Monday, February 3, 2014

የ2014 የዓለም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ

ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

coup map

በያዝነው የአውሮጳውያን ዓመት ሊከሰቱ የሚችሉ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋዎች ይፋ ሆኑ፡፡ በርካታዎቹ በአፍሪካ አገራት ሲሆኑ አደጋው ካንዣበበባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በአሜሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ጄይ ዑልፌልደር የተለያዩ የሒሳብ ስሌቶችን በመጠቀም የ2014ዓም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ትንበያ ከሆነ 40 አገራት ቀይ የአደጋ ምልክት በርቶባቸዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ መፈንቅለ መንግሥት እንዲሆን የሚመኙት ነገር ባይሆንም የመከሰቱ ጉዳይ ግን መነገር ያለበት ነው ይላሉ ምሁሩ፡፡
በተለያዩ የአሜሪካ አንጋፋ ጋዜጦች ላይ የተዘገበው ይኸው ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለማችን ላይ 40 አገራት ከፍተኛ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋ ያነጣጠረባቸው መሆናቸውን በጥናቱ ተገልጾዋል፡፡ አብዛኛዎቹም ከአፍሪካ መሆናቸው አሁንም አህጉሪቱ ለበለጠ ቀውስ የተጋለጠች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
forecast-dot-2014በቀዳሚነት የመፈንቅለ መንግሥት የሚያሰጋቸው አገራት ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኒጀር፣ ጊኒ ቢሳው እና ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክና ደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡ ከአውሮጳ ምንም አገር በዝርዝሩ ውስጥ ያልገባ ሲሆን ዩክሬይን አደጋው ጥላ ካጠላባቸው በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ ከወደ አሜሪካ ዩኳዶርና ሃይቲ ቀዩ የአደጋ ምልክት የታየባቸው ሲሆን ከእስያ ታላንድ፣ አፍጋኒስታን እና ፓኪስታንን ጨምሮ ስድስት አገራት የመፈንቅለ መንግሥት የቀይ ምልክት አደጋ ካለባቸው 40 አገራት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከ40ዎቹ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 25ኛ ላይ ትገኛለች፡፡ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ህወሃት/ኢህአዴግ ሥልጣኑን ለራሱ ታማኞች ብቻ በመከፋፈል እንዲያም ሲል በቤተሰብ ደረጃ በማውረድ እየሸነሸነው በመሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሰሞኑን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አዲስ አድማስ ሲዘግብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን እና የነጻው ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ገልጾ ነበር፡፡
አፋኝ ሕጎችን በማውጣትና ማንኛውንም ዓይነት የግለሰብ መብት በመንፈግ በአንጻሩ ሊኖር የማይችል የቡድን መብት አስከብራለሁ የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ በተመሳሳይ የሚወጡ መረጃዎችን በማጣጣል ዋጋ ቢስ ሲያደርግ መቆየቱን የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡ በተቀረው ደግሞ “ልማት፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣ … ” በማለት የለውጥ ሃሳብ ከመጣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይስተጓጎላሉ በሚል በሕዝቡ ዘንድ ማደናገሪያ በመፍጠር በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች “ጸረ ልማት” በማለት እንደሚወነጅላቸው ያማርራሉ፡፡ በምርጫ ማጭበርበርና ማንኛውንም ፖለቲካዊ ሆነ ማኅበራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በሙሉ ቁጥጥር ሥር ማዋል ኢህአዴግ በሥልጣን ለመቆየት የሚጠቀምባቸው ዓይነተኛ መንገዶቹ እንደሆኑ በስፋት ይጠቀሳል፡፡
ይህንን የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ የቀመሩት ምሁር ስሌታቸውን ለማቀናበር የተለያዩ መረጃዎችን መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአገራቱ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በቅኝ ግዛት የመያዝ ሁኔታ፣ የአገራቱ ዕድሜ፣ ከነጻነት በኋላ የኖሩበት ዓመታት፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የእርስበርስ ግጭት፣ የነጻ ምርጫ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በየቀጣናው ያለ የመፈንቅለ መንግሥት እንቅስቃሴ፣ ወዘተ የተወሰኑት ናቸው፡፡ ይህንን አያይዘውም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ ማድረግ የግድ መፈንቅለ መንግሥት ይሆናል ማለት እንዳይደለ ነገር ግን አደጋውን ተመልክቶ አስፈላጊ እርምጃዎች በመውሰድ እንዳይሆን መከላከል ዓይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (ካርታዎቹ የተወሰዱት ከጄይ ዑልፌልደር ብሎግ ነው)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የዛሬ ዓመት የአሜሪካንን የደኅንነት ምክርቤት ጠቅሶ ባወጣው ዜና በ2030 እኤአ ከሚከሽፉ መንግሥታት (failed states) መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዘግቦ ነበር፡፡ ዜናውን ከዚህ በታች በድጋሚ አትመነዋል፡፡

“በ2030 ከሚከሽፉ መንግሥታት አንዷ ኢትዮጵያ ነች”

ዘገባው የ15 አገራትን ዝርዝር አውጥቷል
የአሜሪካ የብሔራዊ የደኅንነት ምክርቤት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2030 የሚከሽፉ 15 መንግሥታትን (failed states) ዝርዝር አውጥቷል፡፡ “በግጭት መብዛትና በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ምክንያት” ይከሽፋሉ ተብለው ከተተነበዩት የአፍሪካ፣ የእስያና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡
እጅግ የነጠረ፣ ያልተዛባና የተጠና ዘገባ ለአሜሪካ የስለላ ተቋማት፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አውጪዎችና ለዓለምዓቀፍ ግንኙነት ተመራማሪዎች በማውጣት የታወቀው የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ምክርቤት ከተቋቋመ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ምክርቤቱ በሚያወጣቸው ዘገባዎች የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ የተለያዩ መ/ቤቶች ተጽዕኖ እንደማያደርጉበት የሚናገር ሲሆን፤ ዘገባዎቹንም ከአድልዎ እና ከአሜሪካ መንግሥት አቋም ነጻ በመሆን እንደሚያዘጋጃቸው ይናገራል፡፡
NICየም/ቤቱ ዘገባ በተለይ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ለመጪው ፕሬዚዳንት የወደፊቱን የዓለማችን መልክ ምን እንደሚመስል የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ አስተሳሰቦች እና ዓለምአቀፋዊ ዝንባሌዎች ላይ አቅጣጫ የሚጠቁም ትንበያ ያደርጋል፡፡ ለፕሬዚዳንቱ ዓለምአቀፋዊ የደኅንነት ዘገባ ያቀርባል፤ ለብሔራዊ የጸጥታ ምክርቤት እና ለአገር ውስጥ ደኅንነት መ/ቤት ምክር ያቀብላል፤ በአጠቃላይ የአሜሪካን የስለላና የደኅንነት ማኅበረሰብ ሊከተል በሚገባው ጉዳይ ላይ አቅጣጫ የሚያስይዝ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
በዚሁም መሠረት ባለፈው የታህሳስ ወር “በ2030 የዓለም አቅጣጫ፡ አማራጭ አገራት” በሚል ርዕስ አንድ ዳጎስ ያለ ጥናት አቅርቧል፡፡ ይኸው 160ገጽ ያለው ዘገባ የዛሬ 17ዓመት የዓለማችን ገጽታ ምን እንደሚመስል ከየአገራቱ በተወሰደ ጥናትና እዚያው በሚገኙ ተመራማሪዎች የሰበሰበውን ያካተተ ነው፡፡ ዓለማችን የምታዘነብልባቸው ቀዳሚ ሁኔታዎች አንዱ ሰዎች በራሳቸው አነሳሽነት ድህነትን ለመቀነስ፣ በትምህርት ለማደግ፣ በቴክኖሎጂና በህክምና ለመራቀቅ እንዲሁም በገቢም የመካከለኛው መደብ ላይ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቀሱት አንዱ አቅጣጫ ጠቋሚ ነው፡፡
ሌሎቹ ዓለምን አንድ አድርጎ በመዳፉ ሥር የሚገዛ ኃይል የማይነሳ መሆኑ ከሚታዩት ከፍተኛ ዝንባሌዎች ተጠቃሽ ሲሆን አሜሪካ ምንም እንኳ “የዓለም ፖሊስ” የመሆኗ ሁኔታ የሚቀንስ ቢሆንም የዓለምን አቅጣጫ መቆጣጠሯ ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ የዓለም የሕዝብ ቁጥር ከመጨመሩ አኳያ “እያረጁ” የሚሄዱ አገራት የኢኮኖሚ ዕድገታቸው እንደሚያሽቆለቁልና ከገጠር ወደከተማ ፍልሰት እንደሚጨምር፤ 60በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በከተሞች አካባቢ ኑሮውን እንደሚያደርግ ይተነብያል፡፡ በዚህም ምክንያት የውሃ፣ የምግብና የኃይል (ኤነርጂ) ፍላጎት ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያድግ ይናገራል፡፡ የቴክኖሎጂ ምጥቀትና የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎትም የዓለማችንን አቅጣጫ እንደሚቀይር ያስረዳል፡፡
የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት በስፋት እንደሚቀጥልና በበርካታ ፈርጆች ትብብርና ስምምነት እየፈጸሙ ሰፋ ያለ ዓለምአቀፋዊ ኅብረት እንደሚያደርጉ የሚናገረው ይህ ሪፖርት በየአገራቱ እየሰፋ የመጣው በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ክፍተት የማኅበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ይጠቁማል፡፡ ይህም ቀውስ በአንዳንድ አገራት ውስጥ እየሰፋ በመምጣት ለተባባሰ ግጭትና ክስረት እንደሚያጋልጥ የኑሮ ልዩነቱም የማኅበራዊ ቀውሱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርሰው ይተነትናል፡፡ የሃይማኖት ሚና እንደሚጨምር የጠቆመው ዘገባ ይህንኑ ተከትሎ መካረርና ግጭት እንዲሁም አሸባሪነት ለመስፋፋት ሃይማኖት ምክንያት እየሆነ እንደሚሄድ ይናገራል፡፡
በዘገባው ከተነገረው በተጻጻሪ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ወዲህ እስካሁን በ44 አገራት ጉዳይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጣልቃ በመግባት ጦርነት ያካሄደችው አሜሪካ የዓለም ኃያል ሆና እንደምትቀጥል በመናገር ሪፖርቱን የሚያጣጥሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንደማስረጃም አድርገው አሜሪካ በተለያዩ አገራት ያላትን 737 የወታደራዊ ተቋማት ይጠቅሳሉ፡፡ ስለሆነም ዘገባው የአሜሪካ የበላይነት የመቀነሱን ጉዳይ አንስቶ የተናገረውን አይቀበሉም፡፡
እኤአ በ2030 የሚክሽፉት 15ቱ መንግሥታት (ፎቶ: ጂአይ)
ዘገባው የዓለማችንን የወደፊት ሁኔታ ሲተነብይ በዋንኛነት ከጠቀሳቸው ጉዳዮች አንዱ በ2030 የሚከሽፉ መንግሥታትን ዝርዝር ሰጥቷል፡፡ “በግጭት መብዛትና በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ምክንያት” የሚከሽፉ መንግሥታት ተብለው ከተጠቀሱት 15 አገራት መካከል ኢትዮጵያ እንዷ ስትሆን አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቻድ፣ ኒጀር፣ ማሊ፣ ኬኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ ማላዊ፣ ሃይቲና የመን የተቀሩት ናቸው፡፡
ይሁንና ይኸው ም/ቤት እኤአ በ2015 ፓኪስታን የምትከሽፍ አገር ትሆናለች በማለት ትንቢት ሰጥቶ ይኸው እስካሁን አለች በማለት ዘገባውን የሚያጣጥሉ ክፍሎች ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎቹ አገራት ለመክሸፋቸው በቂ ማስረጃ የለም በማለት የዘገባውን ጥቆማ ይቃረናሉ፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ ያለው የመክሸፍ ሁኔታ ሊዋጥለት የማይችለው ኢህአዴግ “ህዳሴ፣ ውዳሴ” ከማለት ይልቅ ይህንን ጉዳይ አጥብቆ ሊያስብበት እንደሚገባና የሥርዓት መበስበስ አመላካች የሆነውን “የመንግሥት ሌቦች” መበራከት መፍትሔ ሊያበጅለት እንደሚገባ ደጋፊዎቹና አመራሩ በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡
በዚሁ የኢትዮጵያ እንደ አገር የመክሸፍ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው አሁን ካላቸው ተግባር አኳያ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአውሮጳ የሚገኙ የፖለቲካና ዓለምአቀፋዊ ግንኙነት ተመራማሪ “ችግሩ የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚውም ነው” ይላሉ፡፡ “በአገር ውስጥ ያለው ተቃዋሚ ከውስጥ የሥልጣን ሽኩቻና ከስብሰባ/ውይይት ጋጋታ ባለፈ መልኩ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ሊያደርግ የሚችል የተቀናጀና ውጤታማ ተግባር ሊፈጽሙ ይገባቸዋል” የሚሉት ምሁር በውጭ ያለውም “ከጊዜያዊና ጥቃቅን የራስ ክብር የመፈለግ አካሄድ በመላቀቅ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ጡንቻውን በወያኔ ላይ ማሳረፍ ይጠበቅበታል” ብለዋል፡፡ “የደኅንነት ተቋሙ ባወጣው ዘገባ ላይ በግልጽ እንደተነበየው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ የመጨመሩ ያህል በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ይህንኑ ለውጥ ማምጣት የሚችል የዘመኑ ቴክኖሎጂ ለአሉባልታና ተራ የፖለቲካ ወሬ ከመጠቀም ይልቅ አገር ለማዳን ተግባር ሊጠቀምበት ይገባል” በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡
የደኅንነት ምክርቤቱ ያወጣው ሙሉ ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡
http://www.goolgule.com/coup-forecasts-for-2014/

No comments:

Post a Comment