Monday, December 23, 2013

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስወጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ የለም ተባለ

  በደቡብ ሱዳን የተነሳውን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የደህንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ ቢሆንም መንግስት እስካሁን  እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑ ታወቀ።

የኢሳት የጁባ ወኪል እንደገለጹት አብዛኛው አገሮች ዜጎቻቻውን እያወጡ ነው ። ኬንያና ኡጋንዳ አውቶቡሶችን በመላክ ፣ አሜሪካና እንግሊዝ ደግሞ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን በመላክ ዜጎቻቻውን እያወጡ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን ጁባ ማረፉን ተከትሎ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ አውሮፕላኑ ግን ቻይናዎችን ብቻ ጭኖ መመለሱ ታውቋል።  ኢሳት ከአየር መንገዱ ለማረጋገጥ እንደቻለው የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻርተር አውሮፕላን በመከራየት  በነዳጅ ማውጣት ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎቹን ወስዷል።
እንዲሁም   ለሽምግልና ጁባ የሄዱትን የኢትዮጵያን ባለስልጣናት በማሳፈር ጁባ ያረፈ አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን፣ ባለስልጣኖችን ካወረደ በሁዋላ ትኬት ቆርጠው ለመውጣት ይጠባበቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ሳይጭን ባዶውን ተመልሷል። ኢትዮጵያውያኑ የኬንያንና የኡጋንዳን አየር መንገዶችን ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ አየር መንገዶቹ ከፍተኛ ዋጋ በመጠየቃቸው ትኬቶችን ለመግዛት አልቻሉም።
ኢሳት ለማረጋገጥ ባይችልም ሶሰት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መደፈራቸውን የሚያመለክት ዜና ደርሶታል። አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም ንብረታቸውን ተዘርፈው በጁባ መንገዶች ላይ ያለ ደጋፊ ሲዞሩ እንደሚታይ ወኪላችን ገልጿል።
የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ  እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ላለፉት ሁለት ቀናት በጁባ ተገኝተው ሁለቱን ሀይሎች ለመሸምገል ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቋል። ደ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ሁለቱንም ሀይሎች ለማቀራረብ ከፕሬዚዳንቱ ጥሩ ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ቦር የተባለው አካባቢ በአማጽያን እጅ የወደቀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ድንበር በሆነው አኮቦ በትናንትናው እለት ጦርነት ተከፍቷል። ዛሬ ደግሞ ማላኪ፣ ዋው እና ባንቲዩ በተባሉት አካባቢዎች ጦርነት ተከፍቷል። ባንቱዊ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት የሚገኝበት ሲሆን፣ በርከታ የዲንቃ ተወላጆች በጽህፈት ቤቱ ግቢ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል። በጁባ የኑዌር ተወላጆች ከዲንቃ ጎሳዎች ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ብለው በተመድ ጽ/ቤት ውስጥ ሲጠለሉ፣ በቤንቲዩ ደግሞ በተቃራኒው ዲንቃዎች ተጠልለዋል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ አዲሲቷ አገር ወደ እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል። እስካሁን ባለው አሀዝ ከ500 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል።

No comments:

Post a Comment