪያጅነት ሲመሩ ከህግ አግባብ ውጪ እቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ አድርገዋል ይላል፡፡ ተከሳሹ “የኮንክሪት ሚክሰር” እና “ቫይብሬተር” ከውጭ ከቀረጥ ነፃ ካስገቡ በኋላ፣ ከእሸቱ ኤልያስ ወልደማርያም አስመጪና ላኪ የገዙ ለማስመሰል ሃሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተዋል የሚል የወንጀል ክስም ቀርቦባቸዋል፡፡ አቃቤ ህግ በክስ መዘርዝሩ ላይ ስለወንጀሉ አፈፃፀም ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ማቅረቡንም ፍ/ቤቱ የክሱን ጭብጥ በንባብ ባሰማበት ወቅት አመልክቷል፡፡ ክሱ በችሎቱ ከተነበበ በኋላም የቀረበው ክስ የውስብስብነት ባህሪ ስለሌለው በመደበኛ ክርክር ሂደት እንዲቀጥል ብይን ተሰጥቷል፡፡
የተከሳሽ ጠበቃ የመቃወሚያ ሃሳባቸውን ተጠይቀው ሲያቀርቡም፤ የአቃቤ ህግ ክስ፣ ተከሳሽ ራሱን መከላከል በሚያስችለው ደረጃ ተዘርዝሮ በሚገባ የቀረበ አይደለም፣ የተጠቀሰው የወንጀል አንቀጽ (379) በባህሪው የሙስና ወንጀልን አያመለክትም፤ ክሱ የቀረበበት አንቀጽ ተገቢ አይደለም” ብለዋል፡፡ ከእሸቱ ኤልያስ ድርጅት ተጭበረበረ የተባለው ሰነድ የመንግስት ሰነድ አይደለም ያሉት የተከሳሽ ጠበቃ፤ ክሱ በዚህ መልኩ መቅረቡ የተከሳሹን የመከላከል እድል የሚያጠብ ስለሆነ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ይደረግልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ለመቃወሚያው በሰጠው ምላሽ ክሱ ተከሳሹ በሚረዳው መልኩ በዝርዝር የቀረበ ነው፣ የተጠቀሰው አንቀጽ የሙስና ወንጀልን የሚጠቅስ ነው፣ የተጭበረበረው ሰነድ በእርግጥም ከግል ድርጅት የወጣ ነው፤ ነገር ግን የጉምሩክ መስሪያ ቤትን በዚያ ሰነድ አሳስተዋል፤ ስለዚህ ፍ/ቤቱ መቃወሚያውን ውድቅ ያድርግልን ሲል ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ ፍ/ቤቱ በአቶ ዮሴፍ አዳዩ ላይ የቀረቡትን ሁለት ክሶች በንባብ ያሰማ ሲሆን አንደኛው ክስ፣ ተከሳሽ በገቢዎችና ጉምሩክ የአዲስ አበባ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ የፍተሻ ክፍል ሃላፊ ሆኖ በሰራባቸው ከ2002 -2003 ባሉ አመታት ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ ግለሰቦች ለያዙት እቃ ቀረጥ ሳይከፍሉ እንዲገቡ በማሰብ፣ ሳይፈተሹ እንዲያልፉ አድርጓል የሚል ነው፡፡ ከዚሁ ክስ ጋር ተያይዞም ንብረትነታቸው የገቢዎችና ጉምሩክ የሆኑ ኦርጅናል የስራ ሰነዶችን መኖሪያ ቤቱ አስቀምጦ ተገኝቷል የሚል የወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡ በተከሳሹ ላይ የቀረበው ሁለተኛ ክስ ደግሞ ህጋዊ ፍቃድ የሌለው ማካሮቭ ሽጉጥ ይዞ ተገኝቷል የሚል ነው፡፡ ለክሶቹ የሰነድና የሰው ማስረጃ እንዲሁም በኤግዚቢት የተያዙ ንብረቶች መቅረባቸውን በክሱ ማመልከቻ ተጠቅሷል፡፡
የተከሳሽ ጠበቃ የመቃወሚያ ሃሳባቸውን ያቀረቡ ሲሆን ወንጀሉ ተፈፀመ የተባለበት ትክክለኛ ቀን በዝርዝር አልተገለፀም፣ የግለሰቦቹ ማንነትና ብዛት በግልጽ መታወቅ ነበረበት፣ የጉምሩክ ሰነዶች በቤቱ ተገኝተዋል የተባለው በየትኛው የወንጀል አንቀጽ እንደሚያስጠይቅ አልተጠቆመም ብለዋል፡፡ ፍቃድ የሌለው መሣሪያ ይዞ መገኘት የሚለውን በተመለከተም ኮሚሽኑ እንዲህ አይነት ክስ ማቅረብ አይችልም፤ ጉዳዩ ከሙስና ጋር የሚገናኝ ስላልሆነ በሌላ አካል ነው መታየት ያለበት ስለዚህ ክሱን ይሰርዝ ሲሉ ጠበቃው መቃወሚያቸውን አቅርበዋል፡፡
አቃቤ ህግ ለመቃወሚያው በሰጠው ምላሽ፤ ድርጊቱ የተፈፀመው በተለያየ ጊዜ ነው፣ ሳይፈተሹ እንዲያልፉ የተደረጉት ግለሰቦች ብዛት እና ማንነት ምስክሮች ሲቀርቡና ማስረጃ በዝርዝር ሲቀርብ በሂደት የሚታይ ይሆናል፣ ሰነዶችን በተመለከተም ኦርጅናል የመስሪያቤቱን ሰነዶች ማስቀመጥ የነበረበት መኖሪያ ቤቱ ሳይሆን መስሪያ ቤት ነው ብሏል፡፡ ህገ ወጥ መሣሪያ ይዞ መገኘት በእርግጥ የሙስና ወንጀል አይደለም፤ ነገር ግን ክሱን አብሮ ለማቅረብ የስነ ስርአት ህጉ እንደሚፈቅድ በሰበር ሰሚ ችሎት ተወስኗል የሚል ምላሽ ሰጥቷል - አቃቤ ህግ፡፡
የተከሳሹ አቶ ዮሴፍ አዳዩ ጠበቃም የተጠቀሰው አንቀጽ ከ10 አመት በታች የሚያስቀጣ ስለሆነ የዋስ መብትን የሚያስከለክል አይደለም፤ የዋስትና መብቱ ይከበር ሲሉ ፍ/ቤቱን የጠየቁ ሲሆን አቃቤ ህግም በዋስ ቢለቀቁ ተቃውሞ እንደሌለው፣ ነገር ግን ከሃገር እንዳይወጡ ለኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ትዕዛዝ ይፃፍልን ሲል አመልክቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ የቆየው ፍ/ቤቱ፤ በአቶ ዮሴፍ አዳዩ ላይ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ተከሳሹ የ5ሺህ ብር ዋስ አቅርበው እንዲለቀቁ እንዲሁም ከሀገር እንዳይወጡ ለኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ደብዳቤ እንዲፃፍ ብሏል፡፡ መዝገቡንም ለጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ በአቶ ማሞ ኪሮስ ላይ ፍ/ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ፣ መቃወሚያውን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 14 ቀን 2006 ቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ክስ ሳይመሰረትባቸው ጉዳያቸው ወደ ምርመራ መዝገብ የተመለሠው አቶ ፍፁም ገ/መድህን፣ በእግዚአብሔር አለበልና ምህረተአብ አብርሃ ጥቅምት 6 ቀን 2006 ፍ/ቤት ቀርበው ዳኞች ተሟልተው ባለመቅረባቸው ለጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
አቶ መላኩ ፋንታ እና አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ ክስ ቀርቦባቸው ማረሚያ ቤት የሚገኙ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች ጥቅምት 11 እና 12 ቀን 2006 ዓ.ም ክሣቸውን ለማንበብ ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
Written by  አለማየሁ አንበሴ
http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment