Wednesday, December 25, 2013

በደቡብ ሱዳን ተገደው የተደፈሩ 4 ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጁባ ገቡ

 በደቡብ ሱዳን የተነሳውን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ የተደፈሩ 4 ሴቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሆስፒታል በሚገኝበት ጁባ ደርሰው ምርመራ 

እየተደረገላቸው ነው። ሴቶቹ መደፈራቸውንና ሆስፒታል መግባታቸውን ኢሳት ለማረጋገጥ የቻለ ሲሆን፣ ሴቶቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ

 ያደረገው ጥረት በመስመር ግንኙነት የተነሳ ሊሳካለት አልቻለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ታውቋል። አምባሳደሩ በዚህ አስቸጋሪ ሰአት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን በአገሪቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተችተዋል።

በሌላ በኩል ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም  የኢትዮጵያን ስደተኞች በተመለከተ ኢምባሲው በቅርበት ጉዳዩን እየተከታተለ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ለሱዳን ችግር የኢጋድ አገሮች የሽምግልና ጥረት መጀመራቸውንም ገልጸዋል። በሽምግልና ጥረቱ ስለተገኘው ውጤት ግን ያሉት ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን የ እርስበርስ ግጭት ተከትሎ  ጎሳ ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያ እንደተፈፀሙ የሚያሳዩ አዳዲስ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።
ጋዜጠኞች ከጁባ የዓይን ምስክሮችን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት ግጭቱን ተከትሎ ከ200 በላይ የሚሆኑ የንዌር ጎሳ ተወላጆች በደህንነት ሀይሎች በጅምላ ተገድለዋል።
ሌላ የጁባ ነዋሪም ሲናገር ብዙዎቹ የጸጥታ ሀይሎች ከዲንካ ጎሳ አባላት ስለሆኑ ኑዌሮችን  እየለዩ ይገድሉ ነበር ብሏል።
ከሳምንት በፊት በጁባ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደተለያዩ ቦታዎች ተሸጋግሮ በሪክ ማቻር የሚመሩት አማጽያን  “ቦር” እና “ቤንትዩ” የተሰኙ ቁልፍ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።
ፕሬዜዳንት ሳልቫኪር  የቀድሞ ምክትላቸው መፈንቅለ መንግስት ሊፈፅሞባቸው እንዳሰቡ ክስ ቢያሰሙም፤ ሪክ ማቻር ግን  በተቃውሞ የተነሱት በስርዓቱ እየተፈፀመ ባለው ጎሳ ላይ ያነጣጠረ የመብት ረገጣ እና ጥሰት ተከፍተው እንደሆነ በመግለጽ ነው  ክሱን ያስተባበሉት።
በቀድሞ  ሁለት  የትግል ጓደኛሞች መካከል በስልጣን ማግስት የተከሰተው ይህ ግጭት በኑዌር እና ዲንካ ጎሳዎች መካከል ሙሉ ጦርነት በማስነሳት ደቡብ ሱዳንን ዳግም መውጫ ወደሌለው የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳይከታት ከፍተኛ ስጋት ማሳደሩን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ሰሞኑን በአማጺዎች ቁጥጥር ስር ውላ ነበረችው ቦር በመንግስት ሀይሎች እጅ መውደቋን ቢቢሲ ዘግቧል። የመንግስት ቃል አቀባይ እንደሉት ጦራቸው ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ከአማጽያን እጅ አስለቅቀዋል። አማጽያኑንም እግር በግር እየተከተሉ እየወጉዋቸው ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ማምሻውን እንዳስታወቁት ደግሞ በአገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሳይገደሉ አልቀረም። በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በጅምላ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች ማግኘታቸውን ባለስልጣኑ ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment