Thursday, December 5, 2013

“መንግሥት ከግንቦት ሰባት ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ የለም” Ethiopian government did not request to negotiate with Ginbot 7

December 4/2013 (በሰንደቅ ጋዜጣ) “መንግሥት ከግንቦት ሰባት ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ የለም” Ethiopian government did not request to negotiate with Ginbot 7

በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፤ ኢህአዴግ ለደርድር ጥያቄ አቅርቦልኛል በሚል እያናፈሰ ያለው መሰረተ ቢስ የፈጠራ ወሬ መሆኑን አቶ ሽመልስ ከማል የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አስታወቁ።
ግንቦት 7፤ ህዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም በኢሳት ቴሌቪዥን በኩል ባወጣው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በሁለት ወር ጊዜያት ውስጥ ለሶስት ጊዜያት ያህል የእንደራደር ጥያቄ አቅርቦልኛል ብሏል። ንቅናቄው ለእንደራደር ጥያቄው ምላሽ በሚል ባሰፈረው ሐተታ የኢህአዴግ የእስካሁኑ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ውጥረት ሲበዛበትና መዉጪያና መግቢያዉ ሲጠፋዉ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችን “እንወያይ፣ እንደራደር” በማለት ለውጥረት ማስተንፈሻ ጊዜ ይገዛል ካለ በኋላ ስማቸው ባልተገለጸ መልዕክተኞች በኩል ደርሶኛል ያለውን “የእንደራደር” ጥያቄ ንቅናቄው በዋናነት ያየው ኢህአዴግ እንደለመደው ድርድርን ለውጥረት ማስተንፈሻነት ለመጠቀም እየሞከረ ነው በማለት ለድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።
አቶ ሽመልስ ከማል ግን በመንግስት በኩልም ሆነ በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በኩል ለግንቦት 7 የቀረበ እንደራደር ጥያቄ እንደሌለ አረጋግጠው መንግስት ቢፈልግ ጌታው እያለ ከተላላኪው ጋር ምን ያደራድረዋል ሲሉ ጠይቀዋል። ይህ የእነዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቅጥፈት መሆኑን ጠቅሰው “በዚህ መንገድ እያሞኙ ገንዘብ መሰብሰብ ለምደዋል፤ ይህም ውሽት ለዚሁ ተግባር የተፈበረከ ነው” ብለዋል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ ድጎማና ድጋፍ ለሚሰጧቸው አካላት ሒሳብ ለማወራረድ ድል አድርገን ልንገባ ነው በማለት ሲቀጥፉ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሽመልስ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በባዶ ሜዳ ራስን አግዝፎ ለማየት ከመመኘት የሚመነጭ ቅዥት ነው ብለውታል።

No comments:

Post a Comment