Wednesday, December 25, 2013

በደቡብ ሱዳን ተገደው የተደፈሩ 4 ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጁባ ገቡ

 በደቡብ ሱዳን የተነሳውን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ የተደፈሩ 4 ሴቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሆስፒታል በሚገኝበት ጁባ ደርሰው ምርመራ 

እየተደረገላቸው ነው። ሴቶቹ መደፈራቸውንና ሆስፒታል መግባታቸውን ኢሳት ለማረጋገጥ የቻለ ሲሆን፣ ሴቶቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ

 ያደረገው ጥረት በመስመር ግንኙነት የተነሳ ሊሳካለት አልቻለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ታውቋል። አምባሳደሩ በዚህ አስቸጋሪ ሰአት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን በአገሪቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተችተዋል።

በሌላ በኩል ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም  የኢትዮጵያን ስደተኞች በተመለከተ ኢምባሲው በቅርበት ጉዳዩን እየተከታተለ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ለሱዳን ችግር የኢጋድ አገሮች የሽምግልና ጥረት መጀመራቸውንም ገልጸዋል። በሽምግልና ጥረቱ ስለተገኘው ውጤት ግን ያሉት ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን የ እርስበርስ ግጭት ተከትሎ  ጎሳ ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያ እንደተፈፀሙ የሚያሳዩ አዳዲስ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።
ጋዜጠኞች ከጁባ የዓይን ምስክሮችን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት ግጭቱን ተከትሎ ከ200 በላይ የሚሆኑ የንዌር ጎሳ ተወላጆች በደህንነት ሀይሎች በጅምላ ተገድለዋል።
ሌላ የጁባ ነዋሪም ሲናገር ብዙዎቹ የጸጥታ ሀይሎች ከዲንካ ጎሳ አባላት ስለሆኑ ኑዌሮችን  እየለዩ ይገድሉ ነበር ብሏል።
ከሳምንት በፊት በጁባ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደተለያዩ ቦታዎች ተሸጋግሮ በሪክ ማቻር የሚመሩት አማጽያን  “ቦር” እና “ቤንትዩ” የተሰኙ ቁልፍ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።
ፕሬዜዳንት ሳልቫኪር  የቀድሞ ምክትላቸው መፈንቅለ መንግስት ሊፈፅሞባቸው እንዳሰቡ ክስ ቢያሰሙም፤ ሪክ ማቻር ግን  በተቃውሞ የተነሱት በስርዓቱ እየተፈፀመ ባለው ጎሳ ላይ ያነጣጠረ የመብት ረገጣ እና ጥሰት ተከፍተው እንደሆነ በመግለጽ ነው  ክሱን ያስተባበሉት።
በቀድሞ  ሁለት  የትግል ጓደኛሞች መካከል በስልጣን ማግስት የተከሰተው ይህ ግጭት በኑዌር እና ዲንካ ጎሳዎች መካከል ሙሉ ጦርነት በማስነሳት ደቡብ ሱዳንን ዳግም መውጫ ወደሌለው የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳይከታት ከፍተኛ ስጋት ማሳደሩን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ሰሞኑን በአማጺዎች ቁጥጥር ስር ውላ ነበረችው ቦር በመንግስት ሀይሎች እጅ መውደቋን ቢቢሲ ዘግቧል። የመንግስት ቃል አቀባይ እንደሉት ጦራቸው ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ከአማጽያን እጅ አስለቅቀዋል። አማጽያኑንም እግር በግር እየተከተሉ እየወጉዋቸው ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ማምሻውን እንዳስታወቁት ደግሞ በአገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሳይገደሉ አልቀረም። በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በጅምላ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች ማግኘታቸውን ባለስልጣኑ ገልጸዋል።

ኢኮኖሚያችን ሲያድግ የህዝቡ ኑሮ ለምን አሽቆለቆለ?


December 25, 2013
ማስተዋል ደሳለው
ላለፉት 8 እና ዘጠኝ ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ አያደገ ነው ሲባል እንሰማለን፤  የእድገት ፍጥነቱ  ላይ የሚነሱ በርካታ ጥያቄውች  ቢኖሩም መንግስት  የመንገድ ግንባታ ፣ የኃይል ማመንጫ ግንባታወችን እና መሰል ነገሮችን  በመጥቀስ እድገት እንዳለ አስረግጦ ይከራከራል::  በሌላ በኩል የኢኮኖሚ እድገቱ ተመዘገበ በሚባልባቸው ዓመታት በዋጋ ንረት የህዝቡ ኑሮ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ  እንደሆነ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው:: ታዲያ  የኢኮኖሚ እድገት አለ በተባለባቸው ዓመታት የህዝቡ ኑሮ ለምን አሽቆለቆለ? ይህን ጥያቄ ከ 7 ዓመት በፊት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ  ተጠይቀው የሰጡት መልስ የዋጋ ንረቱን የኢኮኖሚ እድገቱ እራሱ የፈጠረው ጉዳይ ነው ነገር ግን ቀስ በቀስ እድገቱ ሲቀጥል ራሱ እድገቱ ችግሩን ይፈታዋል ብለው ነበር፤ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በዃላም እንኩአን ሊሻሻል  የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየባሰበት ሂዷል::  ችግሩ የተለያዩ  ምንጮች ቢኖሩትም በዋናነት በ 2 ከፍሎ ማየት ይቻላል::
፩. የኢኮኖሚ እድገቱ ምንጭ
፪. የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር
የኢኮኖሚ እድገት ማለት በአጭሩ ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ተጨማሪ ሀብት መፍጠር ማለት ነው::  በመጀምሪያ ላለፉት 8  እና ዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ  የተፈጠሩት ተጨማሪ ሀብቶች ምንድን ናቸው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ፤  በአብዛኛዉ ሀገሪቱ ዉስጥ የተፈጠሩት ሀብቶች ከመንገድ ፣ ከሕንፃ እና ከ ከኃይል ማመንጫ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ናቸው:: በመቀጠልም የዚህ ሀብት የገንዝብ ምንጭ ምንድን ነው ብሎ ማየት ያስፈልጋል፤ የገንዘቡ ምንጭ በዋናነት ከብድር እና እርዳታ የተገኘ ሀብት ነው ፣ በተለይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ 1998 ዓም ጀምሮ በሶማሊያ በመጀመሪያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት በመቀጠልም የአልሻባብ እንቅስቃሴ መጠናከር ለኢትዮጵያ ትልቅ ሲሳይ ይዞ ነው የመጣው:: በሶማሊያ ያለዉን ሁኔታ  ለመቆጣጠር ምዕራባዉያኑ የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ  በዋና አጋርነት የተሰለፈችዉ ኢትዮጵያ ላለፉት ስምንት ዓመታት በየዓመቱ በቢልየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በእርዳታ መልክ ከምዕራብ ሃገራት እንድታገኝ አድርጓታል:: ይህም ማለት ሀገሪቱ ዉስጥ የጎላ  የኢኮኖሚያዊ መዋቅር ፣ የአሰራር ስርዓት  እና የቴክኖሎጅ ለውጥ ሳይኖር ከፍተኛ ገንዘብ ወደኢኮኖሚው ፈሰስ እንዲሆን አድርጓል:: በሌላ አገላለፅ  የቆየው የሀገሪቱ  ኢኮኖሚ የጎላ የምርት ጭማሪ ሳይኖረው ከዉጭ የተገኘ ብድር እና እርዳታ ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ተጨመረ እና የኢኮኖሚዉ መጠን አደገ ማለት ነው::  ስለዚህ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ እና የሀገሪቱን ተወዳዳሪነት ሊያሻሽል የሚችል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የጎላ  ለዉጥ ሳይታይ ለመሠረት ልማት ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ፈሰስ የተደረገው ገንዝብ የገንዘብ አቅርቦትን (Money Supply) በመጨመር እና  የአገልግሎት ዘርፉ ( Service sector) ከሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተነጥሎ እንዲለጠጥ እንዲሁም ዋጋ እንዲንር በማድረግ አብዛኛዉን ሕዝብ ለችግር አጋለጠ ::
ከብድር እና እርዳታ የተገኘው ገንዘብ መሰረተ ልማት ላይ ሲዉል ከላይ የተገለፀው ችግር ቢኖርበትም በአንፃሩ የመሰረተ ልማት መስፋፋት የማምረቻ ወጭ ( cost of production) እንዲቀንስ በማድረግ የሚያስገኘው ጥቅም አለ ፤ በተጨማሪም ገንዘብ ገንዘብን ይፈጥራል “ money creats money” በሚለው የኢኮኖምክስ  መርህ መሰረት ኢኮኖሚዉ ዉስጥ የተረጨው ገንዘብ በአብዛኛዉ አገልግሎት ዘርፉ ላይ የፈጠረው ተጨማሪ ሀብት አለ:: ነገር ግን ይህ የተፈጠረ ተጨማሪ ሀብት በጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ስላልተመራ ወደጥቂት ሰወች እጅ እንዲገባ ሁኗል::  ሃብቱ እጃቸው የገባ ሰወችም የኢኮኖሚዉን መዋቅር ሊለዉጡ የሚችሉ እንደኢንዱስትሪ አይነት ዘርፎች ላይ ከመሰማራት ይልቅ ከሙሰኛ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለዉን የከተማ ቦታ በኢንቨስትመንት እና በሊዝ ስም በመዉሰድ ህንፃ በመገንባት እየተለጠጠ ላለው የአገልግሎት ዘርፍ በማከራየት በአቁአራጭ ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ ተጠቀሙበት::
በሌላ በኩል የሀገሪቱ የመሬት አስተዳደር ስርዓት በሙስና የተጨማለቀ እና ወጥ ስላሆነና አዳዲስ ብቅ ለሚሉ ባለሀብቶች መሬት ማግኘት ከባድ ስለሆነ ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ወሳኝ ሀብት (strategic resource) የሆነዉን የከተማ ቦታ ቀድመው የያዙ ባለሀብቶች የገቢያ ዉድድሩን ሚዛናዊ እንዳይሆን በማድረግ አዲስ የሚፈጠሩ ተወዳዳሪያቸውን በቀላሉ ከገቢያ ያስወጣሉ:: በተጨማሪም እንደነዚህ አይነቶቹ  ባለሀብቶች በአብዛኛው የፖለቲካዉ እና የግዥዉ ፓርቲ ጥገኛ ስለሆኑ የሚጠበቅባቸዉን ያክል  ግብር እና ታክስ አይከፍሉም:: ሥራቸዉን ስለሚያውቁም በሀገሪቱ በረጅም ጊዜ ሊከሰት ይችላል ብለው የሚፈሩትን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ስለሚሰጉ የሚያገኙትን ትርፍ ወደዉጭ ያሽሻሉ ፤ በጎን ሙሰኛ ባለስልጣናትም የሚዘርፉትን ገንዘብ ከሀገር ያሸሻሉ:: ከዚህ ላይ ፋይናንሽያል ትራንስፓረንሲ ኳሊሽን  ያወጣዉንና ኢትዮጵያ በህገወጥ የገንዘብ ፍሰት (illicit financial flow) በፈረንጆቹ ከ 2000 እስከ 2009 ያጣችዉን 11. 7 ቢልየን ዶላር ልብ ይሏል::
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጤናማ ሁኖ እንዲያድግ ከተፈለገ ከላይ የተጠቀሱት  የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መዋቅር ድክመቶች መስተካከል የሚገባቸዉ ሲሆን ፤ በዉጭ ብድር እና እርዳታ ላይ መንጠልጠሉን ቀንሶ ከሀገር ቤት በፍትሃዊነት ከሚሰበሰብ ግብር ሊሆን ይገባል:: ከዉጭ የሚገኘዉን ሀብትም  በብዛት መሰረተ ልማት ላይ ብቻ ማዋሉ የሚያስከትለዉን ችግር ጥልቅ ጥናት በማካሄድ  መመርመር እና  ገንዘቡ ከመሰረተ ልማቱ ጎን ለጎን የኢንዱስትሪው እና የእርሻዉን ዘርፍ መዋቅር ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ለማስቻልም መሰራት አለበት:: ከሁሉም በላይ ግን የኢኮኖሚ ነቀርሳ የሆነዉን ሙስና ለማስወገድ ከአንድ ፓርቲ የበላይነት ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መሸጋገር እንዲሁም ተጠያቂነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ እንደገለልተኛ ፍርድ ቤቶች ፣ የግል መገናኛ ብዙሃን  የመሳሰሉትን ተቋማት መፍጠር ያስፈልጋል:: ይህ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ ሽህ ጊዜ ብታድግ የኢኮኖሚውን ፍሬ ጥቂቶች እየበሉ የአብዛኛዉ ሕዝብ  ኑሮ ማሽቆልቆሉ ይቀጥላል::

Monday, December 23, 2013

ጉቦ በመቀበል እስረኞችን ፈተዋል የተባሉ የማረሚያ ቤት ሹሞች ታሰሩ

-እስከ 500 ሺሕ ብር ሲቀበሉ እንደነበር ተጠቁሟል

ከአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ከ40 ሺሕ ብር እስከ 500 ሺሕ ብር ድረስ ጉቦ በመቀበል፣ ከአምስት ዓመት በላይና በታች ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ታራሚዎችን በሐሰተኛ ሰነድ ከእስር እንዲፈቱ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ሦስት የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎችና አምስት ግብረ አብሮቻቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
የማረሚያ ቤቱ ሹሞች ኦፊሰር ገብረ መድህን አረጋ ደስታ፣ ረዳት ኦፊሰር ኢሳያስ ከበደ ገብረ ጻድቅና ዋርደር ኢብራሂም መሐመድ ሲሆኑ፣ ከውጭ ሆነው ድርጊቱን በማቀነባበር የተጠረጠሩት ደግሞ ሰለሞን ገለታ፣ ብሩክ ኃይሌ፣ ሳባ ገብረ ሚካኤል፣ ናታን ዘለዓለምና ቴዎድሮስ ግደይ የሚባሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
ሦስቱ የማረሚያ ቤቱ ተጠርጣሪ ሹሞች የእስረኞች አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሲሆኑ፣ በሐሰት የተዘጋጀና ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ የእስረኛ መፍቻ የሚመስል ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም፣ 11 ታራሚዎችን ከ40 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር በመቀበል ከእስር እንደፈቷቸው ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡
 ሰለሞን ገለታ፣ ብሩክ ኃይሌና ናታን ዘለዓለም የተባሉት ተጠርጣሪዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት ቅጣት ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤት እንደቆዩና ጊዜያቸውን ጨርሰው የወጡ መሆናቸውን የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡
ሰለሞን ገለታ፣ ብሩክ ኃይሌ፣ ናታን ዘለዓለምና ቴዎድሮስ ግደይ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተዘጋጀ የሚመስል የእስረኛ መፈቻ ቅጽ በማዘጋጀት ሳባ ገብረ ሚካኤል ለተባለችው ተጠርጣሪ በመስጠት በኮምፒዩተር ካሠሩ በኋላ፣ አመሳስለው ያስቀረፁትን ማሕተምና ፊርማ በማተም፣ ለማረሚያ ቤቱ ሹሞች እንደሚሰጡ የኮሚሽኑ መርማሪ ገልጿል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ትዕዛዝና የእስር መፍቻው ሐሰተኛ ሰነድ የሚዘጋጀው ከአምስት ዓመት በታች ለተፈረደባቸው በ300 ሺሕ ብር፣ ከአምስት ዓመት በላይ ለተፈረደባቸው በ500 ሺሕ ብር እንደነበርና በቁጥጥር ሥር እስከዋሉበት ጊዜ ድረስ ከ11 በላይ ፍርደኞችን እንዲፈቱ ማድረጋቸውን መርማሪው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
ሐሰተኛ ሰነዶቹን፣ ማሕተምና ቲተር በመያዝ ለፎረንሲክ ምርመራ መላኩን በመግለጽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን ዋስትና ተቃውሟል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዳ የሚያሰባስበው መረጃ እንዳለው በመግለጽ፣ በዋስ ቢለቀቁ ማስረጃ ያሸሻሉ የሚል ሥጋት አለኝ ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ጊዜ ቀጠሮውን ፈቅዷል፡፡
ሌላው በተለይ ፍርደኞችን በሕገወጥ መንገድ ከማስለቀቅ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ዳኞችና ፌዴራል ፖሊስ በጋራ ለመምከርና ለመወያየት ታኅሳስ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ስብሰባ መቀመጣቸው ተጠቁሟል፡፡

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስወጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ የለም ተባለ

  በደቡብ ሱዳን የተነሳውን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ በአገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የደህንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ ቢሆንም መንግስት እስካሁን  እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑ ታወቀ።

የኢሳት የጁባ ወኪል እንደገለጹት አብዛኛው አገሮች ዜጎቻቻውን እያወጡ ነው ። ኬንያና ኡጋንዳ አውቶቡሶችን በመላክ ፣ አሜሪካና እንግሊዝ ደግሞ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን በመላክ ዜጎቻቻውን እያወጡ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን ጁባ ማረፉን ተከትሎ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ አውሮፕላኑ ግን ቻይናዎችን ብቻ ጭኖ መመለሱ ታውቋል።  ኢሳት ከአየር መንገዱ ለማረጋገጥ እንደቻለው የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻርተር አውሮፕላን በመከራየት  በነዳጅ ማውጣት ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎቹን ወስዷል።
እንዲሁም   ለሽምግልና ጁባ የሄዱትን የኢትዮጵያን ባለስልጣናት በማሳፈር ጁባ ያረፈ አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን፣ ባለስልጣኖችን ካወረደ በሁዋላ ትኬት ቆርጠው ለመውጣት ይጠባበቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ሳይጭን ባዶውን ተመልሷል። ኢትዮጵያውያኑ የኬንያንና የኡጋንዳን አየር መንገዶችን ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ አየር መንገዶቹ ከፍተኛ ዋጋ በመጠየቃቸው ትኬቶችን ለመግዛት አልቻሉም።
ኢሳት ለማረጋገጥ ባይችልም ሶሰት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መደፈራቸውን የሚያመለክት ዜና ደርሶታል። አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም ንብረታቸውን ተዘርፈው በጁባ መንገዶች ላይ ያለ ደጋፊ ሲዞሩ እንደሚታይ ወኪላችን ገልጿል።
የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ  እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ላለፉት ሁለት ቀናት በጁባ ተገኝተው ሁለቱን ሀይሎች ለመሸምገል ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቋል። ደ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ሁለቱንም ሀይሎች ለማቀራረብ ከፕሬዚዳንቱ ጥሩ ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ቦር የተባለው አካባቢ በአማጽያን እጅ የወደቀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ድንበር በሆነው አኮቦ በትናንትናው እለት ጦርነት ተከፍቷል። ዛሬ ደግሞ ማላኪ፣ ዋው እና ባንቲዩ በተባሉት አካባቢዎች ጦርነት ተከፍቷል። ባንቱዊ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት የሚገኝበት ሲሆን፣ በርከታ የዲንቃ ተወላጆች በጽህፈት ቤቱ ግቢ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል። በጁባ የኑዌር ተወላጆች ከዲንቃ ጎሳዎች ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ብለው በተመድ ጽ/ቤት ውስጥ ሲጠለሉ፣ በቤንቲዩ ደግሞ በተቃራኒው ዲንቃዎች ተጠልለዋል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ አዲሲቷ አገር ወደ እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል። እስካሁን ባለው አሀዝ ከ500 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል።

ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ጻፉ

December 22, 2013

ክንፉ አሰፋ
ፀሃይ አሳታሚ ድርጅት በታኅሣሥ 16, 2006 ዓ/ም (Dec. 25, 2013)  የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን የሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስን ‘እኛና አብዮቱ’ የሚል መጽሃፍ  ለገበያ እንደሚያበቃ አስታወቀ። ሻምበል ፍቅረሥላሴ እንደ ደርግ አባልነታቸው በጋራ ያመኑበትን፣ የተማከሩትን፣ የወሰኑትን፣ የሰሩትን፣ የገጠማቸውንና በቅርብ በዓይን ምስክርነት ያዩትን ተንትነው በ‘እኛና አብዮቱ’ ያስነብቡናል። የራሳቸውን ዕይታ ያካፍሉናል።New book by Fkreselase Wegderes
ልጅ ሆነን አንድ አባባል እሰማ ነበር።”አበላል እንደ ደርግ አባል። አለባበስ እንደ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ!” – የሚል። በተለይ በኔ ትውልድ ያለን ሰዎች፣ ከዚህ ውጭ ስለኝህ ሰው የምናውቀው ብዙም ነገር አልነበረም። ግና እኝህ ሰው በልባቸው መክሊት ለአመታት የቋጠሩትን መረጃ ጀባ ሲሉን፤”… አጻጻፍም እንደ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ” የሚያሰኝ ሆኖ አገኘሁት።
ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ለአስራ አምስት ዓመታት አብዮቱን ሲመሩ ቆይተው ወደ መጨረሻው ከሥልጣን በጡረታ ስም እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። ደርግን በጣለው በወያኔ መንግሥትም ለ፳ ዓመታት ታስረው፣ የሞት ፍርድ የተበየነባቸውና በመጨረሻ ፍርዱ ወደ ዕድሜ ልክ ተዛውሮላቸው ከእሥር ቤት በአመክሮ የወጡ ግለሰብ ናቸው።
ጸሃፊው በድራማ መልክ በመጽሃፋቸው ካሰፈሩዋቸው እውነታዎችና ግለ-ሂሶች ውስጥ አንዳንዶቹን ለአንባቢያን ማካፈሉ አይከፋም።  ደርጎች መፈንቅለ መንግስት አድርገው ሲያበቁ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘንድ ቀርበው ከንጉሱ የገጠማቸውን አስገራሚ ምላሽ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ  በመጽሃፋቸው እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል።
የፖለቲካ እሥረኞች በሙሉ እንዲፊቱ የሚለው ጥያቄ እንደተነበበ ንጉሡ ጣልቃ ገብተው “ለመሆኑየፖለቲካ እሥረኞቹ እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ አቀረቡ። “በእርግጥ የምናውቃቸው የፖለቲካእሥረኞች ባይኖሩም ማንኛውም የፖለቲካ እሥረኛ እንዲፈታ ነው የምንጠይቀው” አሉ ሻለቃ ተስፋዬገብረኪዳን። ንጉሡ ራሳቸውን ነቅነቅ አድርገው ጽሑፉን የሚያነበውን የደርግ አባል እየተመለከቱአልገባችሁም!” ብለው ዝም አሉ። በእርግጥም አልገባንም። ተማሪዎችና የተለየ ዓላማ የነበራቸውየተማሩ ሰዎች የሰነዘሩትን መፈክር ብቻ ነበር ይዘን ንጉሡ ፊት የቀረብነው። በፖለቲካ እሥረኝነትስም በከፍተኛ ደረጃ ለጣሊያን ወራሪ መንግሥት በባንዳነት አድረው አገራችንን የወጉ፣ ለቅኝተገዥነትም የዳረጉትን እንደ ኃይለሥላሴ ጉግሳ ያሉ ወንጀለኞች የፖለቲካ እሥረኞች ተብለው ከግዞትናከእሥር ቤት አስወጥተን እንደ ጀግና ራሳቸውን እንዲቆጥሩ አደረግናቸው።
የነ ጄነራል ተፈሪ በንቲ ጉዳይን አስመልክቶ የሰፈረው ታሪክ ደግሞ እንዲህ ይነበባል።
“በሊቀመንበርነት ስብሰባውን የሚመሩት ጄነራል ተፈሪ ‘የቋሚ ኮሚቴው’በዛሬው ቀን የሚወያይበትንጉዳይ አስመልክቶ የመቶ አለቃ ዓለማየሁ የደርጉ ዋና ፀሐፊ ይገልጽልናል’ ብለው ስብሰባውመጀመሩን ካበሰሩ በኋላ ዓለማየሁ በአጀንዳው ላይ አጭር ገለጣ ማድረግ ሲጀምር ስልክ ተደወለ።ስልኩ /ኮሎኔል መንግሥቱ አጠገብ ስለነበር ወዲያው ቅጭል እንዳለ መነጋገሪያውን በማንሳት ሃሎአሉ። ከሌላው ጫፍ ማን እንደደወለ አላወቀንም። በኋላ እንደታወቀው /ኮሎኔል ዳንኤል ነበርየደወለው። ምን እንደተነጋገሩ አልተሰማም። /ኮሎኔል መንግሥቱ ብቻ “እሺ እሺ” ብለው ስልኩንዘጉት። ስልኩን እንደዘጉ “ይቅርታ ስልኩ የተደወለው ከጎንደር ነው። ጎንደር ውስጥ ችግር አለ።እናንተ ቀጥሉ” ብለው ከጀርባቸው ባለው በር በኩል ውልቅ አሉ። በዚህን ጊዜ ዓለማየሁና ሞገስጥርጣሬ የገባቸው መሰለ።  ዓለማየሁ ንግግሩን አቋርጦ በመስኮት በኩል ውጭ ውጭዉን መመልከትጀመረ። ዓይኖቹ አላርፍ አሉ። ግራና ቀኝ ይመለከታል። አጠገቡ ያሉትን ሰዎች ሁሉ በጥርጣሬተመለከተ። ሻምበል ሞገስም በር በሩን ይመለከታል። ከአሁን አሁን አንድ ችግር ይከሰታል የሚልፍርሃት ያደረበት ይመስላል። ሁሉም የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች ፈርተዋል። እንደፈሩት አልቀረም/ኮሎኔል መንግሥቱ ከወጡ ሁለት ደቂቃ እንኳን አልሞላም ከበስተጀርባ ባለው ኮሪደር የወታደሮችንእርምጃ ሰማን። ወታደሮች ሲንቀሳቀሱ በፊት ለፊታችን ባሉት መስኮቶች በኩል ተመለከትን። በዚህንጊዜ ፍስሐ ደስታ “ተከብበናል” አለ። ወዲያው ሁለቱም በሮች በኃይል ተበረገዱ። ሁላችንም ደነገጥን፣ቀልባችን ተገፈፈ፣ እጢአችንም የወደቀ መሰለን። ድርቅ ብለን በተቀመጥንበት ቀረን።…
ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ሰለ ልጅ ሚካኤልን አስተዋይነት ሲያስታውሱ እንዲህ የሚል ግለሂስም ያስነብቡናል።
እኛ በችኮላ ውሳኔ መስጠታችን፣ ሕዝቡን በደንብ አለማወቃችን፣ ሰፊ የሕዝብ አመራር ልምድማጣታችን፣ የአገርና የውጭውን ፖለቲካ ውስብሰባዊ ግንኙነት አለመገንዘባችን፣ የመንግሥትን አሠራርደንብና ሥርዓት አለመረዳታችን፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥመርታዊ ግንኙነትን መመልከት አለመቻላችን፣የተለያየ ገንቢም ሆነ አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸው ኃይሎች ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብ ያለማጤናችን፣በየዋህነትና በቅንነት ብቻ እንደምንሠራ በመገንዘባቸው ሊሆን ይችላል ልጅ ሚካኤል ከእኛ ጋር መቆየትየሚችሉት ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሚሆን የጠቆሙት…
በወቅቱ ስለ ህዝቡ የእርስ በርስ መጨካከንና መወነጃጀል ባሰፈሩት ክፍል ውስጥ እንዲህ የሚል ታሪክ እናገኛለን።
Former Ethiopian Official Fkreselasie Wegderes
..የሥራ ዕድገት የተከለከለ፣ በሌብነትም ሆነ በስካር ወይምበሌላ ጥፋት የተቀጣ፣ በግል ጉዳይም ሆነ በመንግሥት ሥራከአለቃው ጋር የተጣላ፣ በአጋጣሚው ተጠቅሞ አዲስ ሹመትወይንም ዕድገት ለማግኘት የሚፈልግ ሁሉ ጠቋሚ፣ ወንጃይ፣ከሳሽ፣ ተበዳይ ነው።
የተወሰነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ሌላውን ለመጉዳት ብለውኢትዮጵያ ትቅደምን ይቃወማል፣ ከታሠሩት ባለሥልጣናትወይም ሚኒስትሮች የቅርብ ዝምድና አለው። ስለሆነም ሥራይበድላል፣ ሠራተኛውን ያጉላላል፣ ውሳኔ አይሰጥም” በማለትአለቆቻቸውን የሚከሱ፣ የሚወነጅሉ በርካታ ናቸው። ለደርግአባላት ቤታቸው ድረስ በመሄድ በማስረጃ የተደገፈ ቢሆንምባይሆንም ተቆርቋሪ በመምሰል የክስ ማመልከቻ የሚያቀርቡምነበሩ። እንታሠራለን ብለው በፍርሃት የተደበቁ ባለሥልጣናትንየቅርብ ዘመዶቻቸው ወይም አሽከሮቻቸው ወይምጎረቤቶቻቸው ደርግ ጽሕፈት ቤት ድረስ በመምጣትያጋልጧቸው ነበር። የመሥሪያ ቤቶችን ሰነዶች ፎቶ ኮፒ በማድረግ ወይም ሰነዱን እንዳለ ከፋይሉአውጥተው በማቅረብ “በመንግሥት ንብረት፣ ሀብት ወይንም ገንዘብ ላይ አላግባብ ተወስኗል” ብለውጥቆማና መረጃ የሚያቀርቡም ነበሩ። ሠራተኞች አሠሪዎቻቸውን ይከሳሉ፣ ይወነጅላሉ። ገበሬዎችለዘመናት በደል አደረሱብን የሚሏቸውን የአካባቢ ባለሥልጣናት ይወነጅላሉ። ውንጀላው በርካታነው።
አሽከሮች፣ ዘበኞች፣ ገረዶች… መረጃ ይሰጣሉ፣ ይጠቁማሉ። የተደበቀ የጦር መሣሪያ፣ የተደበቀ ገንዘብ፣ወደሌላ ቦታ የተወሰደ ወይም የሸሸ ሀብት እንዳለም የሚጠቁሙን እነሱ ናቸው። በአንድ ቦታ በርከትያሉ ሰዎች ተሰብስበው ምሽት ከአሳላፉ “ሲያድሙ ነበር” ብለው ከነስም ዝርዝራቸው መረጃውን ደርግጽሕፈት ቤት ድረስ ያመጣሉ። “እኛ እስከዛሬ የበይ ተመልካች ነበርን ዛሬ ዕድሜ ለእናንተ እንጀራሊወጣልን ነውከእናንተ ጎን ተሰልፈን አቆርቋዦቹን እንታገላለንበማንኛውም ጊዜ ትዕዛዝ ብትሰጡንለመፈጸም ዝግጁ ነን!” እያሉ ታማኝነታቸውንና ተባባሪነታቸውን የሚገልጡም ብዙዎች ነበሩ። በጣምየሚያስደንቀው አባቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ እህቶቻቸውን፣ ባሎቻቸውን፣ሚስቶቻቸውን በመክሰስ፣ በመወንጀል፣ በማጋለጥ፣ በመጠቆም ብሎም በማሳሰር ጉዳት ያደረሱበርካቶች መሆናቸው ነው።
እንግዲህ ስለ አዲሱ ‘እኛና አብዮቱ’ መጽሃፍ ይህንን ካልኩ ቀሪውን ለአንባቢ መተው ይበጃል። ሁሉም ሰው መጽሃፉን አንብቦ የራሱን ፍርድ ይስጥ።
ህይወት በሩጫ ትመሰላለች። የተፈጥሮ ህግጋት ነውና የሰው ልጅ እስትንፋሱ እስኪቋረጥ ይሮጣል።  ከዚያም ሩጫውን ይጨርሳል። ሩጫውን ሳይጨርስ በልቡ ቋጥኝ የያዘውን እምቅ ቋጠሮ የሚተነፍስ ደግሞ እድለኛ ነው።  በአንጻሩ ደግሞ በአእምሮውየቋጠረውን የእውቀት ምስጢር ሳያካፍል የሚያልፍ ሁሉ ያሳዝናል። ያለውን የወረወረ ንፉግ አይደለምና መንቀፍም ካለብን የሚወረውረውን ሳይሆን የማይወረውረውን ነው። መተቸት ካለብነም ሃሳቡን እንጂ ግለሰቡን ባይሆን ይመረጣል። በሃሳብ ላይ መወያየትና መተሻሸት ደግሞ አዋቂነት ነው።
በመጨረሻም የመጽሃፉ አርታኢ ኤልያስ ወንድሙ በመግቢያው ላይ ባሰፈረው መልእክት ጽሁፌን ልቋጭ።
የተማረ፣ ያወቀና ያደገ ትውልድና ዜጋ ምልክቱ የተጻፈን ማንበቡ፣ ያነበበውን ማብላላቱና ካነበበው ውስጥ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየቱ ሲሆን፤ እራሱም አስተውሎና አገናዝቦ መጻፉ ደግሞ መማሩን ብቻ ሳይሆን መመራመሩንና ማወቁን የሚያሳይ ታላቅ ተግባር ነው። ለዚህም ደግሞ ግላዊ ነጻነት ያስፈልገዋልና ጫንቃው ላይ ያሉትን ግላዊና ታሪካዊ ቀንበሮች የሰበረ ነጻ ሰው መሆን ይጠበቅበታል። ትምህርትና ዕውቀት አስተዋይነትንና ጥልቀትን ከራስ በላይ ለትውልድ አሳቢነትን የሚያመለክት ታላቅ ኃላፊነት ነው። ለዚህም እንደ ትናንቱ ‘የተማረ ይግደለን’ ሳይሆን፤ የተማረ ያስተምረን፣ ያስተዳድረን ብሎም ይምራን በምንልበት ዘመን ከምናነብበው ውስጥ ያልተስማማንበትን በጨዋነት የመቃወም፣ የፈቀድነውን እንደ ስሜታችን የመደገፍና ተሳሳተ የምንለውን ለእርማት መጠቆም ግላዊ መብታችን ነው።…
* ፀሃይ አሳታሚ ድርጅት ከዚህ በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን፣ የቀድሞውን የህወሃት መሪ ዶ/ር አረጋዊ በርሄን፣ የቀድሞውን የኢህአፓን አመራር አባል የዶ/ር መላኩ ገኝን፣ የቀድሞው ሚንስትር  የአቶ ተካልኝ ገዳሙን መጽሃፍትና  ከስልሳ በላይ የሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክና ጥናት ላይ ያተኮሩ መጽሃፍትን ማሳታሙ ይታወሳል። ‘እኛና አብዮቱ’ የሚለው ይህ አዲስ መጽሃፍ በwww.tsehaipublishers.com ድረገጽና በቀርቡ በየሱቁ አንደሚገኝ ከሎስ አንጀነሰ የደረሰን ዘገባ  አስታውቋል። ሁላችንም ገዘተን እናንብብ።
መጽሃፉን አንብቤ እንደጨረስኩ በሂሳዊ ግምገማ እመለስበታለሁ።

Sunday, December 22, 2013

ንቃ የሀገሬ ህዝብ

                                                                                                                                                                                    Dec 22, 2013
        ከአምሳል ጊዮን  
        aberhanou@gmail.com
     ያኔ በነዚያኛው  ዘመን የሀገሬ  ህዝብ የሀገር ያለህ የመንግስት ያለህ ብሎ ህዝቡን መንግስቱን ሲማፅን እና ሲጮህ  አንገቱን ያላዞረ ህዝብም  ሆነ መንግስት ያለ አይመስለኝም ።  ያኔ ነው አሉ በሰንደቃላማው ወድቃ በተነሳችው ሲባል  ወይ ፍንክች ነበር ፣ ግና ዛሬ ዛሬ የሰንደቃላማው እና የሀገር  ፍቅር እንዳይገባን ሆነን ተወልደን፣ ያደግን የትውልድ ጭንጋፍ ሆነን ፣የትውልድ የኮመጠጠ ቡኮ ሆነን ሲጋገር የማየርባን ልምሻ ሆነን ፣የዘመኑ የመጨረሻ  የሀገር ውራ ማፈርያ ሆነን የትውልድ ፈሪ ሆነን እስከ መቼ  ነው??? 
      ነገሩ እንዲ ነው ሀገር እንመራለን ባዮቹ ሀገሬውን ፈተሹት የፍርሀትን  መንፈስ ብንረጭበት ሲሉ ተማከሩ አሉ  ከዛም  በፓርላማ ላይ ምላስ  እንቆርጣለን ፣ጣት እንቆርጣለን ምንትስ ምንትስ  አሉ ። በመቀጠል ህዝብ በሌላ ፖለትካ  ሊደራጅ  ቢፈልግ ቀደም ያሉትን የተቁሃሚ ፖለትካ  እስረኞች  የዕድሜ  ልክ እስራት፣ ንብርት መውረስ አና  የሞት  ፍርድ  በመፈርድ  በህብረተሰቡ  ላይ  ፋርሃት (ሜንታል ቶርች ) አስቀድሞ እንደማስጠቀቅ አድርጎ ፍርሃት ለቀቁበት።
      ከዚህም  በተጨማሪ  ቀን እና  ማታ  በሚያደነቁረን የቴሌቪዥን ጣቤያቸው ላይ ሲዳከር  የዋልወና ጎኑን ለማሳረፍ እፎይ   አንዳይል በሰንበት  የመከላከያ በሚለው የቴሌቪዥን  ስርጭት ላይ ከዚህ በፊት ደርግ ይጠቀምበት የነበረውን የጦር አውሮፕላን  የታንክና የመሳሪያ ዓይነቶች የጦሩን ብዛት  አያሳዩን ልቡ እስጠኪፋ ያደክሙታል።
አሁንም እነዚህ  መንግስት ነን ባዮቹ  ተማከሩ አሉ፣ እንዴት ነው የህዝቡ ልብ  ውስጥ ምን ተገኘ ? በፍርሃት ተሸበበ ወይ ? የለም ገና  ነው ተባባሉ።  በ1997 ምርጫ የነበረውን የህዝቡን ወኔና የልብልብ  ስሜት ሰልቦ ፣ ፍርሀት በልቡ ወስጥ በማስፈር በየትምህርት ቤቱ ሳይቀር ተማሪው በጠመንጃ አፈሙዝ ነው ምንማረው እስኪል ድረስ ግራ አጋቡት፣ ለአዲስ  አበባ ህዝብ በነብስወከፍ የፌደራል ፖሊስ ዘሩበት ሌላው ቀርቶ ከፍ ባል ድምፅ ካስነጠስክ ያቀምስሃል! ለምን?  ትእዛዝ ነዋ። ጉድ  በይ ሀገሬ ኢትዮጵያ  አጆችዋን ወደ ጌታ ትዘረጋለች የሚለውን ቀየረው ወደመንግስት ለያስብሉን???  ዛሬ በሀገሬ  ህዘብ ልብ ውስጥ  ያለውን ማን ያውቃል ??? ንቃ የሀገሬ ሰው አምቢ በል!!

                                     * እስመ አልቦ ለነገረ ወይስሐኖ ለ እግዚአብሄር *    
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!                                                        

Tuesday, December 17, 2013

የኢህአዴግ አመራር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሐኖምን ገሰጸ

የወደፊቱ ጠ/ሚንስትር ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ የሚነገርላቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ ግሳጼው የቀረበባቸው ” በሳውድ አረቢያ ላይ ተመጣጣኝ የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

ኢህአዴግ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር አስቸኳይ ስብሰባ የጠራ ሲሆን ዶ/ር ቴዎድሮስም ” ያለግንባሩ ውሳኔ እንዲህ አይነት ጠንካራ አስተያየት ለምን እንደሰጡ እንዲያብራሩ ተጠይቀዋል። “ዶ/ር ቴዎድሮስ በቂ ማብራሪያ ለመስጠት ባለመቻላቸው ግለ-ሂሳቸውን እንዲያወርዱ ተጠይቀዋል። ከፓርቲው ይልቅ የግል ዝናቸውን እየገነቡ ነው በሚልም ተገምግመዋል።
የሳውድ አረቢያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ቴዎድሮስ አድሀኖም በሰጡት መግለጫ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው ለ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ደብዳቤ ማስገባቱን ተከትሎ ነው ግምገማው የተካሄደው።
በሳውድ አረቢያ መንግስት ደብዳቤ የተደናገጡት አቶ ሀይለማርያም ወዲያውኑ በቴሌቪዥን ቀርበው ከሳውድ አረቢያ ጋር የቆየ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መኖሩን፣ ይህን ግንኙነት አሁን በተፈጠረው ችግር እንደማይለወጥና ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አቶ ሀይለማርያም የተናገሩትን ተከትሎ በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሙሀመድ ካቢራ የኢትዮጵያ መንግስት 361 የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠታቸውን፣ ሳውዲ በኢትዮጵያ ታላቁ ኢንቨስተር መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጥሩ ስሜት ላይ እንዳልሆኑ ምንጮች ገልጸዋል። ሚኒሰትሩ በፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት መልእክት ጠ/ሚንስትሩን በማጀብ በማንዴላ ቀብር ላይ ሊገኙ ያልቻሉት በጤና ችግር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ኢህአዴግ በሳውድ አረቢያ ላይ ያሳየው የተለሳለሰ አቋም እየተተቸ ነው። ዶ/ር መረራ ጉዲና ሰሞኑን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መንግስት በሳውዲ አረቢያ ላይ የያዘውን ፖሊሲ መተቸታቸው ይታወቃል።

በጅጅጋ የተካሄደው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ማለፉ በክልሉ ሰላም አለመኖሩን ያመለክታል ሲሉ አንድ ታዛቢ ተናገሩ

በመንግስት የሀላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ አንድ ስማቸው እንዳይገለጸት የፈለጉ ሰው ለኢሳት እንደተናገሩት በክልሉ በቆዩባቸው ቀናት የታዘቡት ነገር ቢኖር በክልሉ የሰላም እጦት ዋናው ችግር መሆኑን ነው።

ምንም እንኳ መንግስት ያለምንም ችግር በአሉ መጠናቀቁን ቢገልጽም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ እንደነበር ሃላፊው ይናገራሉ። በከተማዋ ዳርቻዎች ታንኮች፣ ከባድ መሳሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ፣ ልዩ ኮማንዶችና እና እስካፍንጫቸው የታጠቁ እግረኛ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት የ24 ሰአታት ጥበቃ ሲያደርጉ ፣ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ደግሞ የአየር ላይ ቅኝት ያደርጉ ነበር። ጥበቃው እስከ አዋሳኝ ወረዳዎች ዘልቆ እንደነበር የገለጹት ሀላፊው፣ መኪኖች በበአሉ ዝግጅት ወቅት እንዳይንቀሳቀሱ ታግተው እንደነበር ገልጸዋል።  የበአሉ አከባበር በስታዲየሙ ውስጥ ብቻ ይካሄድ እንደነበር የገለጹት እኝሁ ሀላፊ፣ ሌላው የጅጅጋ ክፍል የሞት ከተማ ይመስል ነበር ሲሉ አክለዋል። በጦርነት ቀጠና ውስጥ እንኳ ቢሆን፣ በዚህ አይነት ወታደራዊ ጥበቃ ማንኛውንም አይነት በአል ማክበር እንደሚቻል የገለጹት ባለስልጣኑ፣ አካባቢውን የጎበኙ የውጭ አገር ዜጎችና ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው   ሰላም በኢህአዴግ እይታ ምን ማለት እንደሆነ በቂ ግንዛቤ ወስደዋል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በበአሉ ላይ ለመሳተፍ እንግድነት ተጠርተው ከሄዱት እንግዶች መካከል የኬንያውና የሩዋንዳው አፈ-ጉባኤዎች ተቀባይ አጥተው ሲቸገሩ እንደነበር እኝሁ ሀላፊ ተናግረዋል። የኬንያው አፈጉባኤ የተጋበዙት በአባ ዱላ ገመዳ ሲሆን፣ የሩዋንዳው ደግሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉበኤ ካሳ ተክለብርሀን ነበር። ይሁን እንጅ ሁለቱ ልኡካን ጅጅጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቶ አባ ዱላም ሆኑ አቶ ካሳ ተክለብርሀን አልተቀበሉዋቸውም፣ እነሱን የሚቀበል ሌላ ሰውም አላዘጋጁም። ልኡካኑ ግራ ተጋብተው በጅጅጋ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከቆዩ በሁዋላ፣ የጅጅጋ ፖሊስ በአንድ አሮጌ ፒክ አፕ የፖሊስ መኪና አሳፍሮ ጅጅጋ ሆቴል እንዲያርፉ አድርጓል። ልኡካኑ እንዲያርፉ የተደረገበት ሆቴል ደረጃውን የማይመጥን ነበር ሲሉ ባለስልጣኑ ገልጸዋል። የልኡካን ቡድኑ በመጡበት ወቅት አባ ዱላና አቶ ካሳ ተክለብርሀን በተዘጋጀላቸው የእንግዳ ማረፊያ ክፍል ውስጥ በመዝናናት ላይ ነበሩ።
ልኡካኑ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሄደው ባለመቀበላቸው ማዘናቸው ሳያንስ በተያዘላቸው ሆቴል እጅግ ተበሳጭተው ነበር።  የሶማሊ ክልል አስተዳደር የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ለውጭ አገር እንግዶች ተገቢውን ክብር ባለመስጠታቸው ማዘኑን መግለጹም ታውቋል።

የማለዳ ወግ … ስደተኛው ዘፋኝ በሳውዲ በርሃ …(ከጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ)

የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ … እንደጨው ተበትነናልና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወገኖቸን በየሔድኩበት ከተማ ፣ እግር በጣለኝ የሳውዲ የቀለጡ በርሃዎች ወንድም እህቶቸን አገኛለሁ ። ላፍታም ቢሆን ጊዜ ሰጥቸ እየኑሩት ስላለው ኑሮ ፣ እየገፉት ስላለው ክፉም ደግ ተሞክሮ እጠይቃቸዋለሁ አንድም ሳይደብቁ የሆድ የሆዳቸውን ያጫውቱኛል …

እለተ ቅዳሜ በማለዳው ያቀናሁት በያንቦና በጅዳ መካከል በምትገኝ የዋዲ በርሃ ዙሪያ ነበር ። አየሩ ተቀያይሯል ፣ ከዚህ ቀደም ወደዚህ ቦታ ሳመራ እንደ እሳት ነበልባል የሚጋረፈው ሙቀት ዛሬ የለም ። ለስራ ወዳቀናሁበት በድቅድቁ በርሃ ላይ በተሰራው የድንጋይ መከስከሻ ፋብሪካ እንደደረስኩ አንድ መልከ መልካም ወንድም የግቢውን በር ከፍቶልኝ ለመግባት ወዴት መሄድ እንደምፈልግ የጠየቀኝ ወጣት ሃበሻ ለመሆኑ ቅንጣት ያህል አልተጠራጠርኩምና የሚጠይቀኝን ትቸ እኔው ጠየቅኩት “ሃበሻ ነህ! ” ነበር ያልኩ ። ይህን ስጠይቀው እንደ መሽኮርመም እና እንደመሳቅ እያለ “አዎ ሃበሻ ነኝ ፣ ኢትዮጵያዊ! ” ሲል መለሰልኝ! ብዙ ሃበሾች አላችሁ? ስል ጥያቄየን ቀጠልኩ “አዎ አምስት ሃበሾች አለን! ” አለኝ ፈገግ እያለ … በአሻጋሪ መምጣቴን የሚጠብቅ የፋብሪካው ሃላፊ “አስገባው ፣ አስገባው! ” ሲል ፍልቅልቁ ወንድም ተደናግጦ በወራጅ ብረት እንደነገሩ የተዘጋውን የግቢ ብረት አጥር ከፍቶልን እኔና የስራ ባልደረባ ረዳቴ የፊሊፒን ዜጋው ግላዲ ወደ ግቢው ስንገባ በመስኮት በኩል አንገቴን ወጣ አድርጌ ስራየን ከዋውኘ እንደማገኘው ቃል ገብቸለት ወደ ውስጥ ገባሁ …Saudi Arabia, Nebyu Sirak
ሱዳኑ የፋብሪካ ሃላፊ ከድንጋዩ መፍጫ የቅርብ ርቀት ካለው ጋራጅ አጠገብ ከተሰራች ባለሁለትና ሶስት ዛኒጋባ ቆርቆሮ ቤት ወጥቶ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጥቶ ተቀበለን ። ድንጋዩን እየከሰከሰ ጠጠር የሚያደርገው ፋብሪካ ነጭ አመድ ወደ ሰማይ እየተፋ የጓራል …ዲንጋው እየተፈጨ ጠጠር እየተሰራ መሆኑ ነው! የመንገድ መደልደያ ፣ የምንገድ መጥረጊያ እና የመንገድ ማለስለሻ ዳምጤ ከባባድ የኮንስትራክሽን መኪኖችን ጨምሮ ጥገና የሚያስፈልጋቸው መኪኖች ጋራጁን አጨናንቀውታል … ከጋራጁ ጀርባ ደግሞ እኛ መመርመር ያከብን የተሽከርካሪ ጎማ መአት ተከምሯል። …አምስት የተባሉትን ሃበሾች አግኝቸ እስካዎጋቸው ቋምጫለሁ …የፊት የፊቱን እያስቀረብኩ ለፊሊፒኑ አጋሬ ምን መስራት እንዳለበት በማሳወቅ ስራውን አጣድፊ ግን በአግባቡ መርምሬ እንደጨረስኩት ሌሎች ሁለት ሃበሾች ሃበሻ ወንድማቸው መምጣቴን ሰምተው ኖሮ በፈገግታ እየተፍለቀለቁ መጥተው ሰላምታ ተለዋዎጥን …
ሃበሻ ዝር በማይልበት በርሃ ያገኙኝን ወንድም እነርሱም ሊያስተናግዱ ሊያጫውቱኝ እንደቋመጡ አልጠፋኝም … በተንቀሳቃሽ ኮንቴነር በፋይዚት ግሩም ሆና የተሰራቸው ማረፊያ ቤት ከጋራጁ የቅርብ ርቀር ትገኛለች ። አቧራ የጎረሰውን እጀን ሳልተጠብ በበርሃው ወዳገኘኋቸው ወንድሞች ማረፊያ ቤት አመራሁ … ረመድ ረመድ እያልኩ ከመድረሴ ወንድሞቸ በደስታ እየተፍለቀለቁ ግማሽ መንገድ ላይ ተቀበሉኝ ! ጠባቧ ቤት ማረፊያ ቤት ብቻ እንዳልሆነች ከበር የተደረደሩትን ጫማዎች ስመለከት ገባኝና ጫማየን አውልቄ “ቤት ለእንቦሳ! ” ብየ ዘው ብየ ገባሁ… ቤቷ ጽድት ያለች ናት … ሶስት አልጋዎች በሶስቱ የቤቱ ማዕዘኖች ጥግ ይዘው ተዘርግተዋል ። የተቀበሉኝ ወንድሞቸ ሶስት ሲሆኑ ዘግየት ብሎ ሌላ ወንድም ገባ … አምስተኛው ወንድም የት እንዳለ ስጠይቅ እሱ ስራ ላይ እንደሆነ ገለጹልኝ። ሁላችንም የምናወራው ከአልጋዎች ላይ ተቀምጠን ነው ። እንደገባኝ ከሆነ አልጋዎች ይተኛባቸዋል ብቻ ሳይሆን በመቀመጫነት ያገለግላሉ! … ጫዎታችን ከመጀመራችን በፊት እጀን ለመታጠብ ውሃ ቢጤ ስጠይቅ ድምጹ ጎርነን ያለው “ሸዋንግዛው እባላለሁ!” ብሎ የተዋወቀኝ ወንድም በእጅ ከምትያዝ ማቀዝቀዣ ውሃ ይዞ ወደ ” በር ላይ ላስታጥብህ! ” ብሎ ግማሽ ጎኔን ከበሩበወጣ አድርጌ እንደነገሩ ጣቶችን ውሃ አስነካሁ ብል ይሻላል ፣ ብቻ ታጠብኩ ።
ወጋችን የጀመርነው በድፍኑ አበሻ ሁኘ እንጅ ማንነቴን የተረዳ ሰው የለም! ብዙ የህይወት ልምዳቸውንና ስለስራቸው ስለተመለከቱት የቴክኒክ ስራየ ፣ ሱዳኑበሲጠራኝ ስለሰሙት የእንጀራ ስሜና ስለ አጠቃላይ የሳውዲ ህይወት እንዳንፈራራ ፣ እንዳንደባበቅ ፣ እንደ መተዋወቂያ አወራን … ጋዜጠኛ መሆኔን ትንፍሽ ሳልል “ራዲዮ ትሰማላችሁ ፣ ኢንተርኔት ፊስ ቡክ ትከታተላላችሁ? ” በማለት ደጋግሜ ጠየቅኳቸው! አዎንታቸወን ገለጹልኝ ። ስሜን የእኔ ነው ሳልል ታውቁታላችሁ? ስላቸው አዎንታቸውን በዝርዝር ገለጹልኝ! ስገባ በር የከፈተልኝ እያሱና የቀሩት ሁለት ያህሉ የፊስ ቡክ ጓደኛው እንደሆኑ በኩራት በመግለጽ በቅትቡ የለቀቃቸውን የራዲዮ መጠይቆች እያነሱ የሚያውቁትን ሰው ስም ስላነሳሁላቸው በደስታ ብዙ አወሩኝ! … እንዲህ ጥቂት ከቀጠልን በኋላ ግን እነርሱ እዚህ ስላደረሳቸው መንገድ መጠየቅ ጀመርኩ ! ሁሉም የሆነውን ሁሉ ሲያጫውቱኝ ጫፍጫፉን ያወጋኝ ታሪክ ሳበኝ! ” አበባ ተሸልሜ በጭብጨባ የተሸኘሁ ዘፋኝ ነበርኩ !” ያለኝ ድምጸ ጎርናናው የሸዋንግዛው ታሪክ ልቤን ነካው … ብዙም ሳልቆይ ግን የእውነተኛው አለም ማንነቴን ገላልጨ ሳጫውታቸው ነገሮት ተቀያየሩ! … በጣም ተገረሙ! ብዙ ተጫወትን … ለዛሬ እንዳላደክማችሁ በሚል በሳውዲ በርሃ ስላገኘሁት ወንድም ትኩረቴን ላድርግና ላጫውታችሁ …
ሸዋንግዛው እና ከቀሩት ጓደኞቹ ሃገር ቤት አይተዋወቁም ። ዳሩ ግን ድህነት ፣ የኑሮ ውድነት ፣ የማደግ የመመንደግ ፍላጎት በቁንጮዋ ነዳጅ አምራች ሀገር በሳውዲ አንድ በርሃ ሳውዲ በርሃ ላይ አገናኝቷቸዋል ! … ከሁሉም ወንድሞች ይልቅ ዘፋኙን ስደተኛ ሸዋንግዛውን እዚህ ያደረሰ መንገድ ለማወቅ ጓጉቻለሁ! እናም ላፍታ ከዘፋኙ ወንድም ጋር የሆድ የሆዳችን እድሉን አገኝንና ላፍታ አወጋን … ከሸዋንግዛው ንጉሱ ይባላል ፣ እድሜው በአርባወቹ ውስጥ እንጅ ከዚያ የማይዘል ዘፋኝ መሆኑን ሲያንጎራጉር ከተቀረጻቸው ድምጾች ብቻ ሳይሆነ የተለቀቀውን ነጠላ ዜማ ሰምቸ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም … “ዘመኑ የዘፋኝ ነው” በሚባልበት ዘመን ድምጸ መረዋውን ዘፋኝ ወደ ሳውዲ ምን አመጣው ? በሚል ባለጉዳዩ ስደተኛ ዘፋኝ ጠየቅኩት … መልሶልኛል ….
ሸዋንግዛው ንጉሴ በቀድሞው የአርሲ ክፍለ ከሃገር ሎዴ ኤዶሳ በሚባል አከቀባቢ በአንድ መንደር ተወለደ። የሙዚቃ ጥበብ ገና በብላቴና እድሜው የለከፈችው ሸዋንግዛው በሎዴ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ሲከታተል ጥበብ አብራው አደገች ። በሎዴ የትምህርይ ቤት ኪነት ለመመረጠረም ተሰጥኦ ያደለው ተርገብጋቢ ድምጽ ተሰጥኦውን ደገፈው እናም የቀደሙትን ዜማ እያነሳሳ ሲለው የራሱን እየገጠመና እያንጎራጎረ ህይወት በፈለገችው መንገድ ትጓዝ ዘንድ ሸዋ ብርታት አገኘ። ብዙም ሳይቆይ ታዳጊው ሽዋንዳኝ ከትምህት ቤት ወደ ወረዳ ኪነት ከፍ እያለ ሄደ … ከወርቁ ቢቂላ ( በኋላ ከሃይሌ ገ/ስላሴ ጋር አለም አቀፍ ሩጫን ይሮጥ ነበር) ታዳጊ እያለ የሙዚቃ ዝንባሌ ስለነበረው በአርሲ ሎዴ የወረዳ ኪነት አብረው እንደሰሩ ሸዋ ሩቅ ተጉዞ ዘርዘር ያለ ትዝታውን በአስደሳቹ ፈገግ እያለ በአስደሳቹ ትዝታ ፈገግ እያለ አጫውቶኛል … ሸዋንዳንኝ በወረዳው ኪነት ቡድን ተግቶ እየሰራ ባለበት ወቅትም ወደ ክፍለ ሃገር ኪነት ቡድን ለመምረጥ በተደረገ ውድድር ከወረዳ ወደ አርሲ ክፍለ ሃገር ቢመረጥም የወረዳው ሃላፊዎች በቅንነት “ልጃችን አሰልጥለን አንሰጥም !” በማለታቸው ወጣቱ በሙያው ርቆ የመሄድ ስሜቱ ተጎዳ ! እናም በብስጭት ወደ ውትድርና አለም ገባ ።
ሸዋንግዛው ማንጎራጎሩን ባንድ በኩል በሌላ በኩል ሳይወድ በተጎዳ ስሜት ገፋፊነት የገባበትን የውትድርና ስልጠና ወሰደ። ቀን ቀንን ሲወልድ ግን ውትድርናው ወደ ጦር ሜዳ ሳይሆን ወደ አሳደገው የሙዚቃ ጥበብ ዶለው ! በብስጭት የተጎዳኘው የውትድርና ስልጠና እንደጨረሰ የባሌ ሸዌ የጦር እዝ ማዕከል የኪነት ቡድን አባል ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም ። በጦሩ የኪነት ቡድን በመስራት ላይ እንዳለ የደርግን ስርአት የሚታገለው የኢህአዴግ ጦር ወደ ከተማዎች እየገፋ ሲመጣ የኪነት ቡድኑ ወደ ሲዳሞ በመሄድ ሌላ ተጨማሪ የመከላከል ስልጠና እንዲያደርግ ሲታዘዝ ከጓዶቹ ጋር ስልጠናውን ወሰደ። ከዚያም ድልድሉ ወደ ሞያሌ ሆነና ወደ ዚያው አመራ። በጭንቁ ቀን ያልተለየው የጥበብ አውሌ ማንጎራጎሩን ስላላስቆመው እንቅስቃሴውን ያዩ የሰራዊቱ አባላት ሸዋንግዛው የደቡብ እዝ ኦርኬስትራ ቡድን እንዲቀላቀል ግፊት አድርገው እንዲመረጥ ቢያደርጉም አሁንም የጦር አዛዡ ” ሸዋግዛውን ወደ ደቡብ እዝ አልለቀውም! ” በማለታቸው እድሉ ተጨናገፈ። ይህም ሲሆን ዳግም እክል የገጠመው ዘፋኙ ወጣት ተስፋ አልቆረጠም። ሙዚቃው እንቢ ቢለው በልጅነት ወደ ሚወደው ሌላ ሙያ አጋደለ። ባለበት ብርጌድ የእግር ኳስ ብቃቱን አስመስክሮ እግር ኳስ መጫወቱን በደስታ ተቀላቀለ ! በወቅቱ ኳሱም ተሳክቶለት ኮከብ ኳስ አግቢ በመሆን ተመርጦ እንደነበረ ሲያጫውተኝ ህይወት በትግል እንደምትፈተን አሸንፎም መውጣት ግዴታ እንደሆነ በፈገግታ እየገለጸልኝ ነበር ። ኢህአዴግ መላ ሃገሯን ሲቆጣጠር ጦሩ ፈረሰና ከሞያሌ ወደ ኬንያ የገባው ሸዋንግዛው እና የቀረው ስደተኛው በቀይ መስቀል ትብብር ወደ ሃገር ቤት ሲገባ ቤተሰቦቹን ከጠየቀ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ገባ ።
አዲስ አበባ ለአርሲው ተወላጅ ለሸዋንግዛው የተመቸች ነበረች። በተለይም በልጅነት የተለከፋት ሙዚቃ የሚያጎለብትበት ብቸኛ እድል አገኘ ። እናም በየምሺት ቤቶች “ከተፋ ቤቶች” ተሰማርቶ ምሽቱን እያደመቀ እና ራሱንና ቤተሰቦቹን በመርዳት መስራት ጀመረ ። ባለትዳር የሆነው ሸዋንዳኝ በምሽት ስራው በአሁኑ ሰአት ታዋቂ ከሆኑ ዘፋኞች ጋር እኩል ድምጽ ማጉያን ተጋርቶ በጥበብ ተናኝቷል !
ይህም ሁሉ ሆኖ ፣ ይህንን የከበደ መንገድ ተጉዶ ሸዋንዳኝ ከልጅነት እስከ እውቀት ሙጥኝ ያላት የተለከፈባት ጥበብ አዳብሮ የራሱን ወጥ ዘፈን ለማውጣት አልሆንልህ እያለው መቸገሩ አልቀረም። ሸዋንግዛው እንዲህ እየሆነ ህይወትን ሲገፋ ለማደግ የሚያደርገው ግብግብ ባያሸበርከውም እንዳደከመው ሳይደብቅ አጫውቶኛል። የጥበብ አውሌ ብቻዋን ከተዘፈቀበት ድህነት ራሱን ቀና አላደረገችውም! ይህ እንዳይሆን ፣ በሰው ሰራሽ በጥበብ ላይ የሚሰራ ደባ እየደሰቀው መፈናፈኛ እንዳሳጣው ሸዋንግዛው ይናገራል ! በተለይም “ከከተፋው” ዘፋኝነት ጎን ለጎን ብዙዎችን ዘፋኞች ያሳወቀውን ነጠላ ዜማ ግጥምና ዜማውን ራሱ ደርሶ ቢያወጣም ሃገር ስራውን እንዳያውቅለት ጫና ፈጣሪዎች አላገዙትምና ድንቅ የባህል ዘፈኑ ሳይደመጥለት እንደቀረ ዜማዋን እንድሰማት በመጋበዝ ሸዋ ብዙ አጫወተኝ። በሙዚቀኞች መካከል ውስጥ ለውስጥ የሚሰራውን “የቲፎዞ ” ድጋፍ ፣ አንዳንድ የሃገር ቤት ኤፍ ኤም ራዲዮ ጋዜጠኞችን ሙስና የማይለየው ድጋፍ ግልጥልጥ አድርገው ካወሩት ጉዳዩ ብዙ እንደሆነ ከዚህ በፊት የማውቀውን ታሪክ ሸዋንግዛው መትቶታልና በግላጭ አጫውቶኛል! …
ሸዋን ሳውዲ አረቢያ ስላደረሰው መንገድ እና የወደፊት ህልሙ እንዲያጫውተኝ ጠይቄው እንዲህ አለኝ ” ነጠላ ዜማው አልሳካ ሲለኝ ድህነቱንና የኑሮ ውድነቱን ለማሸነፍ እንዳልቻልኩ የገባት ጅዳ የምትኖረው እህቴ በኮንትራት ስራ እንድመጣ አመቻቸችልኝ። ተሳክቶም ልክ የዛሬ 11 ወር ወደ ሳውደሀ አረቢያ በኮንትራት ስራ መጣሁ ። በዘፈን ብዙዎች ይሳላካላቸዋል ። እኔ የእድል ጉዳይ ሆኖ አልተሳካልኝም ። ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ። የመጣውን መቀበል እንጅ አላማርረውም። አሁን የምሰራው ሮለር በሃገራችን ዳምጤ የሚባለው የኮንስትራክሽን መኪና እየነዳሁ በርሃውን ማቅመናት ነው ። በቃ ህይዎት እዚህ አድርሶኛል! እንደኔ ሃሳብና ህልም ከሆነ እንደምንም የሁለት አመት ኮንትራቴን ጨርሸና ገንዘቤን ሰብስቤ እግዚአብሄር ብሎ የሙዚቃዋ አድባር ከጠራችኝ ወደ ሙዚቃው መመለስ ነው ሃሳቤ፣ ካልሆነ የማገኛትን ይዠ ቤተሰቤንና ራሴን እየረዳሁ በሃገሬ መኖር ነው የምፈልገው! ለእስካሁኑ እግዚአብሔር ይመስገን! ወደፊትም እሱ ያውቃል! ” በማለት መልሶልኛል።
ሸዋንግዛው “ይሻላል እንደሁ! ” ብሎ ስራውን በኮንትራት ከመጣ ቀን ጀምሮ ስራውን የበርሃውን ቃጠሎ ተቋቁሞ ከጓደኞቹ ጋር እየሰራ ቢሆንም ደመወዝ አከፋፈሉ ቅሬታ አንዳለው ፈተና እንደሆነበት ገልጾልኛል። ከሸዋንግዛው ጋር በነበረን ቆይታ በበርሃው ውሎ አዳር ስለሚለከታቸው በእረኝነት ተቀጥረው ስለሚገፉ ኢትዮጵያውያን ይዞታ ሲያጫውተኝ ” የእኛን ተወው ደህና ነው ፣ የእረኛ ወንድሞቻችነወ ህይወት ብታየው ያሳዝናል፣ ሃበሾችን ከሩቅ ታውቃቸዋለህ። ስናናግራቸው ደስተኛ እንዳልሆኑ ይገልጹልናል። ወደ ሃገር ቤት እንዳይመለሱ ከድህነትና ኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ ያላቸውን ቅሪት አንጠፍጥፈው ተሰደዋልና ምነወ ይዘን እንግባ ? ይሉሃል ! ምን ትላቸዋለህ? ያ ያ ስላለ እንጅ ከኢትዮጵያ መጥተህ በበርሃው ውሃ እየተጠማህ የመንጋ በግ ፍየልና ግመል እረኛ ሆነህ ኑሮን መግፋት ይከብዳል። ታለቅሳለህ! ” ሲል ፊቱን በሃዘን ክችመወ አድርጎ አዘወኖ አሳዘነኝ … አዎ እኔም በአካል ተገኘወቸ ያየሁትና ዛሬ በርሃ ላይ ባገኘሁት ዘፋኝ የተገለጸልኝ ህይወት በእርግጥም ያሳዝናል! ያማል! ስሜትን የሚገለወጸው አይሆንም …ብቻ በባለጸጋ አረቦች ሃገር ከአረቦቹ ጓዳ ፣ እስከ ደራው ከተማና በርሃው የእኛ ህይዎት ሲሰሙት ውለው ቢያድሩ ተነግሮ አያልቅምና በዚሁ ልግታው ወደ በርሃው ውሎ የመጨረሻ ምዕራፍ ላቅና…
ከሸዋንዳኝና ከጓደኞቹ የነበረኝ አጭር ቆይታ ታለቅ የጽናትን እና ዥጉርጉሩን ህይዎት የተረዳሁበት መልካም አጋጣሚ ሆኗልና እዚያው ውየ ባድር ደስታየ በሆነ ነበር … ያ እንዳይሆን የእንጀራ እና የህይወት ጉዳይ አልፈቀደልኝም! እናም መለያየት ግድ ሆነ በሳውዲ ራብቅ በርሃ ላይ ያገኘሁትን ዘፋኙን ሸዋንዳኝ እና ጓኞቹን ስለያቸው በፍቅር ተሳስቀን እና ተቃቅፈን ተሳስመን ነበር ደግሜ ልጎበኛቸው ቃል በመግባት … ሸዋንዳኝን ስለየው ያቀበለኝን ባንድ ወቅት ሰርቷት በህዝብ ጀሮ ያልደረሰችውን “ሸዋ ጥበብ ያውቃል! ” ነጠላ ዜማው እየኮመኮምኩ በርሃውን ለቅቄ ወደ ጅዳ መገስገስ ጀመርኩ … በሸዋ ” ሸዋ ጥበብ ያውቃል !” ደምቄ …
” ከወዲያ ከወዲህ ስታንገላታኝ
ይህች የመንዝ ልጅ አስራ ልትፈታኝ
ቃሌ አይታጠፍም የመጣው ቢመጣ
እንዳሻት ታድርገኝ አላበዛም ጣጣ ” ይለዋል … በጥበቡ የሸዋን ጉብል የከበደ ፍቅር ሲገልጸው ….
ምንጃርኛውን ያሚያስደስተው ሞቅ ደመቅ ባለው ቅንብርና ዜማ የታጀበ ብቻ በመሆኑ አይደለም! የሸዋ ግጥሞች መልዕክት አላቸው …
የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ … እንደጨው ተበትነናልና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወገኖቸን በየሔድኩበት ከተማ ፣ በቀለጡ በርሃዎች እና መንደሮችም ወንድም እህቶቸን አገኛለሁ ! እንዲህ በማለዳ ወጌ ወጋወጉን ለተሞክሮ ሳካፍላችሁ ደግሞ ደስታ ይሰማኛል ! ህይዎት እንዲህ ይኖራል …

የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል የተመሰረተበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

 


ታህሳስ 7  2006 ዓም የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ከተመሰረተ  አንድ አመት ሞላው። አንድ አመት  በጭንቅና  በአሳር  ለተያዘች የዛሬይቱ ኢትዮጵያና ህዝቧ እጅግ ረጅም ግዜ እንደሆነ ህዝባዊ ሃይሉ በሚገባ  ይገነዘባል። ባላፈው አንድ አመት ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የመከራ የአሳርና የውርደት ህይወት ይበልጥ እየሰፋ፣ የሚፈጸምበት ግፍ ይበልጥ እየገዘፈ መሄዱን አይተነዋል። በሃገርና በህዝብ ላይ እየወረደ ያለውን ወያኔ ወለድ የስቃይና የፍዳ ናዳ በቅጡ ላጤነው  ሃገሪቱና ህዝቧ የአዳዲስ የስቆቃና የመከራ አይነቶች መፈተኛ ቤተ ሙከራዎች እየተደረጉ ለመሆኑ ጥርጥር አይኖረውም። ለሚራበው ለሚረገጠው በግፍ ለታጎረው፣ በኑሮ ውድነት ለሚጠበሰው፣ ለተሰደደው ለተፈናቀለው ኢትዮጵያዊ እንድ አመት በሲኦል የቀናትና የወራት መቁጠሪያ እንደሚለካ ዘመን እጅግ የረዘመ የስቃይ ግዜ ነው።Ginbot 7 Popular Force logo
የዋልድባ መነኩሳት ገዳማችን  አትድፈሩ አታፍረሱ በማለታቸው እየተገረፉ ለዘመናት ፈጣሪያቸውን ከሚማጸኑበት ለሃገርና  ለህዝብ ምልጃ ከቆሙበት ገዳም በዘር መመዘኛ እየተለዩ  እንደቆ ሻሻ ተጠርገው የተባረሩበት ፣ እምነታችን አትንኩ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችና  መሪዎቻቸው በሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው  ወህኒ መውረዳቸው አንሶ  ወንድሞቻችን ይፈቱ በማለት  ሰላማዊ  ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖቻቸን በወያኔ ነፍሰ- ገዳዮች  በአረመኔያዊ ጭካኔ የተጨፈጨፉት በዚሁ አመት ነው። ወያኔ በህዝብ መሃከል በዘራው የዘር መርዝ የተነሳ በሽዎች የሚቆጠሩ አማሮች ከጉራ ፈርዳና ከቤንሻንጉል፣ ኦሮሞዎች ለዘመናት ከኖሩበት ምስራቅ ሃረርጌ  አካባቢ  እንዲፈናቀሉና በገዛ ሃገራቸው መድረሻ ቢሶች  እንዲሆኑ የተደረገው በዚህ አንድ አመት ውስጥ ነው። ጋምቤላዎች ሙርሲዎች አፋሮችና ሌሎችም ብሄረሰቦችና ማህበረሰቦች የተጨፈጨፉበት፣በልማት ስም ለመጡ የውጭ ወራሪዎችና ወያኔ ለፈጠራቸው ቱጃሮች ቦታ እንዲለቁ ተደርጎ ቀደምቶቻቸው ለዘመናት ከኖሩባቸው ቀየዎች እንዲነቀሉ ተደርገው እንደ አልባሌ ነገር የትም እንዲበተኑ የማድረጉ ሂደት ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ የቀጠለው በዚሁ አመት ነው። በዚሁ አንድ አመት በወያኔ የሃገሪቱ ገዥዎች በህዝብ ላይ የተፈጸመው  ጭካኔና ወንጀል ተዘርዝሮ  የሚያልቅ አይደለም።
ይህ ወያኔ  ሰራሽ ሃገር በቀል የውርደትና  የስቃይ ህይወት አልበቃ  ብሎ ወያኔ ከሳውዲ የጨለማ ዘመን ገዥዎች ጋር በመተባበር ወንድሞቻችን በሳውዲ አውራ ጎዳናዎች ላይ እንዲታረዱ እህቶቻችን በቡድን በተደራጁ የሳውዲ ጎረምሳዎች  እንዲደፈሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶ  ለኢትዮጵያውያን ያለውን እጅግ የከረረ ጥላቻ በአደባባይ ያሳየበት አመት ነው። እንዲህ አይነቱ የጅምላ ግፍና  ውርደት ከመከሰቱ በፊት ህዝባዊ ሃይሉ በአረብ ሃገር በባርነትና  በስደት የሚገኙ እህትቶቻችንን ወንድሞችችን ስቃይ  ስቃዩ አድርጎ በመውሰድ “ላንቺ ነው” በሚለው ድርጅታዊ መዝሙሩ “በባለጌ  አረቦች መዳፍ ውድ ክብራቸው ለጎደፈው እህቶቻችን፣ በአረቦች የባርነት ቀንበር ጀርባቸው ለጎበጠው  ወገኖቻችን እንደርስላችኋለን፣ የተሰባሰብነው  ደማችን የሚፈሰው የመከራ ቀናችሁን ለማሳጠር ነው” የሚል ቃል ኪዳኑ ሰጥቶ  ነበር። የድርጅታችንን ምስረታ አንደኛ  አመት ስናከብር ልባችንን ደስታ ሳይሆን ሃዘን እንዲሞላ የሚያደርገው ይህ ቃል ኪዳናችን ለማክበር የጀመርነው ጉዞ ከድርጅት ምስረታና ከድርጅታዊ ዝግጅት አልፎ   በኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻና ንቀት  የተነፋውን የወያኔን እብሪት በማስተንፈስ የወሰዳቸው ተጨባጭ የአለኝታነት እርምጃዎች ባለመኖራቸው ነው።
ምንም እንኳን ግንቦት7 ህዝባዊ ሃይል እራሱን እንደ ድርጅት አቁሞ  ኢትዮጵያውያንን አሰባስቦ  መራራው ትግል የሚጠይቀውን የፖለቲካ  የወታደራዊ ስልጠናና ትጥቅ አስታጥቆ  በወያኔ  ላይ ለመዝመት የጀመረውን ጉዞ የሚያስቆመው ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ብናውቅም የህዝብ ስቃይ ለግዜው መቀጠሉ የህባዊ ሃይሉን አባላት ማሰቃየቱ አልቀረም። በወያኔ  ግፈኛ አገዛዝ የተንገፈገፈው ወገናችን ህዝባዊ ሃይሉ የወያኔን አገዛዝ እድሜ  የሚያሳጥሩ ፈጣን እርምጃዎችን እንዲወስድ በከፍተኛ  ጉጉት እየተጠባበቀ እንደሆነ  እናውቃለን። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች በተጠንቀቅ እንደቆሙ እናውቃለን። እነዚህ ዜጎች ከሁሉም የእምነት የቋንቋ  የጾታ የእድሜ  የኑሮና  የማህበረሰብ ስብጥር የሚያካተቱ  እንደሆኑ እናውቃለን። በሃገሪቱ ታሪክ ተሰምቶና  ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ  የወታደር ልብሱን  እየጣፈ እንዲለብስ፣  የወታደር ጫማውን መቀየሪያ አጥቶ  ሸበጥ እንዲያደርግ የተገደደውን፣  የወያኔ ጀነራሎች በስልጣንና  በዘረፋ ሲያብጡ በድህነት እንዲሟሽሽ የተፈረደበት የሃገሪቱ ሰራዊት በዘር በእምነት ሳይለያይ ከህዝባዊ ሃይሉ ጎን ለመቆም አሰፍስፎ  የቆመ  እንደሆነ  እናውቃለን። ይህ ሃገራዊ እውነታ ለህዝብ የገባነውን ቃልኪዳን የለምንም ጥርጣሬ  ማስከበር እንደምንችል በሙሉ ድፍረት እንድናውጅ የሚያስችለን ሃቅ ነው።
የወያኔ ጀንበር እየጠለቀች የኢትዮጵያ  ህዝብ ጀንበር እየፈካች የመሄዱ ጉዳይ እንደማይታጠፈው  የመንጋትና  የመምሸት የተፈጥሮ ህግ ነቅነቅ የማይል እንደሆነ ግንቦት7 ጠንቅቆ ያውቃል።  እውቀታችን ልዩ ጥበብ የሚጠይቅ ኣይደለም። ግፍ ፍትህን አሸንፎ፣ እውነት በሃሰት ተደፍቃ፣ ጥላቻ ፍቅርን፣ አድሎ እኩልነትን፣ ሃገራዊ ክህደት ሃገር መውደድን፣ ባንዳነት አርበኛናትን ለዘላላሙ ቀብረው የሄዱበት የሃገራችንና  የሰው ልጆች ታሪክ የለምና የወያኔን አይቀሬ ሞት ለመተንበይ  ልዩ ጥበብ አያሻንም። ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን በዘረፋና በጥላቻ  የደነዘዘ ህሊና ያዳበሩት የወያኔ  ባለስልጣናትም ያውቁታል። ያለእኔ  ጀግና የለም፣ ያለእኔ  አልሞ  ተኳሽ የለም በሚል እብሪት በመጻደቅ የሚታወቁት ወያኔዎች በመቶ ሽዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ተከበው፣  በታንክ በአይሮፕላን በሚሳይል ታጅበው ከሚኖሩበት ቤተመንግስትና ቪላዎች ውስጥ ብርክ እንዲይዛቸው ያደረገው ለመሆኑ፣  ሳር ቅጠሉ ግንቦት ሰባት እየመሰላቸው ሲበረግጉ እንደሚያመሹ፣  የግንቦት ሰባት አባላት እያሉ ከድርጅታችን ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች እያሰሩ ሲያሰቃዩ ፣  ከምላሳቸው ላይ ግንቦት 7  የሚል ስም ተፈናጦባቸው  እንደሚውሉ በራሳቸው ሚድያ  ወያኔዎች ራሳቸው እያሳዩን እያስደመጡን ነው። ከዚህም አልፎ በዚህ አንድ አመት ውስጥ  የህዝባዊ ሃይሉን መሪዎች በመግደል ድርጅቱን ለማኮላሸት ይቻላል በሚል ወያኔ የላካቸው ነፍሰ ገዳዮችና ድርጅቱን ከውስጥ ለመቦርቦር ያሰማራቸው ሰርጎገቦች ተራ በተራ ተልእኳቸው እየከሸፈ በህዝባዊ ሃይሉ እጅ እየወደቁ ወይም ተልእኳቸው እንደማይሳካ ሲረዱ እየፈረጠጡ ወደ ወያኔ ሲመለሱ አይተናል።
ያለፈው አንድ አመት ተመክሯችን ስለወያኔ  ብቻ ሳይሆን ስለራሳችንም ጥንካሬና  ድክመት ብዙ ነገሮች ያስተማረን ኣመት ነው። የቀደምቶቻችን የጀግንነት የአርበኛነት ቅርስ በመላ ህዋሳቸው የተሸከሙ  ለኢትዮጵያ እና  ለህዝቧ ሲሉ ደማቸው ለማፍሰስ ውድ ህይወታቸውን ለመሰዋት ወደኋላ የማይሉ ቆራጥ ብቻ ሳይሆኑ አርቀው የሚያዩ  በርካታ ልጆች  ሃጋሪቷ ያሏት መሆኑን ያረጋገጥንበት አመት  ነው።  በሌላ በኩል ደግሞ  ድርጅታችን የኢትዮጵያን ህዝብ ብቸኛው የመንግስት ስልጣን ባላቤት የማድረጉን ታሪካዊ ራእዩን ለመሳካት የሚያደረገው ትግል ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም ጋር የሚደረግ እንደሆነ  በሚገባ  የተረዳነው  በዚሁ የአንድ አመት የድርጅታችን እድሜ  ነው። ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል ወያኔ በማህበረሰባችን ውስጥ ከዘራቸውና የሃገሪቱን ዜጎች እንዲበክሉ ካደረጋቸው የዘረኛነት የአድሎ  ከህዝብና  ከሃገር ጥቅም በፊት የራስን ጥቅም ማስቀደም፣ የሱሰኛነትና የሙስናና ሌሎችም አደገኛ ባህሎች ጋር ነው።
ህዝባዊ ሃይሉ ደግሞ  ደጋግሞ  እንደገለጸው ትግላችን አንድ መንግስታዊ ስርአት ወድቆ ሌላው የመንግስት ስርአት በመጣ ቁጥር የህዝብ ተስፋ እየጨለመ  “አዲስ ከመጣው ስርአት ያላፈው ያረጀ ስርአት በግፈኛነቱ በዘራፊነቱ ያነሰ ነበር” የሚል የግፈኛና የዘራፊ ስርአቶች ንጽጽር ላይ የቆመ አሳዛኝ የህዝብ ህይወት እንዲያበቃ ነው። ደርግን ያየ የአጼውን ስርአት እንከኖች ረስቶ ንጉሱ ይሻሉን ነበር ያለበት፣ ወያኔን ያየ የደርግን አስከፊ ዘመን ረስቶ መንጌ በስንት ጣሙ ያለበት አሳዛኝ ሁኔታ ከወያኔ መውደቅ በኋላ በሃገራችን እንዳይደገም ነው ትግላችን። የኢትዮጵያ ህዝብ የውድ ልጆቹን ህይወት ገብሮ ወያኔን በማስወገድ የሚያመጣው ስርአት ከወያኔ ብሶ ህዝብ ወያኔ ማረኝ የሚልበትን ቅስም ሰባሪና አዋራጅ የታሪክ ቅጥልጥሎሽ  እንዳይቀጥል ማድረግ ህዝባዊ ሃይሉ የተመሰረተበት፣ አባላቱ መከራ ለመቀበልና መስዋእትነት ለመክፈል በረሃ የገቡበት ዋናውና ብቸናው ምክንያት ነው። ትግላችንን መራራ የሚያደርገው ከበሰበሰውና የአንድ ጀምበር የህዝብ ቁጣ ከታሪክ ቆሻሻ የመጠያ ስፍራ ከሚከምረው  የወያኔ ስርአት ጋር ብቻ ሳይሆን በወያኔ ቦታ የሚተካውን ስርአት ከአድሎና ከዘረኛነት ከዘረፋና ሃገራዊ ክህደት የጸዳ፣ ዳግም ለኢትዮጵያውያን ውርደትና እንግልት ምክንያት እንዳይሆን ለማድረግ ከራሳችን ጋር ሳይቀር የማያቋርጥ ትግልን ማድረግ የግድ ስለሚል ነው። ህዝባዊ ሃይሉ የአመጽ ትግል የሚያደርግ፣ የመሳሪያው ብዛትና  የሰራዊቱ ቁጥር እያደገ  የሚሄድ ሃይል መሆኑን ስለምንረዳ  ይህን ሃይል ገና ከጅምሩ ከብዙ እንከኖች እያጸዱ ማደራጀት ካልተቻለ  በሃገርና በህዝብ ላይ የሚመጣውን አደጋ  የህዝባዊ ሃይሉ አባላት ጠንቅቀው የተረዱት ሃቅ ነው። ይህ ግንዛቤ የሰራዊቱን አባላት በጥንቃቄ መመልመልን፣ ማሰልጠንንና መገንባትን የግድ የሚል ነው።
ይህ ከራሳችን ጋር የሚደረግ ትግል እጅግ መራራ ነው። ታሪካዊ ስህተቶችን ላለመድገም የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ትግል የአካልና የመንፈስ ጽናትን፣ ሃቀኛነትን፣ ታማኝነትን፣ ጀግንነትን የሚጠይቅ ትግል ነው። የወያኔ ስርአት ከሃገር ግድያው በተጨማሪ ትውልድን ለመግደል ሆን ብሎ ያስፋፋቸው እኩይና ጎጂ ባህሎችና ልምዶች ምን ያህል ማህበረሰባችንን እንደጎዱት ህዝባዊ ሃይሉ ባላፈው አንድ አመት እድሜው በሚገባ የተረዳው ጉዳይ ሆኗል። ህዝባዊ ሃይሉ የሚመኘውን የኢትዮጵያ ትንሳኤና ተሃድሶ እውን ለማድረግ እነኝህ  ወያኔ ሆን ብሎ  ያስፋፋቸውን የባህልና የሞራል ብክለት ማጽዳት የግድ እንደሆነ የተረዳ አካል ሆኗል።
ትግላችን መደፍረስን መጥራትን፣ መንተክተክን መስከንን የትግሉ ሂደት አካል አድርጎ  የሚጓዝ ነው።   ትግሉ የሚልመጠመጠውን እንደቀስት ቀጥ ብሎ ከሚራመደው፣ በካፊያው የሚንቀጠ ቀጠውን ለዶፉ ደንታ ከሌለው፣ ዝናር በቅፌን ከምሩ ተኳሽ  የሚለይ መራራ ትግል ነው። ያለፈው አንድ አመት ይህን አስተምሮናል። ህዝባዊ ሃይሉ ትግሉ ቀላል ነው የሚል ከእውነታ ጋር ያልተያያዘ ቃል ለህዝብም ሆነ ህዝባዊ ሃይሉን ሊቀላቀሉት ለተዘጋጁት ወገኖቹ አይናገርም። ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል ለተሰለፉ በሽዎች ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን ትግሉ የሚጠየቅውን የሞራል የስብእና ጥብቅነት፣ከፍተኛ  የሃገርና የወገን ፍቅር፣ ጥልቅ የሆነ የመስዋእትነት ፈቃደኛነት የሚጠይቅ መሆኑን ከማስረዳት አንቦዝንም። ህዝባዊ ሃይሉ ለህዝብ ቃል እንደገባው ከወያኔ  ጋር የምናደርገው ትግል በጥበብ በእውቀት በጥናት በጥንቃቄ የምናደርገደው ነው። ነጻነት ያለመስዋእትነት እንደማይሳካ ብናውቅም ለተራ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስንል በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት የሃገሪቱን ውድ ልጆች በከንቱ የሚማግድ ጀብደኛ እንቅስቃሴ  አናደርግም። የውሸት ተስፋ  ህዝብን አንመግብም።  አይናችንን ከዋናው የኢትዮጵያና  የህዝቧ  ጠላት ከሆነው ከወያኔ ላይ አንስተን በሌሎች  ወያኔን እቃወማለሁ በሚሉ ሃይሎች ላይ አንተክልም። ከወያኔ ሌላ ወደ ጎን የምንዋጋው፣ የምንጨቃጨው አታካራ የምንገጥመው ምንም ሃይል አይኖርም። ወያኔን ለመምታት ህዝባዊ ሃይሉ የጨበጠው  ቡጢ ወገኖቻችን በፍቅር ለመጨበጥ የሚዘረጉ ጣቶች  እንዳሉት በጸረ ወያኔ ዴሞክራሲያዊ ትግሉ  ከልባቸው ለመተባበር ለሚፈልጉ ሃይሎች ሁሉ ግልጽ እናደርጋለን።
ያለፈው አንድ አመት የመሰባሰብ የድርጅት ምስረታ  መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካና የወታደራዊ  ስልጠና የተሰጠበት፣ የድርጅት ማጠናከሪያና የማጥራት ሂደት የተካሄደበት ነው። በዚህ ረገድ የተሰራው ስራ አጥጋቢ ውጤት አስገኝቷል። ስልጠናው፣ ድርጅት ማጠናከሩና  ማጥራቱ ወደፊትም የሚቀጥል ነው። መጪውን አመት የተለየ የሚያደርገው ህዝባዊ ሃይሉ በህዝብ ላይ በሚደርሰው ግፍና ውርደት ከሚሰማው ከፍተኛ ብስጭትና ቁጭት አልፎ ባላፈው አመት ሊደርስላቸው ያልቻለውን የሃገራችንን ግፉአን ህዝቦች መታደግ የሚችልበትን እርምጃዎች መውሰድ የሚችልበት አመት መሆኑ ነው። በዚህ የህዝባዊ ሃይላችን የአንደኛ አመት ምስረታ  ክብረ በአል ወቅት ወገንም ጠላትም በግልጽ እንዲያውቀው የምንፈልገው ይህን ሃቅ ብቻ ነው።
ውድመት ለዋናውና  ለብቸኛው የኢትዮጵያ ህዝብና  የኢትዮጵያችን ጠላት ለሆነው የወያኔ ገዥ ጉጅሌ!
ድል በወያኔ ግፈኛ ስርአት አበሳውን ለሚያየው የመላው የኢትዮጵያ  ህዝብ!

Thursday, December 5, 2013

የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ካድሬዎቻቸው በፓስፖት እና በቀበሌ መታወቂያ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ተገለፀ።

የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ካድሬዎቻቸው በፓስፖት እና በቀበሌ መታወቂያ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ተገለፀ።
 
ሰሞኑንን ኢ.ቲ.ቪ አይናችን በሚል ፕሮግራሙ ባሰራጨው በዚህ ስፊ ዘግባ ላይ የኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ጉዳይ መምሪያ መቤ/ት እና የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት መዋቅር እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቀበሌዎች ውስጥ የተሰማሩ ካድሬዎች በመታወቂያ እና በፓስፖርት ህገወጥ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ከቀረበው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። 
በአንድ ቤት እስከ 40 መታወቂያ የሚወጣበት አጋጣሚ መኖሩን በተጨባጭ፡ያረጋገጠው የፕሮግራሙ አዘጋጅ የኤምግሬሽኝ እና ስደተኞች ጉዳይ መመሪያ ሃላፊዎች ለውጭ፡ሃገር ዜጎች ፓስፖርት በመሸጥ የአሰሪ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ከፍተው አያሌ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ወደ አረብ ሀገር በመላክ ለሞት እና ለስቃይ መዳረጋቸውን ጸሃይ የሞቀ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑ ቢታወቅም ኢቲቪ የተጠቀሱትን ባለስልጣኖች በግርድፉ የህገሪቱን ሰነድ አሳልፈው የሸጡ ብሎ አድበስብሷት አልፎል። 
እንደሚታወቀው ከዛሬ 4 አመታት በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ለሳውዲ አረቢያ የቤት ሰራተኛ ለማቀረብ በገባው ውል መስረት አንዳንድ ከፍተኛ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ባለስልጣናት በውጭ፡ሃገር ዜጎች ስም በእጅ አዙር ሰራተኛ እና አስሪ ኤጀንሲዎችን ከፍተው ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተጓዥ እስከ 7መቶ ዶላር በማስከፈል በወር ከ 45 ሺህ ያላነሱ እድሜያቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ኢትዮጵያውያንን ህጻናት እህቶቻችንን ጭምር ያለምንም የህይወት ዋስትና ወደ ሳውዲ አረቢያ በመላክ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ.መንግስት ባወጣው ህግ ሸፋን በወገኖቻችን ደም ንግድ ላይ ተሰማርተው መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ ። የሳውዲ አረቢያ መንግስት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ወደ ሃገሩ እንዳይገቡ የመግቢያ ቪዛ ማገዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የተጠቀሱትን ኤጀንሲዎች ላልተወሰነ ግዜ መዝጋቱን ለማረጋገጥ ተችሏል። 
Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ

“መንግሥት ከግንቦት ሰባት ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ የለም” Ethiopian government did not request to negotiate with Ginbot 7

December 4/2013 (በሰንደቅ ጋዜጣ) “መንግሥት ከግንቦት ሰባት ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ የለም” Ethiopian government did not request to negotiate with Ginbot 7

በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፤ ኢህአዴግ ለደርድር ጥያቄ አቅርቦልኛል በሚል እያናፈሰ ያለው መሰረተ ቢስ የፈጠራ ወሬ መሆኑን አቶ ሽመልስ ከማል የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አስታወቁ።
ግንቦት 7፤ ህዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም በኢሳት ቴሌቪዥን በኩል ባወጣው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በሁለት ወር ጊዜያት ውስጥ ለሶስት ጊዜያት ያህል የእንደራደር ጥያቄ አቅርቦልኛል ብሏል። ንቅናቄው ለእንደራደር ጥያቄው ምላሽ በሚል ባሰፈረው ሐተታ የኢህአዴግ የእስካሁኑ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ውጥረት ሲበዛበትና መዉጪያና መግቢያዉ ሲጠፋዉ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችን “እንወያይ፣ እንደራደር” በማለት ለውጥረት ማስተንፈሻ ጊዜ ይገዛል ካለ በኋላ ስማቸው ባልተገለጸ መልዕክተኞች በኩል ደርሶኛል ያለውን “የእንደራደር” ጥያቄ ንቅናቄው በዋናነት ያየው ኢህአዴግ እንደለመደው ድርድርን ለውጥረት ማስተንፈሻነት ለመጠቀም እየሞከረ ነው በማለት ለድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።
አቶ ሽመልስ ከማል ግን በመንግስት በኩልም ሆነ በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በኩል ለግንቦት 7 የቀረበ እንደራደር ጥያቄ እንደሌለ አረጋግጠው መንግስት ቢፈልግ ጌታው እያለ ከተላላኪው ጋር ምን ያደራድረዋል ሲሉ ጠይቀዋል። ይህ የእነዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቅጥፈት መሆኑን ጠቅሰው “በዚህ መንገድ እያሞኙ ገንዘብ መሰብሰብ ለምደዋል፤ ይህም ውሽት ለዚሁ ተግባር የተፈበረከ ነው” ብለዋል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ሁኔታ ድጎማና ድጋፍ ለሚሰጧቸው አካላት ሒሳብ ለማወራረድ ድል አድርገን ልንገባ ነው በማለት ሲቀጥፉ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሽመልስ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በባዶ ሜዳ ራስን አግዝፎ ለማየት ከመመኘት የሚመነጭ ቅዥት ነው ብለውታል።

Monday, December 2, 2013

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በውጭ ስርአቱ ጥሩ ነው ይበሉ እንጅ በግል ሳናግራቸው ለውጥ እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል ሲሉ ወ/ሮ አና ጎሜዝ ተናገሩ

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በውጭ ስርአቱ ጥሩ ነው ይበሉ እንጅ በግል ሳናግራቸው ለውጥ እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል ሲሉ ወ/ሮ አና ጎሜዝ ተናገሩ

ህዳር (ሃያ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል እና የኢትዮጵያን የ1997 ምርጫ የታዘቡት ወ/ሮ አና ጎሜዝ ይህን የተናገሩት አዲስ ስታንዳርድ ለተባለ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ነው።
በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው የአውሮፓ፣ አፍሪካና ካረቢያን አገሮች የፓርላማ ጉባኤ ላይ የተገኙት ወ/ሮ አና የአምባገነን ምንጭ የሆነው መለስ ዜናዊ ቢሞትም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ አለመምጣቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ተለውጣለች በማለት በአደባባይ የሚናገሩት ባለስልጣናት በግል ሳነጋግራቸው በኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ መደረግ አለበት ብለው ይላሉ ያሉት ወ/ሮ አና፣ አቶ ሀይለማርያም  ከሙስና ጋር በተያያዘ አንዳንድ መጠነኛ እርምጃዎችን ቢወስዱም፣ የትግራይ ተወላጅ ባለመሆናቸው ስልጣናቸውን ለማቆየት እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸዋል። ቀደም ብለው እስክንድር ነጋንና ርእዮት አለሙን ለመጎብኘት በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ትእዛዝ ወደ ቃሊቲ የተጓዙት የአውሮፓ ህብረት ልኡካን፣ በእስር ቤቱ ሀላፊዎች መከልከላቸው በአገሪቱ ውስጥ ያለውን እውነታ የሚያሳይ ነው ያሉት ወ/ሮ አና በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ እንዳለ እንደሚያውቁም ተናግረዋል።
የመለስ ዜናዊ መንግስት ስልጣኑን ለማቆየት ሲል ሙስሊምና ክርስቲያኑን ለማጋጨት ጥረት ሲያደርግ እንደነበርም የፓርላማ አባሉዋ ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ወጣቶች አፍኖ መያዝ አይቻልም ያሉት ወ/ሮ አና የፖለቲካ ሜዳውን ለዲሞክራሲ መክፈት ኢትዮጵያን ከውድቀት እንደሚታደጋት ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ዜጎች ጋር በተያያዘ በሳውድ አረቢያ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ማንዣበቡን ኢትዮጵያውያን ተናገሩ

ከኢትዮጵያ ዜጎች ጋር በተያያዘ በሳውድ አረቢያ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ማንዣበቡን ኢትዮጵያውያን ተናገሩ

ህዳር (ሃያ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በሳውድ አረቢያ የሚታየው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነው ይላሉ ያነጋገርናቸው ዜጎች። ከ40 ሺ በላይ ኢትዮጵያን በእስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቀናቸውን ይጠባባቃሉ። የኢትዮጵያ መንግስት በመቶ ሺ የሚቆጠረውን ስደተኛ ለማስተናገድ የመደበው የሰው ሀይል 40 ብቻ ነው። የሳውድ አረቢያ መንግስት ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ምድር ተጠራርገው እንዲወጡ እየቀሰቀሰ ነው። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አደጋ ሊፈጠር ይችላል ብሏል  አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ጋዜጠኛ።
በዛሬው እለት በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች የተበተነው የኤስ ኤም ኤስ መልዕክት  ህጋዊ ለተባሉትም ሆነ ህገወጥ ለሚባሉት ኢትዮጵያውያን የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ይላሉ እኝህ ጋዜጠኛ።
በሞባይል ስልኮች የተበተነው ኤስ ኤም ኤስ ኢትዮጵያውያንን ቀጥራችሁ የምታሰሩ እንዲሁም መኖሪያ ቤት ያከራያችሁ ሁሉ በአስቸኳይ እንድታስወጡ፣ ይህን ባታደርጉ ግን 100 ሺ ረያል ትከፍላለችሁ የሚል እንደሆነ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል። ይህን መልእክት ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተከራዩበት ቤት ተባረዋል። 9 ኢትዮጵያውያንን ወደ አስጠጋው ኢትዮጵያዊ በመደወል መታሰቢያ ቀጸላ አነጋግራቸዋለች። እርሱ እንደሚለው መልክቱ መተላለፉን ተከትሎ ጓደኞቹ ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርጎ በእርሱ ቤት ተጠልለዋል
ከቤታቸው ከተባረሩት መካከል አንዱ ከ8 ወራት በፊት አባቱ ቤታቸውን ሸጠው ፣ በኪራይ ቤት እየኖሩ በህጋዊ መንገድ እንደላኩት ይናገራል። አሁን ቤትክን ለቀህ ውጣ ተብሎ ህይወቱ አደጋ ላይ ወድቋል
የሳውዲ መንግስት በኦፊሴል እንዲህ አይነት መልክት ያስተላልፍ እንደሆነ የጠየቅነው ጋዜጠኛ፣ መንግስት በቀጥታ እንዲህ አያደርግም ነገር ግን እርሱ ባሰማራቸው ሰዎች አማካኝነት መልክቶችን እንደሚሰድ ይታወቃል ብሎአል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ዘመቻ በማድረግ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት መታደግ ሲችል በቀን ይህን ያክል ሰው አስመጣሁ በማለት ፕሮፓጋንዳ ይነዛል የሚለው ጋዜጠኛው፣ በሳውዲ የቀረው ኢትዮጵያዊ ወደ አገር ቤት የተመለሰውን በብዙ እጥፍ ይበልጣል ሲል በአገሪቱ ያለውን እውነታ አስረድቷል።
በሌላ በኩል ከሳውድ አረቢያ ወደ የመን የገቡ 3 ሺ ያክል ኢትዮጵያውያን በምግብ እጥረት ተጎሳቁለው እንደሚገኙ እስር ቤት ድረስ በመሄድ ጋዜጠኛ ግሩም ተክለሀይማኖት ጎብኝቷቸዋል።

ሰልፍ ብቻ በቂ ነው ወይ? አንድ መላ እንበል….ተርበዋል፣ ተጠምተዋል..እንድረስላቸው በግሩም ተ/ሀይማኖት

ሰልፍ ብቻ በቂ ነው ወይ? አንድ መላ እንበል….ተርበዋል፣ ተጠምተዋል..እንድረስላቸው በግሩም ተ/ሀይማኖት

saudi-2-225x300
በሳዑዲ ለተከሰተው ሁኔታ..ለወገን ድምጽ ለማሰማት ይህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ በየሀገሩ የሚያደርገውን ሰላማዊ ሰልፍ ሳይ ልቤ ቅቤ ጥጥት ያደርግና ሳይበቃው አንድ ሀሳብ ውስጤ ስውጥ ብሎ ይጦልማል፡፡ እንደገና ብልጭ ይልና ምላሽ ፍለጋ ያንከራትተኛል፡፡ ‹‹..እያደረግን ያለነው በቂ ነው ወይ? ድብደባውም ይቁም የሞቱትም ይታወሱ…በህይወት ያሉትስ ምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት? በተለያየ ቦታ ታጉረው ምግብ እጦት፣ ውሀ ጥም..ሌላም ሌላም ችግር አለባቸው፡፡ ሀገር ሲገቡም ማረፊያ ቦታ የሌላቸው ሞልተዋል…ይህን ሳስብ ምን ብናደርግ ይሻለናል?›› የሚለው ጥያቄ በጉልህ ውስጤ ተጽፎ ምላሽ ይናፍቃል፡፡ አምጬ አምጬ..ውስጤ ሲላወስ ቆይቶ መፍትሄ ፍለጋ ከማውቃቸው ጋር ሁሉ ስወያይ ቆይቼ አንድ ስለሺ የተባለ ወዳጄ ከወደ ሀገረ እንግሊዝ ሀሎ ብሎ አማካረኝ፡፡ ውስጤ ያሰበውን ስለነገረኝ ወይም ምን ማድርግ እንዳለብኝ እያሰብኩ የነበረውን አወጋሁት፡፡
የምናደርገው እንቅስቃሴ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በእርግጥ በታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ህብረት አሳይተናል፡፡ ለነገሩ ኢትዮጵያዊያን ስንነካ እንደ ንብ ግር ብለን ህብረታችንን እናሳያለን፡፡ ግን ይህ ብቻ በቂ ነው ወይ? የገቢ ማሰባሰቢያ ማድረግ እና በማጎሪያ ቦታ ያሉትን ምግብ የምናቃምስበት ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ ነው፡፡ ሀገር የገቡትስ ቢሆን ነገ ጎዳና አናያቸውም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ ከሳዑዲ ከመጡት ውስጥ የተወሰኑትን ለማናገር ሞክሬ ነበር፡፡ 12 እና 13 አመት ሳዑዲ ሲኖር እናት አባቱ ሞተው ቤቱን ቀበሌ የተረከበበት ሁኔታ ያጋጠመው ልጅ እንዳለ..መግቢያ የሌለው በፊትም ቤተሰብ አጥቶ በባህር የወጣ አለ፡፡ ዛሬ የት ነው የሚገባው አግብቶ ወልዶ ያለም አለ ዛሬ የት ነው የሚመለሰው ቤተሰብ ላይ…ሁሉም ምላሽ የሌላቸው አሳሳቢ ነገሮች ናቸው፡፡
ገቢ አሰባስበን አንድ ነገር ማደድረግ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ? በውጭ ያሉ አርቲስቶችም ቢሆን የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ቢያደርጉ በጣም በደስታ ብዙዎች እንደሚሳተፉ አምናለህ ወገን ለወገኑ የቻለውን ለማድረግ ወደ ኋላ አይልም የሚያሰባስበው ማጣት ይመስለኛል፡፡ እባካችሁ አንድ መላ እንበል….ተርበዋል፣ ተጠምተዋል..እንድረስላቸው

Sunday, December 1, 2013

የ132 ድርጅቶችን ማህተም በመጠቀም ሃሰተኛ ሰነድ ሲያዘጋጅ የነበረው ተከሰሰ


  •  
    የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና የኢ/ር ሃይሉ ሻውል ቲተርና የፓርቲያቸው ማህተም 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የበርካታ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ማህተም
የኦነግና የኢሜሬት ኢምባሲ ማህተሞች ተገኝተዋል

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የ132 መንግስታዊና የግል ድርጅቶችን ማህተም እንዲሁም የፖሊስ ኮሚሽነሮችን

እና  የተለያዩ ግለሠቦችን ቲተር በህገወጥ መንገድ በመያዝ ለግለሠቦች ሃሠተኛ ማስረጃዎችን ሲሠራ ነበር የተባለው

ተጠርጣሪ ላይ በፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ የቀረበው ክስ እንዲሻሻል ፍ/ቤት ብይን ሰጠ፡፡
አቃቤ ህግ በተጠርጣሪው አቶ ኮከብ ጥላሁን አማረ ላይ ሁለት ክሶችን ያቀረበ ሲሆን በመጀመሪያው ክስ ላይ የውጭ

ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የኤምባሲዎች፣ የግልና የመንግስት

ዩኒቨርስቲዎች፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የሃገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የአስተዳደሩን

የተለያዩ ቢሮዎች የክልል መንግስታት የተለያዩ መስሪያ ቤቶች የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ

ኮሚሽን  የቦሌ ኢምግሬሽን የኢትዮ ቴሌኮም እና የንግድ ሚኒስቴር የተለያዩ ቢሮዎችና ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ማህተም

እንዲሁም የፖሊስ ኮሚሽነሮችና ኢንስፔክተሮችን ጨምሮ የተለያዩ ግለሠቦችን ቲተር በተጨማሪም የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ

ጋዜጠኞች ማህበርንና የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ማህተምና የሊቀመንበሮቻቸውን ቲተር ይዞ መገኘቱን

አመልክቷል፡፡
ተከሳሹ ከመንግስት ሚኒስቴር መስርያ ቤቶችና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ባሻገር እንዲሁም አሜሪካ እና የግብፅ

ኤምባሲዎችን ማህተም፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ)፣ የአንድነት

ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ማህተሞች እና የሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ

ድርጅቶች ማህተም ይዞ መገኘቱ ተገልጿል፡፡ የኢ/ር ኃይሉ ሻውል እና የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ቲተሮችም ይዞ ተገኝቷል

ይላል የክስ ዝርዝሩ፡፡
ከግል ተቋማት መካከልም የእንይ ሪል ስቴት ማህተም፣ ብዛት ያላቸው የግል ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆችን ማህተም፣

የተለያዩ ባንኮችን ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ማህተም እንዲሁም መንግስት ወደ ግል ይዞታነት እንዲዞር በማሠብ ተደጋጋሚ

ጨረታ የሚያወጣበት የግዮን ሆቴሎች ድርጅት ማህተም ይገኙበታል፡፡
በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ላይ ተከሣሹ በድምሩ 132 ከሆኑት የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ማህተምና ቲተር እንዲሁም ህጋዊ

ሠነዶች በተጨማሪም ኮምፒውተሮች፣ ስካነር፣ ልዩ ልዩ የሃሠት ሠነዶች ተዘጋጅተው የሚገኙባቸው ሲዲዎችን ይዞ

በመገኘቱ፣ በፈፀመው የመንግስትን ወይም የመንግስት ባለስልጣናት ማህተሞችንና የህዝብ ጥቅምን የሚመለከቱ ነገሮችን

ሃሠተኛ አድርጐ ወይም አስመስሎ ለመስራት የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ይዞ መገኘት ወንጀል ተከሷል፡፡
በኮሚሽኑ አቃቤ ህግ በሁለተኛ ክስነት የቀረበውም ግለሠቡ እነዚህን ማህተሞች፣ ቲተሮችና ሠነዶች በመጠቀም ለተለያዩ

ግለሠቦች ህገ ወጥ የትምህርት ማስረጃ፣ የልደት ሠርተፊኬት፣ የተለያዩ ድጋፍ ሠጪ ደብዳቤዎች፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የስራ

ልምድ፣ የንግድ ፈቃድ፣ የመኪና ሊብሬ፣ የኤምባሲ ደብዳቤዎች እንዲሁም ፓስፖርቶች እና ሌሎች ብዛት ያላቸውን

ህገወጥ ሠነዶች እጁ እስከተያዘበት ሐምሌ 2005 ዓ.ም ድረስ አስመስሎ በማዘጋጀት፣ ተከሣሹ በፈፀመው መንግስታዊ

እና የህዝብ ጥቅምን የሚመለከቱ ሠነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ተከሷል ይላል፡፡
የመንግስት እና የግል ተቋማት ሠነዶች መስለው በተከሣሹ የተዘጋጁ ሃሠተኛ ሠነዶች በተከሣሹ መኖሪያ ቤት በተደረገው

ብርበራ መገኘታቸውም በክሱ ተመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሃሙስ እለት የዋለውና የሙስና ጉዳዮችን የሚመለከተው የከፍተኛው ፍ/ቤት  1ኛ ወንጀል ችሎትም

ቀደም ባለው ቀጠሮ ከተከሣሽ የቀረበውን የክስ መቃወሚያ እና ከአቃቤ ህግ የተሠጠውን የመቃወሚያ መልስ ከመረመረ

በኋላ በሠጠው ብይን፤ ተከሣሹ ኮሚሽኑ ክሡን የማቅረብ ስልጣን የለውም በማለት ያቀረበውን ተቃውሞ

እንዳልተቀበለው አስታውቆ፤ ከሣሽም ሊያሻሽላቸው ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ብርበራ

የተካሄደበትን ቤት አድራሻ በተመለከተ አቃቤ ህግ በተገቢው መንገድ አሟልቶ እንዲያቀርብ፣ “ሌሎች በርካታ ሃሠተኛ

ሠነዶች” ተብለው የተመለከቱ በዝርዝርና በቁጥር እንዲጠቀሱ እንዲሁም የመንግስት እና የግል ሠነዶች ተለይተው

እንዲቀርቡ ሲል ፍ/ቤቱ ብይን የሠጠ ሲሆን በአጠቃላይ አቃቤ ህግም ክሡን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ብሏል፡፡
ቀጣዩን ሂደት ለመመልከትም መዝገቡን ለታህሣስ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡