Monday, February 9, 2015

ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ!

ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ!

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
isayas a fewerki
አቶ ኢሳይያስ እንዴት ነዎት ባያሌው? ሌሎቹ የሕዝባዊ ግንባር አመራሮችስ እንዴት ናቸው? ሕዝቡስ እንዴት ነው? አቤት! አቤት! አቤ……..ት! ለማንኛውም ድምፅዎን ማሰማትዎ መልካም ነው፡፡
በቅርቡ ለኢሳት የራዲዮና የቴሌቪዥን (የነጋሪተ-ወግና የምርዓየ-ኩነት) ጣቢያ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ጣቢያው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያደርስልዎት ዘንድ ከኢሳት ጋዜጠኞች ጋር ቃለመጠይቁን ማድረግዎን ሰማን፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልን! እግዚአብሔር ያክብርልን! ብለናል፡፡ ግን እንዲያው እውነት ለመናገር አቶ ኢሳይያስ ከአማርኛ ይልቅ እንግሊዝኛው ቀንቶዎት ቀርቦዎት ቀሎዎት ነው ከፊሉን ቃለ ምልልስ በእንግሊዝኛ ያደረጉት? በእርግጥ አባትዎ እንዳስጠነቀቁዎት ጠንቅቀው (perfectly) በማያውቁት ቋንቋ ያውም ቃለ መጠይቅን ያህል ነገር ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን እኮ አቶ ኢሳይያስ የእርስዎ አማርኛ ደኅና እና እንዲያውም ከአብዛኞቻችንም የተሻለ አልነበረም እንዴ? ምን ወሰደብዎት?
ለማለት ያህል “የጥላቻ አይደለም” ይበሉ እንጅ አማርኛ ለመናገር አለመፈለግዎ እውስጥዎ ሊሻገሩት ያቃተዎት የጥላቻ አጥር እንዳለ የሚያሳይ አይመስልዎትም? አማርኛን ጥላቻው ለምን? እናንተ እንደምትሉት የቅኝ ገዥያቹህ ቋንቋ ስለሆነ? አማርኛችንም እኛም እንኳን ቅኝ ገዥ አልነበርንም የአንድ ሀገር ሰዎች እንጅ፡፡ ባይሆን እንግሊዝኛዎት የቅኝ ገዥዎ ቋንቋ ስለሆነ በዚህ ምክንያት ጥላቻው ሊሰማዎት ከተገባ ጥላቻው ሊሰማዎት ይገባ የነበረው ለእንግሊዝኛው እንጅ ለአማርኛስ አልነበረም፡፡ ነው ወይስ ይሄ የዲፕሎማሲ (የአቅንኦተ-ግንኙነት) ነገር አይሆንልዎትም? ለነገሩ በዲፕሎማሲ (በአቅንኦተ-ግንኙነት)  ብልጠት ውስጥዎ የማያምንበትንና የማይፈልገውን ነገር አድርገው ከሚሸነግሉን እሱው ሳይሻል አይቀርም ስለሆነም ትክክል ነዎት፡፡
አቶ ኢሳይያስ እኔ እማ እልዎት! የኢሳት ጋዜጠኞች አስመራ መግባታቸውን ከዚያም ደግሞ ቃለ ምልልስ ለመስጠት እርስዎ መፍቀድዎን ወይም ኢሳት ለእርስዎ መፍቀዱን ስሰማ ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር አገናዝቤ አንዳች ግራሞት (surprise) ከእርስዎ ጠብቄ “ብራቮ ኢሱ” ብየ ሽቅብ በደስታ ለመዝለል እራሴን አዘጋጅቸ ስጠባበቅ ነበር የሰነበትኩት፡፡ ነገር ግን ይገርምዎታል ይሄ እንዳልሆነ ሳውቅ እጅግ ነበር የተከፋሁት፡፡ በእጅጉም አዝናለሁ፡፡ እንግዲህ ወይ እኔ እጅግ ሲበዛ የዋህ ነኝ ወይ ደግሞ እርስዎ እጅዎ የገባውን ወርቃማ ዕድል ሊረዱ የማይችሉና ይሄንንም ያበላሹ ማስተዋል የጎደለዎት ደካማ ሰው ነዎት ማለት ነው፡፡
አቶ ኢሳይያስ አይጠራጠሩ ከሁለቱ አንደኛው እውነት ነው፡፡ አይታወቅም ሁለቱም ሊሆን ይችላል፡፡ የሚያሳዝነው እኔ እጅግ ሲበዛ የዋህ በመሆኔ ተስፋ የማይደረግን ነገር ተስፋ አድርጌ ቢሆንም እንኳ በእኔ ባሳፈረኝ የዋህነቴ ውስጥ ቁልጭ ብሎ የሚታየው እርስዎ እምነት ሊጣልብዎት የማይችሉ ሰው መሆንዎ ነው ምክንያቱም ስንት ነገር እያለ ያንን ሁሉ ትቶ በወንድማዊ ፍቅር እንዲህ ተስፈኛ ያደረገውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቅንና ንጹሕ ሰብእና በመረዳት ቅንና በጎ ምላሽ መስጠት የማይችሉ መሆንዎን ስለሚያሳይ ስለሆነም በነገሩ ትዝብት ላይ የሚወድቀው ከእኔ ከየዋሁ ይልቅ እርስዎ ነዎት፡፡ ነገሩ ግን ማናችንንም አይጠቅምም፡፡ ምክንያቱ ሁለተኛው ከሆነ ደግሞ ማለትም እርስዎ አሁን ካለው ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ አንጻር ጉዳዩን በመረዳት አርቀው በማሰብ ግራ ቀኙን በመቃኘት ከኪሳራ ትርፍን፣ ከጥል ፍቅርን፣ ከጦርነት ሰላምን፣ ከጥፋት ልማትን፣ ከቅርብ አዳሪነት ሩቅ አላሚነትን፣ ከጥፋት ጋር ከመጥፋት በንስሐ መታደስን በመምረጥ እጅዎ የገባውን ወርቃማ ዕድል በሰዓቱ በመጠቀም ለራስዎም ለሀገርዎም ለሕዝባችንም ታሪክ ይሠራሉ የሚለውን የኛን የተሳሳተና እጅግ ተስፈኝነት የተሞላ ግምትና ምኞታችንን እውን ለማድረግ ወያኔም በእርስዎ እጅ የገባውን ካርድ ነጥቆ ለራሱ ሊጠቀምበት እየነዛ ያለውን ወሬና ሌሎች ተጨባጭና ገዝፈው ያሉ ሀቆችን ተገንዝበው ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ባለመቻልዎ ዕድሉን ያበላሹ ደካማ ሰው ሆነው ከሆነም ይሄም የማይጠቅመውና የሚከፋበት ለእኔ ሳይሆን በተለይ ለእርስዎ ነው፡፡
ለማንኛውም አቶ ኢሳይያስ አፍሬብዎታለሁ አዝናለሁ፡፡ የሰው ጭንቅላት ላለው ሁሉ ካሳለፍነው ሕይዎት የግዳችንን ከሚያስተምሩ ብዙ ነገሮች ብዙ ተምረዋል ብየ ሳስብ ምንም ሳይማሩ ስላገኘሁዎት እጅግ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ አቶ ኢሳይያስ ለመሆኑ 23 ዓመታት ሙሉ የት ነበሩ? በአንድ ሰው ዕድሜ ከነገሮች ለመማር ከዚያ በፊት ያለውን ትተን 23 ዓመታት እኮ እጅግ በጣም ብዙ ጊዜ እኮ ነው፡፡ ይሄንን ሁሉ ዓመት የት ምን እየሠሩ ነበሩ? ሌላ ዓለም ላይ? ከባድ እንቅልፍ ላይ? ወይስ ምን ውስጥ ገብተው ከረሙ? “ተማር ላለው በአርባ ቀኑ ይማራል አትማር ያለው ግን በአርባ ዓመቱም አይማር” ነበር የሚለው ያገሬ ሰው እርስዎ ስንት ዓመትዎ ነው? ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህን ያህል ጊዜ ያልተማሩ ሌላ ከምን በምን ያህል ጊዜ ሊማሩ ነው? ምን ነው? ምን ነው? ምን ነው? አቶ ኢሳይያስ? በጤናዎም አይደሉ እንዴ? ይሄንን ያህል ዘመን ያሳለፍናቸው ተጨባጭ ሀቆችን እንደ ተረት ተወርቶልን ሳይሆን ኖረንባቸው፣ ተበልተንባቸው፣ ተለብልበንባቸው፣ ከስረንባቸው፣ ተቃጥለንባቸው፣ አፈር ግጠንባቸው የዳከርንባቸውን ስንክሳሮች እንዴት መገንዘብ መረዳት ከእነሱም መማር አቃተዎት? ምንድን ነው የሚጠብቁት? ምንድንስ ነው የሚመኙት? የሚያልሙትስ? እንዴት? ለምን? እኮ ለምን? በጣም ነው የማዝነው፡፡ ዝም ብየ ሳስብዎት ዕድለ ቢስ ቁማርተኛ መስለው ይታዩኛል ከአሁን አሁን ይቀናኛል እያለ ሲበላ ሲበላ መጨረሻ ላይ እርቃኑን እንደሚቀረው፡፡
አቶ ኢሳይያስ ግን እርግጠኛ ነዎት ያዋጣናል? ያ ነባሩ ዜማ ከቶውንም እንደማያዋጣ ያሳለፍነው ሁሉ ከበቂ በላይ አይናገርም? ደሞ እንደገና ሌላ ተጨማሪ የመከራ ዘመን ያስፈልገናል? እርስዎንና መሰሎችዎን ከዚህ ተጠቃሚ የሚያደርግዎት ምንድን ነው? ምንድንስ ነው የሚያስፈራዎት? መሪ ማለት ምን ማለት ነው የሚመስልዎት? ሚናው ኃላፊነቱስ? እንደ ሰው እንደ መሪም ወደፊት ታሪክ ምን ብሎ እንዲያዎሳዎት ነው የሚፈልጉት? ምን ያስደስትዎታል? ለምን? ሰው ሆኖ የማይሳሳት ይኖራል ብለው ያስባሉ? ስሕተትን አምኖ መታረም እንዴት እንደተራራ ከብዶ ሊታይዎት ቻለ? ምንድን ነው እሱ የዚህን ያህል ተስፋ ያስቆረጠዎት ነገር? እርስዎ በታረሙ ለንስሐ በበቁ እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ስሕተትዎ የቱንም ያህል ከባድና በርካታም ቢሆን ይቅር ለማለት አንዲት ጋት እንኳን ወደ ኋላ የሚል ሕዝብ አልነበረም፡፡ ያልፈጠረበትን! ከመታረም በንስሐ ከመመለስ ይቅር ከመባባል ልናገኘው እንችል የነበረው ሰላም፣ ተድላ ድስታ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ እድገት፣ ብልጽግና ወዘተ. እንዴት ሊታይዎት አልቻለም? ምን ከለለብዎት? ምን ጋረደብዎት? የእውቀት ማነስ? ክፉ ሰብእና? ጠባብነት? ጎጠኝነት? ጥላቻ? ቅጥረኝነት? እልህ? ካፈርኩ አይመልሰኝ? ክፋት? ሰይጣናዊ ዓላማ? ወይስ ሌላ ምን? ከእልህና ከካፈርኩ አይመልሰኝ ምን ማትረፍ ይቻላል? እንዴት እርስዎን የሚያህል ሰው በእልህና በካፈርኩ አይመልሰኝ የደናቁርት አስተሳሰብ ይታነቃል? በእርስዎና መሰሎችዎ እንዲህ መሆን የሚሊዮኖች (የአእላፋት) ዕድል የቀጠናው ዕጣ ፋንታ መበላሸቱ እንደሰው አያሳዝንዎትም? አያሳስብዎትም? ለነገሩ “ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል” አይደል እንዴ! የሚለው መጽሐፉስ? የዘሩትን ሊያሳጭድዎት ይሆናላ እንግዲህ፡፡ እንግዲህ ልብ ይስጣቹህ እንጅ ሌላ ምን ይባላል? ጨርሻለሁ፡፡ ይብላኝላቹህ ለእርስዎና ለመሰሎቹዎ እንጅ እኛስ ከእርስዎና ከመሰሎቹዎ ያጣነውን ሁሉ በእግዚአብሔር እርዳታ በቅርቡ እንደምናገኘው እንደሚያዩትም በእግዚአብሔር ስም አረጋግጥልዎታለሁ፡፡
አቶ ኢሳይያስ ይሄንን ስልዎት ቃለ መጠይቁን አዳምጨው አይደለም ገና ተተርጉሞ አልተለቀቀምና፡፡ ነገር ግን “ዘፋኝ ካወሳወሱ ያስታውቃል” አይደል የሚባለው? አዎ! በምን በምን ጉዳይ ላይ ምን ምን እንደተናገሩ ቅምሻ ቅምሻውን ስሰማው አንዳችም አዲስ ነገር እንደሌለው ተረዳሁ፡፡ “ለምን አንዲት ቃል ትበቃዋለች” አይደል የሚለው መጽሐፉ? በየዋህነቴ ተስፋ ያደረኩትና የጠበኩት ነገር መና ሆኖ እንደቀረ ስለገባኝ ነው፡፡ ይሄ ሦስት ሰዓታት ያህል የፈጀ ቃለ መጠይቅ በእብለት በክህደትና በማስመሰል የተሞላ እንደሚሆን እገምታለሁ ምክንያቱም ለምሳሌ በእናንተ እጅ ደብዛቸው ስለጠፋ የአንድነት ከዋክብት ብርቅ ድንቅና ቆራጥ የኢትዮጵያ ልጆች ተጠይቀው ሐሰት ነው ብለው እንደመለሱና ማንኛውም ሰው መጥቶ ሊያረጋግጥ እንደሚችል መናገርዎን ሰምተናል፡፡ ጥሩ አቶ ኢሳይያስ ታዲያ እነዚያን ሳተና ወንድሞቻችንን ምኑ በላቸው? የት ደረሱ? ወይ በነበረን የተሳሳተ አመለካከት ስሕተት ሠርተናል አጥፍተናል ይቅርታ ይደረግልን ይቅር በሉንና ይሄንን የጨለማ የሞት የጥፋት መዝገብ ይቅር በመባባል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግተን ከሰጠምንበት ማጥ ከወደቅንበት ትቢያ ስለምንወጣበት ስለምንነሣበት ቁም ነገር በአንድነት እናቅድ እንምከር፣ ስለ ወደፊቱ እናስብ፣ ሕይዎታችንን እጣ ፋንታችንን እንዴት እናብጀው እናሳምረው? ስለሚለው እንወጥን ቢሉ መልካም በሆነ ነበር፡፡ እርስዎ ግን ይሄንን ሊያደርጉ አልቻሉም፡፡ እርስዎ የያዙት ባዶ የቃላት ጨዋታ ነው ያውም ሳይችሉበት፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታ እኛ ታዲያ እንዴት እንመንዎት አቶ ኢሳይያስ? እዚህ ከእኛ ዘንድ እንደፈለጉ ሊያታልሉት ሊሸነግሉት የሚችሉት ሕፃን ያለ ይመስልዎታል? ይሄንን ያህል ያልበሰሉ ነዎት ማለት ነው? ይሄንን ያህል አንተዋወቅም ማለት ነው? በዚህ በዚህ ገራቹህ ከወያኔ ጋራ አንድ ናቹህ፡፡ ቆይ ግን ማንኛቹህ ነው ሌላኛቹህን ያስተማረው? አባትየው ልጅየውን ወይስ ልጅየው አባትየውን? እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት ይሄንን ለኢሳት የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ለምን ፈለጉት? ዓላማውስ ምንድን ነው?
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
አቶ ኢሳይያስ አንድ ላሳስብዎት የምሻው ጉዳይ ቢኖር አሁንም ቢሆን ያ ወርቃማ ዕድል ከእጅዎ አልወጣም ገና አላመለጠምና ከነቁ ከባነኑ ከእጅዎ ከማምለጡ በፊት ወይም ወያኔ እየሞካከረው እንዳለው የታሪክ አጋጣሚ እጅዎ ላይ የጣለውን ዕድል ከእጅዎ ነጥቆ ለራሱ ከመጠቀሙ በፊት ሸርን፣ ሴራን፣ ተንኮልን፣ ክፋትን፣ ጥላቻን ወዘተ. ወደኋላዎ መልሰው ላያነሷቸው ጥለው ንጹሕ ልብዎን ብቻ ይዘው በመቅረብ ወርቃማውን ዕድል ቀድመው ይጠቀሙበትና በዚህ ሕዝብና በዚህች ሀገር ላይ ተጭኖ ያለውን መርገም ከላያችን አሽቀንጥረን ለመጣል እናብር፡፡ በእርግጠኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ እየፈነጠዘ ጥሪዎን በደስታ ይቀበላል ጉዳያችንንም በአንድ ጀምበር የምንቋጨው ይሆናል፡፡ ከዚያም ፀሐያችን ትወጣለች ተስፋችን ተአምር በሚባል ፍጥነት ይለመልማል፡፡ አቶ ኢሳይያስ ሕዝባችን እኮ ብዙ ቀድሞ ሄደ መሪ ከሕዝቡ ሲቀድም እንጅ በሕዝቡ ሲቀደም ደስ አይልም ብዙ ኪሳራም ያስከትላል፡፡ የምልዎ ነገር ግልጽ ነው አይደል አቶ ኢሳይያስ? እንደተረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይመኑኝ ይሄንን ያደረጉ እንደሆነ ብቻ ነው የሁላችምን ምኞት የሚሰምረው በጎ ሕልማችን እውን የሚሆነው፡፡ መልካም ዕድል እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋር ይሁን!!!

Speak Your Mind

*

No comments:

Post a Comment