Saturday, March 8, 2014

ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ

(ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም)

gun



የተማረ ወይም የእውቀት ባለቤት እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፍል ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትግል ሰላማዊ ይሁን ወይስ በትጥቅ ትግል የሚለውን የጦፈ ክርክር ሲያደርግ ሃያ ሁለት ዓመታት ሆነው፤ ዳኛ የሌለበት ክርክር ስለሆነ የመደማመጥ ግዴታ ታይቶበት አይታወቅም፤ ስለዚህም በሁለቱ መሀከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ አያውቅም፤
አንድ፣ ከሁሉ በፊት ሰላማዊ ትግል በሀሳብ ደረጃ መሆኑንና የትጥቅ ትግል ደግሞ በተግባር መሆኑን ለይቶ ለመረዳት ችግር ሆኖ ቆይቶኣል፤ በሌላ አነጋገር ሰላማዊ ትግል በሀሳብ፣ በንግግር፣ በተለያዩ ሀሳብን ለማስለወጥ መቀስቀሻ በሚሆኑ መንገዶች ተቃውሞን መግለጽ ነው፤ በአንጻሩ የትጥቅ ትግል በጠመንጃ ወይም በጉልበት ያለውን የአገዛዝ ሥርዓት ለመለወጥ የሚደረግ ሙከራ ነው፤
ሁለት፣ እንዲህ ከሆነ በሰላማዊ ትግል ለሚያምኑ ሰዎች ያለምንም ጥርጥር በተለያዩ ዓላማዎችና ዘዴዎች ላይ መከራከርና ሀሳብን ማጥራት አስፈላጊ ነው፤ በሰላማዊ ትግል ተግባር አለ ቢባልም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ አቅዋሞችን ከማሳየት አያልፍም፤ አገዛዞች ጃዝ! ብለው ውሻና ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ሲለቁ የጉልበት ጥርስና ዱላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያርፋል፤ ጉዳት ይደርሳል፤ ሰላም ይቃወሳል፤ በሕዝብና በአገዛዙ መሀከል ቂም ይጀመራል።
ሦስት፣ የትጥቅ ትግል ደግሞ በተዋረድ በሚተላለፍ ትእዛዝ የሚፈጸም ግዴታ ነው፤ በትጥቅ ትግል ጉልበተኛ ከጉልበተኛ ጋር፣ ብረት ከብረት ጋር ይጋጠማል፤ የሰው ልጅ ለእርድ ይቀርባል፤ በሕይወታቸው በልተው ያልጠገቡ ምስኪኖች ለጥቂት ሰዎች የሥልጣን ጉጉት ይታረዳሉ፤ ያለቀባሪ በጅብና በአሞራ ይበላሉ፤ ዕድለኞች የሚባሉት እጆቻቸው፣ ወይም እግሮቻቸው ተቆርጠው፣ ወይም ዓይኖቻቸው ጠፍተው፣ ወይም ከዚህ ሁሉ የባሰ ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት የሚቀሩት ናቸው፤ ከነዚህ በሕይወት በቀሩት የጦር ጉዳተኞችና በጦርነቱ ላይ በሞቱት መሀከል የትኛው የተሻለ አንደሆነ የሞቱት ባይናገሩም ጉዳተኞቹ ይናገራሉ፤ ‹የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!› እያሉ።
አራት፣ ሁለቱ የትግል ስልት ዓይነቶች በባሕርይ የተለዩ ናቸው፤ አንዱ ሌላውን የሚደግፍ አይደለም፤ ሰላማዊ ትግል የትጥቅ ትግልን ለመደገፍ ሰላማዊ የሚለውን ስያሜ መጣል አለበት፤ የትጥቅ ትግልም ሰላማዊ ትግልን ለመደገፍ ትጥቅ የሚለውን ስያሜ መተው አለበት፤ ሰላማዊ ትግልና የትጥቅ ትግል አራማጆች ድል ቢያደርጉ ማን ወንበሩ ላይ እንደሚወጣ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ጠመንጃ የያዘው ሥልጣኑን ሲይዝ ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል! ያውም ከተፈቀደለት!
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አርበኞች ሳይቀሩ በሩ ተዘግቶባቸው ለደጅ ጥናት እንደተዳረጉ አይተናል፤ መልኩን ለወጥ ቢያደርግም ደርግን ከተፋለሙት ውስጥ በአዲስ አበባና በአስመራ ወንበሮች ላይ ሲወጡ የተሸነፉት ወይ ለወያኔ ገብረው ሎሌነት ገቡ፤ ወይም በአሜሪካ መሽገው ያቅራራሉ፤ ዘመኑ እንዳለፈባቸውም ገና አልተረዱም።
አምስት፣ ሰላማዊ ትግልና የትጥቅ ትግል ሁለቱም ብርቱ ቃል ኪዳንን ይጠይቃሉ፤የቃል ኪዳናቸው ልዩነት አንዱ እስከሞት ለመታገል፣ ሌላው ደግሞ እስከመግደልና እስከመሞት ለመታገል መሆኑ ነው፤ ለሰላማዊው ትግል ከፍተኛ መንፈሳዊ ወኔ የሚያጎናጽፈው ለመግደል ያለው ተቃውሞ ነው፤ ሕይወትን ለማልማት ሕይወትን መቅጠፍ የአስተሳሰብም የመንፈስም ጉድፍ ያለበት ሥራ ነው።
የሰላማዊ ትግል ዋናውና ቀጥተኛው ተልእኮ ሕዝብን ለሥልጣን ባለቤትነት ማብቃት ነው፤ ሥልጣንን ለመያዝ አይደለም፤ ስለዚህም ኢላማው ሕዝብ ነው፤ በሥልጣን ወንበሩ ላይ ያሉት የሰላማዊ ትግሉን የሚቃወሙት በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ ነው፤ ሰላማዊ ትግሉ የሚያተኩረው በሕዝቡ ጆሮ፣ አእምሮና ልብ ላይ ነው፤ አገዛዙ በበኩሉ ጸጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛለት ሕዝብ እውቀቱ ዳብሮ፣ መብቶቹን ሁሉ ተገንዝቦ፣ በሕግ ለሕግ እንጂ ለሰው አልገዛም በማለት ልቡ እንዳይሸፍት አፈናውንና ማነቆውን በማጠናከር እያደነቆረ ለመግዛት ይፈልጋል፤ የሰብአዊ መብቶችን የሚያስተምሩና በአገዛዙ አካላት የሚፈጸሙትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያጋልጡ ድርጅቶችን ማዳከም ወይም ማጥፋት ለአገዛዙ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፤ ኢሳት የሚባለው የቴሌቪዥንና የራድዮ ፐሮግራም ለወያኔ የውስጥ እግር እሳት የሆነበት ለዚህ ነው፡፡ በሰውነት ደረጃ ሕዝቡ መብቶቹን ሁሉ እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ፣
በዜግነት ደረጃ ሕዝቡ ለሥልጣን የሚያበቃውን የዜግነትና የፖሊቲካ መብቶች እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ፣ ሕዝቡ የሰውነትና የዜግነት መብቶቹን ተገንዝቦ በአገዛዝ ስር አልተዳደርም የማለት መንፈሳዊ እምቢተኛነት እንዲያድርበት ማድረግ፣ በግልጽ ጭቆናን የሚጠላና ለመብቶቹና ለነጻነቱ በቆራጥነት የሚቆም ሕዝብ እንዲፈጠር ማበረታታት፣ መብቶቹንና የሥልጣን ባለቤትነቱን የተረዳና ከጭቆና ጋር የተጣላ ሕዝብ በፖሊቲካ መስመር ቡድኖችን እየፈጠረ እንዲደራጅ ማድረግ፣ ያወቀና የነቃ፣ በፖሊቲካ መስመር የተደራጀና ማናቸውንም ዓይነት ጭቆና የሚጠላ ሕዝብ ለማንም ጉልበተኛ የማይንበረከክ ሕዝባዊ ኃይል እንዲሆን መጣር፣
የትጥቅ ትግል ዋናውና ቀጥተኛው ተልእኮ በሥልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ አውርዶ ወንበሩን ለራሱ ለመውሰድ ነው፤ ይህንን ሲያደርግ ሕዝቡን ወደጎን ትቶ ወይም ዘልሎ ነው፤ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ በጠመንጃ ሥልጣን የሚይዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥልጣኑን ለሕዝብ እናስረክባለን፤ ትክክለኛ ምርጫ እናካሂዳለን በማለት ሕዝቡን በተስፋና በጠመንጃ ይዞ ነው፤ ነገር ግን ሥልጣንን ሕዝብ ለፈቀደው አስረክበው ከቤተ መንግሥት ሲወጡ አናይም፤ ሲሸሹ ወይም ሬሳቸው ሲወጣ እንጂ።
ብዙውን ጊዜ የማይታሰብ ወይም ብዙዎች የሚዘነጉት የሁለቱ ትግሎች የገንዘብ ወጪ በጣም ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ነው፤ ሰላማዊ ትግል በሕይወትም፣ በንብረትም፣ በመሣሪያም በዝግጅትም የሚያስከፍለው ዋጋ ከትጥቅ ትግል ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነው።
ስለዚህም በሁለቱ በተለያዩ ስልቶች አራማጆች መሀከል የሚደረግ ክርክር ምን ዓይነት ነው? የሰላማዊው የመጀመሪያ ደረጃ ኢላማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የትጥቅ ትግል የመጀመሪያ ደረጃ ኢላማው የወያኔ አገዛዝ ነው፤ በሌላ አነጋገር በሰላማዊ ትግል ሕዝቡ በሰላማዊ ትግል ትንሽም ቢሆን የነጻነትን አድማስ ለማስፋት እንዲችል ድፍረትን በማስተማር በኩል የማይናቅ አስተዋጽኦ ቢያደርግም አገዛዙን የመነቅነቅ ኃይል ገና አላዳበረም፤ አንድም ውጤት አላሳየም፤ የትጥቅ ትግሉ ከፉከራና ከሽለላ እስካሁንም አልወጣም፤ የሰላማዊ ትግል ዓላማ ሕዝቡ መብቶቹን እንዲያውቅ ለማንቃትና ለመብቶቹ እንዲታገል የሚያስችለውን ብቃት ለማስጨበጥ ነው፤ ስለዚህም ዘዴው በሕዝቡ ላይ ነው፤ የትጥቅ ትግሉ ዘዴ አገዛዙን በጉልበት ገልብጦ በዚያው ባልተለወጠ ሕዝብ ላይ ሌላ አገዛዝ ለመመሥረት ነው።
በኢትዮጵያ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ሁሉ የቆሙበትንና የቆሙለትን ዓላማና ዘዴ በግልጽ ተገንዝበው ካልተሰለፉ በተንፈራጠጠ አስተሳሰብ የተባበረ ተግባር ሊገኝ አይችልም።
http://www.goolgule.com/non-violent-or-armed-struggle/

እነዚህ ሰዎች የሚናገሩትንም አያውቁም (ሲሳይ አባተ፣ ከአዲስ አበባ)

“ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት” (ጠቅላይ አሽከር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከደቂቃዎች በፊት የተናገረው)

ታጋይ አለማየሁ አቶምሳ
ጓድ አለማየሁ አቶምሳ
ለትግሉ መስዋእት የሆኑት ታጋይ አለማየሁ አቶምሳ
(የማን አስከሬን ተሸፍኖ የማን ሊገለጥ?)
የሕወሓት መንግሥት በአገዛዝ ዘመኑ ከተሳኩለት ነገሮች አንዱና ዋነኛው የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን ባማረ ሁኔታ ማከናወን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ውስጥ ለምሳሌ የሀየሎም አርአያ፣ የጭራቁ መለስ ዜናዊና የትዳር አፋቹ የወንበዴው ጳጳስ የጳውሎስ ደማቅ የልቅሶና የቀብር ሥነ ሥርዓቶች በዋቢነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የጥላሁን ገሠሠን ያላካተትኩት የሕዝብና የሀገር ልቅሶና ሀዘን ስለነበረ ነው፡፡ እንጂ በሀገር ደረጃ ካየነው የጥላሁንን የመሰለ ደማቅ ልባዊ ሀዘን የተገለጸበት ልቅሶ ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ በጥላሁን ቀብር ሕዝብ በዐዋጅና በማባበያ ወጥቶ እንዲለቀስ አልተደረገም፡፡ በጥላሁን ቀብር የሀገር ሀብት ከካዝና እየተመዘረጠ ከናቴራና ኮፍያ እየተገዛ ፖስተርም እየተለጠፈ፣ የውሎ አበልም እየተከፈለ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብና ማቴሪያል እንዲባክን አልተደረገም፡፡ በጥላሁን ቀብር ሕዝብ በግዳጅ እንዲያለቅስና ከሥራ እየቀረ ከአንጀቱ ሳይሆን ከአንገቱ እንዲያላዝን አልተደረገም፡፡ የሰሜን ኮርያን ልቅሶ የሚያስንቅ የግዳጅ ልቅሶ ያዬነው በመለስ ዜናዊ ቀብር ነው – በሀፍረት የለሹ ወያኔ አስገዳጅነት፡፡Former president of the Oromia region, Ato Alemayehu Atomsa
ዛሬ ደግሞ ግራ የተጋባ ልቅሶ እያየን ነው፡፡ የሰዎች መሞት በውነቱ ያሳዝናል፡፡ አቶ አለማየሁ አቶምሳ ሞቷል – በሰውነቱ ከልብ እናዝናለን፡፡ በሆዳምነቱና ከታሪካዊ ጠላቶቹ ጋር ተባብሮ ለሀገር መቀበር በመታገሉም እንዲሁ እናዝንበታለን፤ ለማንኛውም ፈጣሪ ነፍሱን ይማር – አፈሩንም ገለባ ያድርግለት፡፡ ለልጆቹና መላ ቤተሰቡ አጽናኝ መላእክትን ይዘዝላቸው፡፡ በመሠረቱ ሰውዬው የሞተው ዛሬ አይደለም፡፡ የሞተው የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ናዝሬት ውስጥ ታካሄደ በተባለ የኦህዴድ ጉባኤ ላይ ጓደኞቹ ይሁኑ ሌላ ወገን በሚጠጣው ይሁን በሚበላው ነገር ላይ መርዝ በሰጡት ጊዜ ነው፡፡ ወያኔ ራሱ ገድሎ  ሙሾ ማውረድን የተካነበት በመሆኑ ራሱ የገደለውን አለማየሁ በድምቀት እየሸኘው ነው፡፡ ዕንቆቅልሹ ወያኔ ክንፈ የሚባለውን የደህንነት ኃላፊውን ባስገደለበት ወቅት እንዴት በመሰለ ሁኔታ ቁንጮው ጭራቅ መለስ እያለቀሰ እንደሸኘው የምናስታውሰው ነው፡፡ እስስቶች ናቸው፡፡
የዛሬው ግራ አጋቢ የልቅሶ ሥነ ሥርዓት ምን ይመስላል? ሬሣው በዓለም እንደሚታወቀው ከአንገቱ በላይ እንዲታይ አልተደረገም፡፡ በኔ ግምት ይህ ያልሆነበት ምክንያት የፈራረሰው የመለስ አስከሬን ተሸፍኖ እንደተሸኘ ሁሉ ይህንንም ሰውዬ የእርሱ መናጆ በማድረግ የመለስ አስከሬን ሁኔታ እንዳይታወስና መነጋገሪያ እንዳይሆን ነው፡፡ አስከሬንን አለማሳየት ባህላቸው ነው እንዲባልና የመለስን መፈራረስ ለማስረሳት የፈለጉ ይመስለኛል፡፡ እንጂ የአለማየሁ ሰውነት እንደመለስ የፈራረስ አይመስለኝም፡፡ አንደኛ ነገር ይህ ሰው የሞተው ሰሞኑን ስብሰባ እያካሄደ በነበረበት ጊዜ ድንገት ተስለምልሞ በመውደቅና ከዚያም ወዲያውኑ ወደውጪ ተልኮ የህክምና ርዳታ ተደርጎለት ነው፡፡ ስለዚህ ጭንቅላቱም ሆነ ፊቱ ገና ‹ፍረሽ› ነው፡፡ ሁለተኛ ከሞተም በኋላ እንደመለስ ለወራት አልተደበቀም፤ የተፋጠነ የቀብር ሥነ ሥርዓት ነው እየተደረገለት ያለው፡፡ በዚህች በቀብር ሥርዓት እንኳን ከሕወሓት ውጪ ያሉ ሌሎች ወገኖች መወሰን አልቻሉም ማለት ነው፡፡
ይህ ሀዘን ክልላዊ እንጂ ፌዴራላዊ አይደለም፡፡ የፕሮቶኮል ጉዳይ ያነጋግራል፡፡ ባንዴራ ዝቅ ተደርጎ መውለብለብ ያለበት ሰውዬው ይመራው ነበር በሚባለው “ክልላዊ መንግሥት” እንጂ በመላዋ ኢትዮጵያ መሆን አልነበረበትም፡፡ ስህተት ነው፡፡ አወሳሰኑ ራሱም ስህተት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም የጥቂት ግለሰቦች ውሳኔ ይመስላል፡፡ የተሰበሰበ የፓርላማ ጉባኤ ሳይኖር ጥቂት ሽፍቶች እንደፈለጉ የሚያዙበትና የሚናዝዙበት መንግሥት ያለን ለመሆናችን አንደኛው ዋቢ ነው፡፡ ለማስመሰልም እንኳን አልቻሉበትም፡፡ ለወትሮው የማስመሰል ሁኔታ ይታይ ነበር፤ የዐይን ጥቅሻ ብቻ እያዬ የሚያጨበጭብና በረጃጅም ዲስኩሮች ወቅት ደግሞ እያዛጋና እያንጎላጀ እንቅልፉን የሚለጥጥ ፓርላማ ያለን እኛ ብቻ ነን – ዕድሜ ለወያኔ፡፡ አሁን አሁን የነበረው ጥቂት የማስመሰል ትያትር በጭራሽ ጠፍቷል፡፡ ከአንድ ጎሬ ውስጥ የተደበቀ ሥውር መንግሥት ሳይኖር አይቀርም፡፡ ያ ሥውር ወያኔዊ ኃይል የመንግሥት ወንበሮች ላይ በጎለታቸው እነኃይለማርያምንና ተሾመን የመሳሰሉ ሆዳሞች አማካይነት በስልክ በሚተላለፍ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሀገሪቱን እንደፈለገ መንዳቱን ቀጥሏል፡፡
ሬሣው መልበስ ያለበት የክልሉን ባንዴራ መሆን ሲገባው በአንድ በኩል የወያኔን የኢትዮጵያ ባዴራ አልብሰው በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮምያ የሚባለውን አዲስ ወያኔ ሠራሽ ሀገር ባንዴራ አልብሰውታል፡፡ አስከሬኑ የሚመስለው አስከሬን ሳይሆን  የተለያዩ ቀለማት ባላቸው ጨርቃ ጨርቆች ያሸበረቀ የጠንቋይ ቤት የመጠንቆያ ክፍል ነው፡፡ ቋንቋቸው ደግሞ የበለጠ ግራ ያጋባል፡፡
እነዚህ ሰዎች የቃላት አጠቃቀማቸው ራሱ አስገራሚ ነው፡፡ ጭራቁ መለስ ሲሞት ደደቧ ሚስቱ “መለስ ተሰዋ” ብላ በሀዘናችን መሃል አሳቀችን፡፡ አንድ ሰው ተሰዋ የሚባለው በጦርነት ላይ ሲሞት ወይም ለግዳጅ በሄደበት ሳይመለስ ሲቀርና ሕይወቱ በዚያው ሲያልፍ ነው፡፡ እንጂ በሰላም ሀገር ታሞ የሞተን ሰው ተሰዋ ማለት የቋንቋ ችግርን ከማሳየቱ በስተቀር ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ በውነቱ ማይምነት ነው፡፡ በሌላ ወገንም የመንግሥት ሥልጣን ከያዙ ከ23 ዓመታት በኋላ “ታጋይ” እያሉ ሰዎቻቸውን ሲጠሩ ስንሰማ ምን ማለት እንደፈለጉ አይገባንምና መቸገራችን አይቀርም፡፡ ታጋይ የሚባለው በትግል ወቅት ነው፡፡ አሁን ባለሥልጣን ሊያውም የአሜባን ቅርፅ ይዞ ከኤርትራ በስተቀር በመላዋ ኢትዮጵያ እዚያና እዚህ ጉች ጉች ያለ የተንጣለለ የኦሮሚያን ክልላዊ መንግሥት “ከነሙሉ ክብሩና ማዕረጉ በነፃነት ሲያስተዳድር” የነበረ ዕንቁ ዜጋ! አይ ወያኔ፡፡ ስንቱን ነው እያሳየን የሚገኘው፡፡ ይብላኝልህ አንተ ታሪክ የምትባል ሀገራዊ ደደብ መዝገብ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሀገር ከነዚህ መዥገሮችና ነቀዞች ነፃ ስትወጣ ሀፍረትህ ምንኛ የበረታ ይሆን?
ደንቆሮው ኃይለማርያም ደግሞ ያሳዝነኛል፡፡ የተሰጠውን እንዳነበበ “የሥልጣን ጊዜው”ን ሊጨርስ ነው፡፡ ምን ዓይነቱ ገልቱ ሰው ነው? እሱም ዛሬ ልክ እንደዚያች የመርገምት ፍሬ እንደአዜብ ጎላ አለማየሁን ‹መስዋእት የሆነ ታጋይ› ብሎት ዐረፈው፡፡ የት ዐውደ ውጊያ ሲፋለም ይሆን አቶ አለማየሁ የተሰዋው? በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡ ለመለስ የተናገረውን ትንሽ ለወጥ አድርገው ጽፈው ሰጡትና “ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለሰማዕታት” ብሎ ተናገረ፤ አለማየሁም ሰማዕት መሆኑ ነው (ሰማዕት የሚባለውንም ቃል ከሃይማኖታዊው ዐውድ አውጥተን ለዓለማዊ ፍጆታ ካዋልነው በትግል ወቅት የተሰዋ ማለት እንጂ በአገር አማን በበሽታ የሚነጠቅን ዜጋ ለማመልከት አይደለም)፡፡ ለውጡ በፊተኛው ጊዜ ይህን መፈክር የተናገረው ለመለስ ነበር፡፡ አሁን ግን ለሞቱትና ለመሞት ለተዘጋጁት ለነሳሞራና ሥዩም እንዲሁም ለሌሎቹም ተራቸውን እየተጠባበቁ ላሉ ሟቾች ጭምር ነው፡፡ የወደፊቱ ጊዜ የወያኔዎች መረፍረፊያ ጊዜ ነው፡፡ (ኢቲቪን አሁን ስመለከት ካህናት ጸሎተ ፍትሃት እያደረጉ ነው፡፡ የታደሉ ወያኔዎች ናቸው ጃል! ቤተ ክርስቲያንን ሲፈልጉ ያጠፏታል ሲፈልጉም የማስመሰያ  ፍትሃት እንድታደርግላቸው ያስደርጓታል፤ ሁሉ በጃቸው ሁሉ በደጃቸው – ማን ሃይ ሊላቸው፡፡ አለማየሁ እየተፈታ ነው፤ ሊያውም ከስንት አድባራት በልዩ ትዕዛዝ በተጠሩ ጳጳሳትና ካህናት፡፡ ይሄኔ ተቃዋሚ ቢሞት ኖሮ መንግሥትም ቤተ ክርስቲያንም ያን የሞተ ሰው እንደሥጋት በመቁጠር የውሻ ያህልም ክብር ባልሰጡት፡፡ ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያንና ምን ዓይነት መንግሥት ናቸው ያሉን? ያሉ የሚመስሉ ግን የሌሉ፡፡ ለሞተም የሚያዳሉና ሙታንንም የሚከፋፍሉ አስገራሚ ጉዶች!)…
ብዕር ካነሳሁ አይቀር በእግረ መንገድ አንድ ሌላ ጉዳይ ላንሳ መሰለኝ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ምን እየነካቸው ነው? ትናንት አንድ መጣጥፋቸውን ከዘሀበሻ ድረገፅ ላይ አነበብኩ፡፡ ጽሑፋቸው ቆንጆ ነው፡፡ እንደሁልጊዜው ሁሉ በፍቅር ነው ያነበብኩት፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ አዝንባቸዋለሁ፡፡ ግራ የገባቸውም ይመስለኛል፡፡ ግራ ተጋብተውም እኔንም ግራ ያጋቡኛል፡፡ ምን ያለ ግራ አጋቢ ዘመን ላይ ደረስን እባካችሁ!
ግንቦት ሰባትን ለምን ትኩር ጥምድ አድርገው እንደያዙት አልገባህ ብሎኛል፡፡ እርሳቸው እደግፋዋለሁ በሚሉት ሰላማዊ የትግል ሥልት የኢትዮጵያን ሕዝብ ነፃ ማውጣት እንደማይቻል የተረዱ አልመሰለኝም፡፡ የትጥቅ ትግልን እንዳናናቁና ሕዝቡ ለባርነት እንደተጋለጠ በሰልፍና በወረቀት ላይ ብቻ ተወስኖ እየተጯጯኸ ዕድሜውን እንዲጨረስ ይፈልጋሉ መሰለኝ፡፡ ምን ማለታቸው ነው? “ያውጡብሽ እምቢ፤ ያግቡብሽ እምቢ” ይባላል እንደዚህ ያለ የማይፈታ ዕንቆቅልሽ ሲገጥም፡፡
መካሪ ማጣት ነው፡፡ ወይም ሰውን መናቅ ነው፡፡ እንደ አካሄድ ትልቅነት ጥሩ ነው፡፡ አባትነት መልካም ነው፡፡ ታዋቂነት ደግ ነው፡፡ መማር መመራመር ውብ ነው፡፡ በሥራ ጉዳይ ሀገርን ተዟዙሮ መቃኘትና ለትውልድ የሚተርፍ ምሁራዊ ትሩፋት ማስገኘት ብዙዎች ተመኝተው የማያገኙት መታደል ነው፡፡ በነዚህ ሁሉ ፕሮፌሰሩን አከብራለሁ፤ እወዳቸውማለሁ፡፡ ብዙዎች ወገኖቼ እንደሚቸሯቸው ያለ እውነተኛ ፍቅር እኔም ለእኚህ ሀገራዊ ቅርስ አባት አለኝ፡፡ ይሁንና ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ለሀገር አንዳች ነገር እንሠራለን ብለው ገንዘባቸውን፣ ዕድሜያቸውን፣ ጊዜያቸውንና መላ ትኩረታቸውን የሚያውሉ ወገኖችን ማወክ ተገቢና ወቅታዊም አልመስለኝም፡፡ አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው፡፡ አዙሮ ማየት ደግሞ በትልቅና በትንሽ ስብዕና የሚወሰን አይደለም፡፡ ስህተትን መሥራት በሰውነት ደረጃ የሚገታ እንዳልሆነ ሁሉ ከስህተት ጎዳና ለመውጣት መጣርና ራስን ለመፈተሸ ጊዜና አቅል መግዛትም ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ እናም ክቡር ፕሮፌሰር ነገሬን በጥሞና እንደሚረዱልኝ እገምታለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን ሁኔታ የተገነዘቡ አልመሰለኝም፡፡ እርሳቸው በፋክት መጽሔት የፈለጉትን ስለተነፈሱና በጡረታም ሆነ በሌላ መንገድ በሚያገኙት (መጠነኛ) ገንዘብ ሕይወታቸውን ከብዙዎች ዜጎች በተሻለ ሁኔታ ስለመሩ ሕዝቡ ተመችቶታል ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን የባርነት ሰቆቃ መረዳት አለባቸው፡፡ ችግሩ የአምባገነንነትና የዴሞክራሲ ጉዳይ አይደለም፡፡ በነፕሮፌሰር ቀለል ተደርጎ እንደሚገለጠው የዴሞክራሲ ዕጦትና የአምባገነን መንግሥት ጉዳይ የሀገራችን አንገብጋቢ ችግር አይደለም፡፡ ይሄን መሰሉ የነፕሮፌሰር ገለጣ ቅንጦት ነው – እዬዬም ሲደላ ነው ወገኖቼ፡፡ የኛ ችግር በነፃነትና በባርነት መካከል የሚዋልል የጠበበ አማራጭ ነው፡፡ ነፃነቱ ከተገኘ በኋላ ስለአምባገነን መንግሥትም ሆነ ግለሰቦች መነጋገር ይቻላል፡፡ አሁን ግን በአፓርታይድና በቅኝ ግዛት ውስጥ በመከራ ሥጋ በመከራ ነፍስ ውስጥ ተጣብቀው እየኖሩ ስለወደፊት አምባገነን ሥርዓት መነጋገር በትንሹ ቂልነት ነው፡፡ አለፍ ሲልም ዕብደትና ወፈፌነት ነው፡፡ አሁን በሌለ ሥልጣን፣ ባልተገኘ ምቹ ሀገራዊ የሥልጣን አያያዝ ሁኔታ ገና ለገና ግንቦት ሰባት ሥልጣን ይይዝና ጭቆናን ያራምድ ይሆናል ብሎ ሕዝብን ማደናገርና ማደናበር ከሀበሻዊ የምቀኝነት አባዜ ነጻ አለመውጣትን እንጂ ቀናነትን የተላበሰ ሀገራዊ መቆርቆርን አያመለክትም – It is really a far-fetched and more of imaginary concern for the time being. ትግላችን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አቢይ ትኩረት  ይህን በስብሶ ያበሰበሰንንና ተረካቢ ትውልድ ሳይቀር እንዳይኖረን እያደረገን የሚገኘውን የዘረኝነት ሥርዓት አስወግደን ቢያንስ ቢንስ ሁላችንንም በእኩል የሚጨቁን ወይም በእኩል የሚገድል ሥርዓት ማምጣት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ትግል ቀላል ነው፡፡ የራሳችንን ጨቋኞች ካገኘን በኋላ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ጉዜ በግማሽ አጠረ እንደማለት ነው፡፡ አሁን ግን በቅዠት ዓለም እየዋኙ እንደዶክኪሾት በምናብም በእውንም ከሚያስቡትና ከሚያገኙት “ጠላት” ጋር መላተም የህመም ካልሆነ የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ ያስተዛዝባልም፡፡ እንዴ፤ ልብ እንግዛ እንጂ፡፡ እስከመቼ አንድ ዓይነት አንቺ ሆዬ ቅኝት እንዘፍናለን? “ሦስተኛውን” ዐይናችንን እንግለጥ፡፡
አንዲት ሴት እንዲህ አለች አሉ – ለባሏ፡፡ “ስንደዶ ቀጭቼ፣ አከርማ ቆረጬ ወስከምቢያ ሰፍቼ እሸጥና አንዲት ላም እገዛለሁ፡፡ ላሚቱን አስጠቅቼ አርግዛ ስትወልድ ጥጃዋን እዚያች እግገኗ ላይ አስራታለሁ፡፡” ሞኙ ባል ደግሞ “የለም፣ የለም፤ ምን ማለትሽ ነው? እግገኑ ላይማ አናስርም፤ ሰው ይገባል ይወጣል፡፡ የሰው ዐይን ደግሞ እንኳንስ ጥጃ ድንጋይ ይሰብራል፡፡ ስለዚህ ጓዳ ውስጥ እንጂ እዚህ አናስራትም፡፡”  ሚስትዮዋም ቀጠለች፡- “ምን ማለትህ ነው፤ ጓዳ ውስጥማ አናስርም፤ እዚሁ ነው የምናስራት፡፡ ደግሞስ አንተን ምን ጥልቅ አደረገህ? ለፍቼ ደክሜ ላሟን እምገዛና አሰጠቅቼ ጥጃዋን እማስወልድ እኔ፡፡ …” ክርክሩ ጦፈ፤ ወደ ከፍተኛ ግጭትም አመራና ባልዮው አጠገቡ የነበረ የቡና ዘነዘና አንስቶ አናቷን በርቅሶ ገደላት – ነፍሷን ይማር፡፡ ይታያችሁ – በላም አለኝ በሰማይ ምኑም ምኑም በሌለበት ሁኔታ በባዶ ሜዳ ተጨቃጨቁና ተገዳደሉ፡፡ የብዙ ሰዎች ችግር ይህን ይመስላል፡፡ የሌለ ሥጋት እየፈጠሩ በማውራትና በማስወራት ከፊት ለፊት የተጋረጠብንን ትልቅ ተራራና አለት በጋራና በቻልነው መንገድ ሁሉ ገፍተን እንዳንጥል ደንቃራ እየሆኑብን ነው፡፡ የሚሆነው ሁሉ ከመሆን ባይዘልም እነዚህን መሰል የ“ሳይቸግር ጤፍ ብድር” ዜጎች ወደየኅሊናቸው እንዲመለሱ እንጸልይ፡፡ እንቅፋትነታቸው ግልጽ ነውና፡፡
ግንቦት ሰባት ስህተት ሊሠራ ይችላል፤ “እንከን የለሽ ነው፡፡ ምሉዕ በኩልሄም ነው” የሚል እምነትም ሆነ አስተሳሰብ የለኝም – በሰዎች ስለሰዎች የሚመራ በመሆኑ ፍጹም ነው ማት አንችልም፡፡ ግን ከስህተታቸው እየተማሩ ወደ መልም ዘለቄታ የሚያመሩ ይመስሉኛል፡፡ (አንዲት ቀልድ ቢጤ ጣል ላድርግ፤ አንድ ሰው የሚጋልበው ፈረስ ዐመለኛ ኖሮ ተቸግሯል፡፡ አልታዘዝለት ብሎ ገደል ሊከተው ደረሰ፡፡ ተመልካቾችም አንዳቸው “አንገቱን ያዘው”፣ ሌላኛቸው ልጓሙን ጨብጠው” ደግሞም ሌላኛቸው “እርካቡን እርገጠው” ወዘተ. ሲሉ የሰማቸው ችግር ውስጥ የሚገኝ ሰውዬ “አይ መሬት ያለ ሰው!” አለ አይባላል፡፡ ልክ ነው – ያልተነካ ግልግል እንዳለማወቁ ቁጭ ብሎ ወሬ የሚጠርቅ የኔ ዓይነቱ ሥራ ፈት ሰው የሚለው አያጣምና ብዙ ሊፈላሰፍ በዚያ ፍልስፍናውም ብዙ ሊሳሳት ይችላል፡፡ ተሳስቶ ከማሳሳት ይሰውረን ወገኖቼ፡፡) በመሠረቱ እኔ የግንቦት ሰባት አባልም ሆነ አቦካቶው አይደለሁም፡፡ ግን አዳሜ እየተነሣ የጭቃ ጅራፉን ሲለጥፍበት ያሳዝነኛል – ብዙ የምታዘበው ነገር ስላለ ነው እንደዚህ በምሬት የምናገረው፡፡ በእውነቱ የማንሠራና የማናሠራ ዜጎች ብዙ ነን፡፡ ባሕርያችን ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግር ክርት ዐመል ያለን ብዙ ነን፤ ምን እንደሚሻለን አላውቅም፡፡ አለቃ ገ/ሃና “ለቦና ጥጃ ውስ ምን አነሰው” አሉ አሉ፡፡ እናስ ስንትና ስንት የሚወራበትና የሚጨነቁለት ችግር እያለ አሁን በምትወዱት ሞት ይሁንባችሁና ግንቦት ሰባት ለኢትዮጵያ ከወያኔ የበለጠ ራስ ምታት ሆኖ ነው ይህን ያህል ሰዎች እንቅልፍ አጥተውለት ከወያኔ ባልተናነሰ ለውድመቱ የሚቋምጡለት? ከማንም ጋር ይሥራ – የሚያዋጣውን የሚያውቅ ራሱ ነው፡፡ ስህተቱን መጠቆም፣ ማረም፣ ማስተማር፣ ማስተካከልና በተቻለ አቅም ሁሉ መርዳት ሲገባ ቤተስኪያን እንደገባች ውሻ ችው ችው ማለት ከአንድ ጤናማ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይጠበቅም፤ ሁል ጊዜ በምቀኝነት አባዜ መጠመድም ተገቢ አይደለም፡፡ ትንሽዬ ዝናና ስመጥርነት ስላገኘ ብቻ ባለን የቆዬ የምቀኝነት ባህል እየታወርን ሳቢን ለመግረፍ መጣደፍ አግባብ አይደለምና አንዳንዶቻችን ከምንጓዝበት እርምጥምጥ መንገድ በአፋጣኝ እንውጣ፡፡ ቢያንስ ዝም እንበል – ቆርጠን እየቀጠልን በምንፈጥራቸው ስድቦች ሰድበን ለሰዳቢ አንስጠው – “የምታሸንፈውን ምታ” ቢሉት ወደ ሚስቱ እንደሮጠው ፈሪ ባል ወያኔ ሲያቅተን በዚህ የትናንት ድርጅት አንረባረብ፤ ባይሆን ወፌ ቆመች እንበለውና የበኩሉን እንዲጥር እናግዘው፡፡ ከፈራነውም አሁኑኑ በእማኞች ፊት እናስፈርመውና ሥልጣኑን ከወያኔ እንደቀማ – ህልሙ ተሳክቶለት መቀማት ከቻለ – ሕዝብ ለሚመርጠው ሰው እንዲያስረክብ ቃል እናስገባው፡፡ በበኩሌ ምነው ግንቦት ሰባት በተሳካለትና በኢትዮጵያዊ አምባገነን በተገዛሁ እላለሁ፡፡ የራሴን አምባገነን መታገል እመርጣለሁ በባርነት የአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ ከሰውነት በታች ሆኜ ከምኖር፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ግንቦት ሰባት በሁኔታዎች አስገዳጅነት ሊሠራቸው በሚችላቸው ስህተቶች ምክንያት በጭካኔና በኢዴሞክራሲያዊነት ከወያኔ ጋር መፈረጅ የጤና አይመስለኝም፡፡ በእግረ መንገድም ኢሳትን ከግንቦት ሰባት ጋር እያያያዙ ይህን የሕዝብ ብሶት መተንፈሻ ጣቢያ እንዲጠላ የማድረግ ዘመቻ አሁኑኑ ማቆም የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ኢሳትን ሲዘልፉትና ሲሰድቡት ስሰማ እነዚህ ሰዎች በተጠናወታቸው ሥነ ልቦናዊ ደዌ አዝናለሁ፡፡ ከወያኔ ምንዳ ተቀብለው ይሆን ብዬም ለማሰብ እገደዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ዘመን ክፉኛ የተከፋፈልንበትና በጦዘ የርስ በርስ ቅራኔ የገባንበት ዘመን ይኖር ይሆን? ለማንኛውም ስንናገርና ስንጽፍ ከአንዴ በላይ አሰብ እያደረግን ቢሆን መልካም ነው፡፡ ወደ ቀብር ልሄድ ነው –  ቻዎ፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11343/

Thursday, February 27, 2014

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና …

(ይድነቃቸው ከበደ)

ealines


“የኢትዮጵያ ሃየር መንግድ ለአፍሪካ ኩራት ነው” ሲባል ከቃላት መፈክርነት ባለፈ የአውነትም ኩራት ስለመሆኑ ጥርጣሪ  የሚያድርባቸው ዜጎች እንደሚኖሮ እገምታለው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንግድ በረዥም ታሪኩ ውስጥ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በአንፃራዊነት በተቋሙ ውስጥ ስማቸው እጅግ የገነነ ብቁ አብራሪዎች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች (ግራውንድ ቴክኒሻን) እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በአብዛኛው በኢትዮጵያዊያን የተሞላ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአፍሪካ ኩራት ለመባል የበቃው፡፡ ይህ ኩራት እና አድናቆት ከታላቁ አፍሪካዊ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ጀምሮ ጥቂት በማይባሉ አፍሪካዊያን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሎሜ፣ማላዊ እና ቶጎ በመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ አክሲዮን ሼር በመግዛት እያስተዳደረ እና እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ የአፍሪካ አገር ተወላጆች በአብራሪነት እና በቲክኒሻንነት እያሰለጠነ ይገኛል፡፡ ይህ ደገሞ አየር መንገዱ በበለጠ በአፍሪካ እና በተቀሩት የዓላም አገራት ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስችሉት መልካም ተግባራቶች ናቸው፡፡ እንዲ አይነቱ ለውጥ እና እድገት ለአገር ኩራት ስለመሆኑ ጥርጣሪ የሚያሳድር አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ የተገለፁት የአየር መንገዳችን መልካም ስራዎች በተቋሙ ውስጥ ለሚታዩ የአስተዳደር ችግሮች እና አየር መንገዱ ሊደርስበት ይገባው ለነበረ የእድገት ደረጃ አለመድረስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እና መሰል አሳቦችን አንስቶ ለመወያየት ብልጭ ድርግም የሚለው የአየር መንገዳችን እድገት የአሳብ ፍጭት ለማድረግ የሚገድብ አይደለም፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የራሱ የሆነ ድንቅ ታሪክ ያለው ነው፡፡ የአየር ኃይል ካፒቴኖቻችን እንደ ንስር አሞራ ከሰማይ ወደ ምድር በሚገርም ብቃት በመብረር ጠላትን እና የጠላት ሠፈርን አመድ በማድረግ የሚታወቁ ናቸው፡፡ እንዲህ አይነቱ ግርማ ሞገስ ያለው የአገር ኩራት የሆነው ተቋም እና ተቋሙ ያፈራቸው ባለሙያዎች በወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ቀጥተኛ ትዕዛዝ ለመፍረስ በቃ እንጂ፡፡ ተቋማትን አፍርሶ እንደ አዲስ መገንባት አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስርዓቱ ዋንኛ መገለጫ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉ ነገር እንደአዲስ የመጀመር መርዘማ የሆነ የኋላ ጉዞ ሙጥኝ ብለው የተያያዙት፡፡ የሰዎቹ አደገኝነት የሚጀምረው ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደ አገር መታየት ከጀመረች መቶ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ነው ብለው የነገሩን ዕለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያን አየር ኃይል በማፍረስ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአዲስ መልክ እንዲቋቋም ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት እጅግ በጣም ድንቅ የሆኑ የአየር ኃይል ካፒቴኖቻችን ከአገር ለመሰደድ ተገደዋል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የአንድ ሳንቲም ግልባጭ የሆኑት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና አየር ኃይል ካፒቴኖቻችን ሽሽትና ምክንያት እንዲሁም ውጤት በአጭሩ ለማየት ከላይ የቀረበው አሳብ እንደመንደርደሪያን ሊያገለግል ይችላል፡፡
በአብዛኛው የአየር መንገድ ሠራተኞች በተለይ በአብራሪዎች እና በቴክኒሻኖች የሚነሳው ጥያቄ አስተዳደራዊ በደሎች ናቸው፡፡ እነዘህም ተመጣጣኝ የደሞዝ ክፍያ፣የሰራ እድገት እና የስራ ዝውውርን የሚመለከት ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ አብራሪ የወር ደሞዙ ትልቁ 7 ሺህ ዶላር ሲሆን ( ይህ የገቢ ግብር ጭምር የሚያካትት ነው) ለውጭ አገራት ዜጎች ግን ላቅ እንደሚል ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ሲታይ የብሩ መጠን ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ክፍያው የሚፈፀመው የኢትዮጵያ አየር መንገዱ አለም አቀፍ እንደመሆኑ መጠን አለም አቀፍ ደረጃ በጠበቀ መልኩ ነው መሆን ያለበት፤ ለዚህም ነው ወራዊ ደሞዝ በብር ሳይሆን በዶላር የሚከፈለው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ነው የአየር መንገድ ካፒቴኖች ለስራቸው ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚጠይቁት፡፡
ይሁን እንጂ ሠራተኞች እንደሚናገሩት አስተዳደሩ ለጥያቂያቸው ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ‹‹ስራውን መልቀቅ ትችላላችሁ›› ነው የሚባሉት፡፡ በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዋና እና ምክትል አብራሪዎች ከአገር በመውጣት በተለያየ አገር የሥራ ብቃታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ነገሩን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ እንዲረዳ ይህን መመልከት በቂ ይመስለኛል ባለፈው ሳምንት ተጠለፈ የተባለው ኤጥ 702 አውሮፕላን ዋና አብራሪ የነበሩት ግለሰብ ኣኢር እታሊአ (ኣል-እታኢአ) በተባለ የአየር መንገድ ድርጅት ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተው በውር 3 ሺህ ዶላር እየተከፈላቸው በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እኚህ ግለሰብ በኢትዮጵያ አየር መንግድ ውስጥ 14 ሺህ ዶላር እየተከፈላቸው ይገኛል ፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ሎሜ፣ ቶጎ እና ማላዊ እንዲሁም በተቀሩት ማህከላዊ ምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ ባለው ከፍተኛ የሼር መጠን የሚያንቀሳቅሳቸው እና የሚያስተዳድራቸው የአየር መንገድ ድርጅቶች አሉ፡፡ በእነዚህ የአየር መንገድ ድርጅቶች ውስጥ በቴክኒሻንነት የሚያገለግሉ ማንኛው የውጪ አገር ዜጋ ከ 3 እስከ 5 ሺህ ዶላር ክፍያ ያገኛል፡፡ ነገር ግን ተመሳሳይ የት/ት እና የስራ ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊ ቴክኒሻን የሚከፈለው 1 ሺህ ዶላር የማይሞላ ነው፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርጅት ውስጥ ሌላው በሠራተኞች ዘንድ ትልቅ ቅሬታ ሆኖ የሚነሳው የስራ ዝውውር እና እድገት ግልፅነት እና ተጠያቂነት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ወደ ተሻለ የስራ ቦታ ለመዘዋወር እና የደረጃ እድገት ለማግኘት በአብዛኛው በቅርብ አለቃ መላካም ፍቃድ ላይ የተመሰረተ እንጂ የሥራ ውጤትን ግብ ያደረገ አይደለም፡፡ ይህም ማለት በአየር መንገድ ድርጅት ውስጥ በሚኖሩ የስራ ክፍሎች በዋና ተጠሪነት የሚቀመጡት በአብዛኛው ለወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ቅርብ ከመሆናቸው በላይ ለስርአቱ ደም እና አጥንታቸውን የገበሩ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ለሰራተኛ እድገት እና ዝውውር ዋንኛ መመዘኛ በማድረግ ተመልክተው ፍቃዳቸውን የሚሰጡት የሰራተኛው የስራ ልምድ እና የት/ት ዝግጅት በመመልከት ሳይሆን፣ ለወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ያለውን አመለካከት እና ጎሳን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አብዛኛው የአየር መንገድ ሰራተኞች በድርጅታቸው ለሚታየው የአስተዳደር ችግሮች በቁጭት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ ሰራቸውን በመልቀቅ ከአገር ወጥተው ይገኛሉ፡፡
ይህ በእንዲ እንዳለ ከሰሞኑ ትልቅ አጀንዳ በመሆን መነጋገሪያ የሆነው የረዳት አብራሪ ሃይለመድህን አበራ የአውሮፕላን ጠለፋ ነው፡፡ የአውሮፕላን ጠለፋ ፖለቲካን መሰረት አድርጎ በአገራችን የተጀመረው ህዳር 29 ቀን 1965 ዓ.ም ሲሆን እነዋለልኝ መኮንን እና ማርታ መብራቱ ያካተተ ነበር፡፡የያኔው ጠላፋ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ዋና አሳቡ ፖለቲካ ጥገኝነትን በመጠየቅ ከአገር ሸሽቱ ለመኖር ሳይሆን በጃንሆይ እና በአስተዳደራቸው ላይ ለተነሳው አመፅ የአውሮፕላን ጠለፋው የአመፁ የእስትራቴጂ አካል ጭምር ስለነበረ ነው፡፡
በእንዲ መልኩ የተጀመረው ፖለቲካዊ ይዘት ያለው የአውሮፕላን ጠለፋ በደርግ መንግስት ምን ያህል ተግባራዊ እንደሆን መረጃ ለማግኘት በእኔ በኩል ያልተቻለኝ ቢሆንም፤ ነገር ግን የአውሮፕላን ጠለፋ በቁጥር እና በአይነት በዝቶ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ጠለፋ የታየው በወያኔ/ኢህአዴግ የመንግስት የአስተዳደር ወቀት ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንዲሁም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የመንገደኛ እና የጦር አውሮፕላን ካፒቴኖች በተለያየ አገር የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው  በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡
በእርግጥ የእነዚህ ካፒቴኖች የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቅ በራሱ የእውነት ፖለቲካዊ ይዘት አለው ወይስ የለውም ለማለት ተገቢ የሆነ ጥናትና እውነታን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ እና መስል አጋሮቹ በመንግስት ከደረሰባቸውን በደልና ግፍ በላይ በአገር ላይ የሚፈፀም በደል አላስችል ሲላቸው የፈፀሙት ገድል ሁሌም ታሪክ በበጎ የሚያስታውሰው ነው፡፡
ሌላው እና ለዚህ ጹሑፍ ዋንኛ መነሻ የሆነው አሳብ የረዳት አብራሪ ሃይለመድህን አበራ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ማንም ሰው በእርግጠኝነት ሊናገር የሚችለው አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ መነሳቱ እና ጄኔቫ ማረፉ ሲሆን፣ አውሮፕላኑ በጄኔቫ ያረፈው በታቀደው መልኩ ሳይሆን ከዚያ ውጪ በሆነ በረዳት አብራሪ ሃይለመድን አበራ ፍቃድ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ነገሮች በአብዛኛው መላ ቅጡ በጠፋ መረጃ የተተበተበ ነው፡፡ በማህበራዊ ድረ-ገፅ እና በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች የሚነገሩ ነገሮች በአብዛኛው የወያኔ/ኢህአዴግ  መንግስት ደጋፊ፣ እንዲሁም ተቃዋሚም የሆን ሁሉ ዋንኛ መነሻ አሳባብ ከራስ ጥቅም እና ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡ ይህም ስለመሆኑ የተነገሩት እና የተለቀቁትን መረጃዎች በማየት መገንዘብ ይቻላል፡፡
የነገሩን ውስብስብነት የበለጥ የሚያገላው ደግሞ የፓይለቱ ቤተሰቦች የሚሰጡት መረጃ ነው፡፡ ለማሳየነትም እንዲረዳ እህቱ ፣አክስቱ ፣ወንድሙ እንዲሁም የአጎቱ ባለቤት እና የቅርብ ጎደኛ በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ቃላቸው ፈፅሞ ሊቀራረብ የማይችል ነው፡፡ በተለይ ታላቅ ወንድሙ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ባደረገው ቃለ መጠይቅ በአብዛኞቻቸን ዘንድ ሞቅ አድርግን ይሆናል ብለን በገመትነው ነገር ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ነው የደፋበት፡፡
ይድነቃቸው ከበደ
ይድነቃቸው ከበደ
የረዳት ካፒቴን ሃይለመድን አበራ አውሮፕላኑን የጠለፈበት ምክንያት በእርግጠኝነት ልናውቅ የምንችለው ከራሱ በሚነገር እውነት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀኑ የራቀ አይደለም ፤ስለዚህም ቀኑ ተጠብቁ ሙገሳውም ትችቱም ቢቀርብ ይበለጥ የተሻለ ይሆናል፡፡ እኔ በበኩሌ በዚህ ጉዳዩ ከመጀመሪያው ጀምሮ የያዝኩት አቋም ይህን ነው፡፡
የዚህ ጹሑፍ ማጠቃለያ የሚሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚታዩ ችግሮች ዋንኛ ምክንያት የአስተዳደር የአቅም ውስንነት መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቀጥተኛ የሆነ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እና ብልሹ ፖለቲካዊ የአገር አስተዳደር ነው፡፡ በመሆኑም ሥራቸውን ብቻ በማየት በሥራቸው ለደረሰባቸው በደል አየር መንገዱን ለቀው ጥገኝነት የጠየቁ፡፡ እንዲሁም ከሚከፈላቸው ዶላር በላይ ስለአገራቸው እና ስለ ህዝብ ተቆርቁረው እንቢ ለሀገሬ ብለው ለተሰደዱ ለሁሉም ተጠያቂው በስልጣን ላይ ያለው የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ነው፡፡
http://www.goolgule.com/ethiopian-airlines-and/

Tuesday, February 4, 2014

አቶ በረከት ስምኦን ኢህአዴግን በመድብለ ፓርቲ ስም ለርጅም ጊዜ እንዲሄድ ማድረግ እንደሚገባ ገለጹ

ከሚዲያ ዝግ በመሆን ለኢህአዴግ ካድሬዎችና ሹሞች በተዘጋጀው ውይይት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን  በኢትዮጵያ በልማታዊ አጀንዳ የሚወከለው ኢህአዴግ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን፣ ሌሎች ፓርቲዎች ወይ ይህንን የሚጻረሩ ናቸው፣ ወይም ትርጉም የሌላቸው ናቸው ብለዋል።  ኢህአዴግ ለረጅም ጊዜ  በስልጣን ላይ ለማስቀጠል በመድብለ ፓርቲ ስም ይዞ መጓዝ እንደሚጠቅም አቶ በረከት ተናግረዋል።

የመድበለ ፓርቲ ስርአት ለአገራችን ተመራጭ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ ያለው ግን የአውራ ፓርቲ ስርአት ነው ያሉት አቶ በረከት፣ ይህም ስርአት ሁለተኛው ተመራጭ በመሆኑ በአገራችን ለርጅም ጊዜ ይቀጥላል ብለዋል። የአውራ ፓርቲ ስርአት አንድ ፓርቲ በምርጫ እያሸነፈ ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል መሆኑንም አቶ በረከት አክለዋል።
አቶ በረከት ይህን የተናገሩት ህዝቡ ሳይሰለች ኢህአዴግን እንዴት ለ50 አመት ተሸክሞ ሊሄድ እንደሚቻል ባስረዱበት ወቅት ነው።
http://ethsat.com/amharic/

በደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ አሰቃቂ ረሀብ መከሰቱ ተዘገበ

አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመጥቀስ እንደዘገቡት በደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ አስከፊ ረሀብ መከሰቱን ተከትሎ የህዝቡ ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል። የሲኤን ቢሲ ዘጋቢ እንደገለጸው ችግሩን ለመቅረፍ እስከ 100 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ ያስፈልጋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የያዘው የምግብ ክምችት ማለቁንም በዘገባው ተገልጿል። እንደ ሲኤን ቢሲ ዘገባ በአፍሪካ ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልግ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋው ኢትዮጵያዊ ነው።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ሰሞኑን በፓርላማ ተገኝተው ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው የነበረ ቢሆንም ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን አፋጣኝ ምግብ የሚፈልጉ ሰዎችን ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን አድርሶታል።
http://ethsat.com/amharic/

የቡራዩ ነዋሪዎች ፌደራል ፖሊስ ከአካባቢው እንዲወጣ እየጠየቁ ነው

በኦሮምያ ልዩ ዞን በቡራዩ ከተማ ትናንት የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ የፌደራል ፖሊሶች በከተማዋ ወጣቶች ላይ የሚፈጽሙት ተደጋጋሚ ግድያ፣ የጸጥታ ስጋት ስለፈጠረብን አካባቢውን ለቆ ይውጣ በማለት መጠየቃቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል። የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ገዳይ የፌደራል ፖሊሶችን ለፍርድ እናቀርባለን በማለት ህዝቡን ለማረጋጋት እየሞከሩ ነው።

በህዝቡና በፌደራል ፖሊስ መካከል ግጭቱ የተነሳው ከትናንት በስቲያ ዳንኤል አስቻለ የተባለ በቡራዩ ከተማ ማረን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ይኖር የነበረ ወጣት  በፌደራል ፖሊሶች መገደሉን ተከትሎ ነው ። በብዙ ጓደኞቹ ዘንድ በጸባዩ ተወዳጅ እንደነበር የሚነገርለት ወጣት ዳንኤል አኳ አዲስ በሚባል የውሃ ማምረቻ ድርጅት ውስጥ በሾፌርነት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር።
ወጣት ዳንኤል በአንድ መዝናኛ ክበብ ውስጥ  አንድ ሲቪል የለበሰን ሰው ገፋ አድርጎ ሲያልፍ፣ ሲቪል የለበሰው ሰው ለምን ተገፋሁ በሚል ስሜት ከሟቹ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ መግባቱን፣ ጭቅጭቁን ተከትሎም ገዳዩ በሟች ላይ ቦክስ ሰንዝሮ ከመታው በሁዋላ ጓደኞቹ እንዴት ተደፈርን በሚል ስሜት ሟችን በቦክስ ፣ በጫማ ጥፊ ከመቱት በሁዋላ እንደገና አስፋልት ላይ አውጥተው በጫማ ጥፊ ሲመቱት፣ ሟች በጀርባው ሲወድቅ ጭንቅላቱ ደም እንደፈሰሰውና ልጁ ለመሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ ወደ አካባቢው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ቢወሰድም ጤና ጣቢያው ከሃቅሙ በላይ እንደሆነበትና  አዲስ አበባ ወደሚገኘው ጥበቡ አጠቃላይ ሆስፒታል ተወስዶ ህኢወቱ በዚያው አልፏል።
በእለቱ ልጁን ደብድበው የገደሉት ሲቪል የለበሱት የፌደራል ፖሊሶች፣ ሬሳውን ሲያዩ ከህዝቡ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ በመግባታቸው ፖሊስ በርካታ ጥይቶችን በመተኮስ ለማረጋጋት ሙከራ አድርጓል። በማግስቱ ትናንት የከተማዋ ነዋሪዎች አስከሬኑን በመያዝ የመንግስት ያለህ፣ ወንጀለኞች ይያዙልን የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮች ማሳማት ሲጀምሩ፣ ቡራዩ ማዘጋጃ ቤት አካባቢ ሲደርሱ ከአመራር አካላትና ከፖሊስ ጋር ግብግብ ተፈጥሯል። የአካባቢው ወጣቶች ለመንገድ ስራ ተብሎ የተቀመጠውን ኮብል ስቶን ድንጋይ እያነሱ ድንጋይ በመወርወራቸው የመዘጋጃ ቤቱ መስኮቶችና በሮች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ተቃውሞውን ተከትሎ መስሪያ ቤቶች ተዘግተው ውለዋል።
በዛሬው እለትም በተለይ ማረት በሚባለው አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ገዳዮቹ ለፍርድ ይቀርቡና ፌደራል ፖሊስም አካባቢውን ለቆ ይውጣ  በማለት ጥያቄዎችን ማቅርባቸው ታውቋል። ውጥረቱ እንደቀጠ ሲሆን፣ ፌደራል ፖሊስም በአካባቢው ተሰማርቶ ይገኛል።
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአካባቢው የሰፈረው የፌደራል ፖሊስ 4 የአካባቢውን ወጣቶች መግደሉ ታውቋል።
http://ethsat.com/amharic/

በልጅ ፍቅር የተዋጀው የነፃነት ትግል (ከንግስት ወንዲፍራው)

(የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፀሃፊ)

ልጄ ኤልዳና ሆይ ሰሞኑን ምን ያህል እንደምናፍቅሽ አውቃለሁ፡፡ እቤቴ ሆኜ ላንቺ ለውዷ ልጄ የናትነት ፍቅር መገለጫ የሆነውን የጡት ማጥባት ስራዬ ላይ ያልተገኘሁት ከጡቱ ከምታገኚው ነገር በላይ የሆነ ላንቺ የሚያስፈልግሽ ነገር ስላለ ነው፡፡ የዚህ ከምንም ነገር በላይ የሆነው ነገር ሰሙ ሃገር ይባላል፡፡Freedom: the quality or state of being free
ቀድሞ ሃገርሽ በአያቶችሽ እና በቅድመ-አያቶችሽ ደምና አጥንት ታፍራ እና ተከብራ ብትኖርም ዛሬ ግን ወያኔ ይሉት ከሃዲ እና አጉራሽ እጅ ነካሽ የሆነው ቡድን መንግስት ነኝ ብሎ ይቺን ከኔ ከምታገኚው ነገር በላይ የሆነችውን ሃገርሽን እንደ ዳቦ እየቆራረሳት በመሆኑ ይህንን ለመቃወም ካንቺ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቄ እንድገኝ ተገድጃለሁ፡፡
ሃገር ማለት ልጄ ነገ አንገትሽን ቀና አድርገሽ የመትራመጂበት የክብር መድረክሽ ማለት ነው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ እንደልብሽ የነፃነት እስትንፋስሽን እየተነፈስሽ ከፍ ስትዪ የምትቦርቂበት፣ ስታድጊ ጎጆሽን የምትቀልሺበት እንዲሁም ስታረጂም የምትሞረከዢበት የክብር ቤትሽ ማለት ነው፡፡ ይህ የክብር ቤትሽ ሙሉ ይሆን ዘንድ አንድ ነፃነት የሚባል ነገር ያስገልገዋል፡፡ ይህ ማለት ትንሽዬዋ ቤትሽ ደምቃ ለመታየት መብራት እንደሚያስፈልጋት ሁላ እቺ ሃገርሽም ነፃነት ይሉት ነገር ያስፈልጋታል፡፡
ያለ ነፃነት ሃገር ጨለማ ነች፡፡ እኔ እናትሽ ደግሞ ምስጋና ለአባትሽ ይሁንና ለእናንተ ለውድ ልጆቼ ጨለማ አላወርስም፡፡ ጨለማ ሃገር ከማውረስ ደሃ ሃገር ማውረስ ይሻላል፡፡ በነፃነት የጠጡት ውሃ ከወተት በላይ ይጣፍጣል፡፡
ልጄ ሁሉ ኢትዮጰያዊ እናት እናትሽ እንዲሁም ሁሉ ኢትዮጰያዊ አባት አባትሽ ነው፡፡ ሰዎች አንቺ እና እኔ ወይም አባትሽ በደም ተሳስራችኋል ይሉሽ ይሆናል ልክ ናቸው፡፡ ግን እኛ ከመላው ኢትዮጵያው ደም የተቀዳን እና አጥንት የተፈለጥን ፍጡራን ስለሆንን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ካንቺ ጋር በቀጥታ በደም የተሳሰረ ነው፡፡ ይህንን ትስስር ማንም አይፈታውም ወይም አይቆርጠውም፡፡ አንቺም ብትሆኚ…፡፡ ዛሬ ካንቺ ርቀው ከሚገኙት ኤርትራዊያንም ጋር ቢሆን በደም የተሳሰርሽ ነሽ፡፡
ልጄ እኔ እና አባትሽ ከምናስፈልግሽ በላይ ሃገር እና ነፃነት ያስፈልግሻል፡፡ ሚሊዮን እናት፣ ሚሊዮን አባት እንዲሁም እጅግ ብዙ ሚሊዮን ወንድም እና እህቶች አሉልሽ፡፡ እነዚህን ሁላ የወለደችልሽ ግን አንድ ናት–ኢትዮጵያ፡፡ ከምንም በላይ እቺ እናት ታስፈልግሻለች፡፡ በእኔ እና በአባትሽ ከምትኮሪው በላይ በኢትዮጵያዊነትሽ ኩሪ፡፡
የሚያኮራ ማንነት፣ ታሪክ እና ጀግንነት አለሽ፡፡ ኩራትሽ ከሜዳ ወድቆ የተገኘ ሳይሆን የተከፈለበት ኩራት ነው፡፡ ከዋጋዎች ሁሉ በላይ የሆነው የሰው ልጅ ህይወት የተከፈለበት ኩራት፡፡
ሚኒሊክ በጀግንነቱ ያቀናው፣ ዩሃንስ አንገቱን ያስቀላለት፣ ቴዎድሮስ እራሱን የሰዋለት የታፈረ እና የተከበረ ማንነት አለሽ፡፡ እኔም ዛሬ በታላቋ ጎንደር ከተማ የተገኘሁ ይህንን አፈር የተነሰነሰበትን ማንነትሽን፣ በደም የተዋጀው ነፃነትሽ እና በጀግኖች አጥንት የታጠረ ዳር ድንበርሽን ለማስከበር ከሚደረገው ሰፊ እና ሰላማዊ ትግል አካል የሆነውን የሃገርሽ እና የጎረቤታችን ሱዳን ድንበር ጉዳይ ነው፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10910/

ጦሰኛው የዐይን ኩልና መሬት ቅርምት በኢትዮጵያ

ይሄይስ አእምሮ

እንደመነሻ – በዚህች ቅጽበት በኢቲቪ እየተላለፈ የሚገኘውን አንድ የእንግሊዝኛ ፕሮግራም ብትመለከቱ የት እንዳላችሁ ልትገረሙ ትችላላችሁ፡፡ ወጣቷ ሴት ጋዜጠኛ ለፈረንጆችና አዲስ አበባን ከእግር እስከራሷ ለማያውቋት ቄንጠኛ የኢትዮጵያ ወይም የሌላው ዓለም ዜጎች ስለዚህችው ገሃነም ከተማ ቆንጆ ምስል ለመፍጠር እየቃተተች ስሰማት ሚስቴ እስክትታዘበኝ ድረስ ከንፈሬን ጠመም በማድረግ አሽሟጠጥኳት፤ ሳላውቅ በስሜት ነውና ጋዜጠኚት ይቅርታሽን እባክሽ፡፡ ሚስቴን ግን ታዘብኳት – “ሞጥሟጣ” ብላ አትሰድበኝ መሰላችሁ፤ ሆ! ለካንስ “ሰውን የሚሰደበው በሚያውቀው ነው” መባሉ አለነገር አይደለምና – ዳሩ መጽሐፉስ ቀድሞ “ኢይከብር ነቢይ በብሔሩ” ብሎስ የለም? በጥቂት የሌሊት የመንገድና የዳንስ ቤት መብራቶችና በጥቂት ዘመነኛ ዳንኪራ ረጋጮች፣ በጥቂት ተምነሽናሾና በጥቂት ገንዘብ መንዛሪዎች የሚሊዮኖች እሥር ቤት የሆነችው አዲስ አበባ እንደለማችና እንዳለፈላት የሚቆጠር ከሆነ የኢቲቪ ድካም በርግጥም ዋጋ አገኘ ማለት ነው፡፡ እውነቱ ግን ይህች ጋዜጠኛ እንደምትለው አይደለም፤ በራሱ ርዕስ ስመለስበት እዳስሰዋለሁ፡፡ ግን ግን ስድስት ሚሊዮን አካባቢ ነዋሪ በሚገኝባት አዲሰ አበባ በጥቂቱ አሥር ሺህ ሰዎች ቢቀማጠሉባትና ሌት ተቀን የሰማይን ጣሪያ በኋላ እግሯ ረግጣ እንዳራቀችው በቅሎ አለልክ ጠግበው እየፈነጠዙ ያሻቸውን ቢያደርጉ አዲስ አበባና አዲስ አበቤዎች አልፎላቸዋል ማለት እንዳልሆነ ኢቲቪዎችም ሆኑ የወያኔው መንግሥት ሊሸፋፍኑት እንደማይችሉ ልናስታውሳቸው ይገባል፡፡ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ነው ነገሩ፤ አዲስ አበባ እነሱ እንደሚያሳዩዋት አይደለችም፡፡ አሁን ወደተነሳሁበት ላምራ፡፡
Land grab in Ethiopia
ጋምቤላ፣ ኢትዮጵያ
“ይበጃል ብለው የተቀቡት ኩል ዐይን አጠፋ፡፡” የምንለው ግሩም ሥነ ቃል አለን፡፡ ጦሰኛ የዐይን ኩል ነው፤ ለጌጥ ብለው ቢቀቡት ዐይንን ከነጭርሱ ደርግሞት ዐረፈው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በሕይወት ዘመኔ እስካሁን ከታዘብኳቸውና አሁንም ድረስ ከምታዘባቸው በርካታ መንግሥታዊ ዐዋጆችና ደንቦች መካከል ብዙዎቹ ከመንግሥቶቻችን የሚፈልቁ ሣይሆኑ ከውጭ የተኮረጁ ናቸው – እንደዬመንግሥቶቻችን የርዕዮተ ዓለም ቅኝት ከምሥራቁ ወይም ከምዕራቡ፡፡ የሚኮረጅ ነገር ደግሞ አዋጭነቱና ተግባራዊነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ የጦጢት ምሳሌ ቀላል አስረጂ ነው፡፡
ተማሪው ዛፍ ሥር ሆኖ ሲያጠና ቆይቶ ምሳውን በልቶ እስኪመለስ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሚያጠናበት ዛፍ ላይ ሆና የተማሪውን ድርጊት ትከታተል የነበረችዋ ጦጣ ትወርድና ደብተሩን ልክ እሱ ሲያደርግ እንደነበረው አደርጋለሁ ብላ በእስክርቢቶ ትሞነጫጭርበታለች፡፡ ሲመለስ ተበለሻሽቶ ያገኘዋል፡፡ በዚህ ነገር ሁሌ ይበሳጫል፡፡ አንድ ቀን ግን ቢላዎ አምጥቶ በደንደሱ በኩል አንገቱን ይገዘግዝና ደብተሮቹ ላይ በማስቀመጥ ለምሳው ወደቤቱ ይሄዳል፡፡ ሲመለስ ኮራጇ ጦጢት ራሷን በራሷ ገዝግዛ ገድላ አስከሬኗን ተዘርግቶ ያገኘዋል፤ ተገላገለ(ችም)፡፡ ከዚያን በኋላ የሚያናድደው ጦጣ አልነበረም፡፡ በዱሮው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍት በአንደኛው የሚገኝ ጥሩ ታሪክ ነው፡፡
ብዙ የአፍሪካ በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥታት ኩረጃ ይወዳሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ከራሳቸው ማመንጨት የማይችሉ ቀፎራሶች ስለሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ በቂ የመንግሥት አመራር ዕውቀትና ችሎታ ስለሌላቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ ከየዘርፉ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸውን ምሁራን ስለማያስጠጉና ከደደቡ ጭንቅላታቸው አሟጠው ሊያወጡት የሚችሉት የሕዝብ አስተዳደር ጥበብ ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ከሕዝባቸው ሥነ ልቦናዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ሕይወት ጋር ፍጹም ሊስማሙ የማይችሉ ኩረጃዎችን ከሌሎች ሀገራት በተለይም አደጉ ከሚባሉና በስንትና ስንት ተሞክሮ ከተፈተኑ መንግሥታት እንዳለ እየገለበጡ በሀገርና በሕዝብ መቀለድን እንደዋና መዝናኛቸው ያደረጉት ይመስላሉ፤ አለማወቃቸውን ሊያውቁም ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ሶሻሊዝም ግልብጥ ነው፤ የሠፈራ ፕሮግራም ግልብጥ ነው፤ ሕገ መንግሥት ግልብጥ ነው፤ የትምህርት ሥርዓቱና ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፓኬጁ ግልብጥ ነው፤ የአስተዳደር መዋቅሩ ግልብጥ ነው፤ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አወቃቀር ግልብጥ ነው፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ግልብጥ(ቅጂ) ነው፡፡ ያልተገለበጠ ነገር የለም፡፡ እኛም ተገልብጠናል፤ ኢትዮጵያዊነታችን ቀርቶ ሌላ ሌላ ነገር ሆነናል ወይም እየሆንን ነው፡፡ ግልብጥነት ከዚህ በላይ የለም፡፡ ብዙዎቹ ሲገለበጡ ግን ስማቸውና ቅርጻቸው እንጂ ከአንጀት ለሀገር ዕድገትና ልማት ታስቦ አይደለም፡፡
አንዲትም ትንኝ አልገደልኩ፡፡
አንድም አማራ ከሚኖርበት አካባቢ አልተፈናቀለም፡፡
አንድም ሰው ከቀዬው አልተፈናቀለም፡፡
አንድም ኢትዮጵያዊ (በሳዑዲ) አልተንገላታም፡፡
አንድም ኢትዮጵያዊ በፖለቲካ ምክንያት አልታሠረም፡፡
አንድም ዜጋ በተቃውሞ ሠልፉ ምክንያት አልተገደለም ወይም ማረሚያ ቤት አልገባም፡፡
አንድም ዜጋ ከእርሻውና ከመኖሪያ ቦታው (ቦታው ለኢንቬስተሮች በሊዝ በመሸጡ ምክንያት) አልተፈናቀለም፡፡
አንድም ሰው አልተራበም፡፡
አንድም ነጋዴ በግብር ብዛት አልተማረረም፡፡
አንድም የመንግሥት ሠራተኛ በኑሮው አልተማረረም፡፡
አንድም ገበሬ ኢሕኣዴግን እጠላለሁ አላለም፡፡
ወዘተ……
ኦ! ኦ! ኦ! ኦ! በጣም፣ በጣም፣ እጅግ በጣም ዕድለኞች ነን፡፡ ብዙ “አንድም”-ኦችን መጥቀስ ይቻላል – የመንግሥት ሰዎቻችን የኛን የሞልቃቃ ዜጎቻቸውን የተደላደለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኑሮ ለሚዲያ ፍጆታና ለዓለም አቀፉ ማኅበረስብ ለማስረዳት በሚያደርጉት የዘወትር ጥረት የሚናገሩትን ለማስታወስ ነው እነዚህን ጥቂት ምሳሌዎች ያነሳሁት እንጂ ሁሉም ነጭ ውሸቶች ቢጠቀሱ ሰማይ ብራና ውቅያኖሶች ቀለም ቢሆኑ ተጽፈው አያልቁም ፡፡ (ማሳሰቢያ፡ ይህን ጦማር የምጽፈው በታሪክ መዝገብ ቤት የሚቀመጥልኝ በዚህ ጉዳይ ዙሪያም የጮኽሁት አንዳች ነገር እንዲኖረኝ በመሻት እንጂ ወያኔ ሰምቶኝ፣ ከሚያደርገው ነገር ይታቀባል ከሚል ሞኝነት እንዳልሆነ አስፈላጊ ባይሆንም እዚህ ላይ መጠቆም እፈልጋለሁ፤ የተረገመ ቡድን ጊዜውን ጨርሶ በታሪክ ወጀብ እስኪጠራረግ ድረስ የዜጎችን ብሶትና የታላላቆችን ምክር የሚሰማበት ጆሮም ሆነ ትግስት እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡ ወያኔዎች በተለይ የሚቃወማቸው የሚመስላቸውን ወገን ‹ጭራ ለማስበቀል› የሚወዳደራቸው የለም፡፡ ጠላቶቻቸውን በማናደድ በምድር አንደኞች ናቸው – የሰማዩን አላውቅም፤ ያው የነሱው ጌታ ሊቀ መላኩ ሣጥጥናኤል ሊሆን እንደሚችል ከመጠርጠር በስተቀር፡፡)
የወያኔን ምግባር የምታስታውስ የአንዲት ሴት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ሴትዮዋ ባሏ ከሚለው በሁሉም ነገር ተቃራኒ ናት፡፡ “እንብላ” ሲላት “እንፍሳ” የምትል በባሕርይዋ ፍጹም ጋግርታም የሆነች የትዳር ላይ ወያኔ ናት፡፡ እኛ የወያኔን ጠባይ ማወቅ አቅቶን በትንሹ 23 ዓመታትን በ“እንካስላንትያ በብጣሽ” “ምናለ በድሪቶ” ዓይነት መደናቆር ስንጃጃልና ወርቃማ ጊዜያችንን በከንቱ ስናባክን ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ እንደዘለቅነው የዚች ሴትዮ ባልም አንዳች መፍትሔ በመፈለግ ወርቃማ ሊያደርገው ይችል የነበረውን የትዳር ሕይወቱን በከንቱ በማባከን ሲደናቆር ባጅቶ በመጨረሻው ያቺ ሴት ጎርፍ ወስዷት ትሞታለች፡፡ መንደርተኛው ተጠራርቶ የዚያችን ሴት ሬሣ ፍለጋ ወደ ወንዝ ይወርዳል፡፡ ባል “ወንድሞቼና እህቶቼ አንደዜ ስሙኝማ!” ይልና እንዲህ ይላቸዋል፡ “ሚስቴ ለኔም ሆነ ለቤተሰቡ ቀና ሆና አታውቅም፤ ነፍሷን ይማረውና ምነዜም ተቃራኒ ነበረች፡፡ ስለዚህ ለጎርፉም ስለማትታዘዘው እንዲህ ሽቅብ ወደላይ እንጂ ወደታች አትሄድለትምና ወደታን ትተን እንዲህ ተወደላይ በኩል እንፈልጋት” በማለት ጎርፉ በሚሄድበት አቅጣጫ ሣይሆን በሚመጣበት አቅጣጫ በኩል እንዲፈልጓት ሃሳብ አቀረበና በጎርፍ ሰውን የመውሰድ ዓለም ውስጥ አዲስ ታሪክ አስመዘገበ፡፡ ወያኔም ሆን ብሎና እንደሥልት የሚከተለው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሚበጅ ሃሳብ ከቀረበ ሁልጊዜም – ከጥቂት በጣት የሚቆጠሩ አብነቶች በስተቀር – ተቃራኒውን መንገድ ነው የሚከተለው፡፡ ያንንም የሚያደርገው ለኢትዮጵያ የሚበጀውን አጥቶት ሣይሆን ሀገራዊ ስሜት የሌለው በመሆኑና እንደስትራቴጂ የሚከተለው የአገዛዝ ዘይቤ ከቀድሞዎቹ ገዢዎች በተለዬ ፍጹም ፀረ-ኢትዮጵያ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሚገርመው ታዲያ የሱ የለዬለት ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ሣይሆን የኛ በወሬና በጩኸት ዕድሜያችንን መፍጀታችን ነው፡፡ የበሬው ምናምን ይወድቅልኛል ብላ ስትከተለው እንደዋለችው ቀበሮ እኛም ወያኔ ሰው ይሆናል ብለን አገዛዙን እንዲያሻሽል ብዙ ብንጮኽም እስካሁን ምንም አልለወጥነውም፤ ወደፊትም ለመቼውም ቢሆን ከዚህ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮው ልንለውጠው አንችልም፡፡ ይልቁንስ እየሣቀብንና የለመደውን የግመሎቹንና የውሾቹን ተረት እየተረተብን ሲዖላዊውን የናቡከደነፆርንና የፈርዖንን አገዛዝ እንዳነገሠብን ይኖራል፡፡ ማርሽ መለወጥ ያለብን እኛው ነን፡፡ ወያኔ ወሬን በማሳመርና በጥናት ጽሑፎች ጋጋታ ወይም በእርግማንና በተቃውሞ ሠልፎች ብዛት ወይም በጋዜጣዊ መግለጫና ኆልቁ መሣፍርት በሌላቸው ፓርቲዎች ምሥረታ ወይም በጎጥና በዘውግ በሚደራጁ ንቅናቄዎችና ግምባሮች ቱማታ … ከሥልጣኑ ሊወገድና እውነተኛ ዲሞክራሲ ሊመጣ አይችልም፡፡ ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ጊዜ እጅግ ቢያልፍም አሁንም ቢሆን ችግሮች እየከፉ እንጂ እየተሻሻሉ ባለመሄዳቸው የምናደርገውን የተናጠል እርምጃ ገታ አድርገን ወይም ከተኛንበት ጥልቅ እንቅልፍ ነቅተን በጋራ አንድ ነገር ማድረግ ይገባናል፡፡ ፈረንጆቹ “Better late than never.” እንደሚሉት እየሞተ ላለ ሕዝብ በማንኛውም ሰዓት የሚደርስለት ረድኤት ትልቅ ፀጋና በረከት ነውና ሀገራችንን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት እንተባበር፡፡ መፍትሔው እሱና እሱ ብቻ ነውና፡፡
መሬት ቅርምት ስለሚባለው የወያኔ አንዱ ፋሽን ትንሽ እንነጋገር፡፡ በመሠረቱ ቀደም ሲል እንዳልኩት ወያኔ በተፈጥሮው ዐይንና ጆሮ ስለሌለው እንጂ በዚህ ጉዳይ ያልተባለ የለም፡፡ ፈረንጁም ሀበሻውም ብዙ ተናግሮበታል፤ ብዙም ጽፎበታል፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ ከመሄድ በስተቀር የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ለአሁኑ ሰሞኑን ከወጡ ዜናና ሀተታዎች መካከል ከሁለት ምንጮች ያገኘኋቸውን ሁለት ዜናዎችን ተመርኩዤ ጥቂት ላውራና እፎይታ ላግኝ – የከበደኝ ጭንቅላቴም ቀለል ይልልኛል፡፡ እነዚህ ምንጮቼ ሪፖርተርና ኢትዮሚዲያ ናቸው፤ በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉት ነገር አለ፡፡
ሪፖርተር “መንግሥት ‹የውጭ ባለሀብቶች የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያን አይመለከትም› አለ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሰሞኑን ለፓርላማ ተብዬው የደናቁርት እንቅልፋሞች ስብስብ የተናገሩትን የስድስት ወር ዘገባ በመጥቀስ ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም እዬዬው የሚሉት እንግዲያውስ የጂቡቲና የሣዑዲ ዐረቢያ የእርሻ መሬቶች ለኢንቬስተሮች ስለተሸጡ ይሆናል፡፡ በአምስቱም በሮች ከአዲስ አበባ ስንወጣ የሚታዬው ለሕዝቡ ከጥፋት በስተቀር ተጨባጭ ዕድገትና ልማት የማያመጣ የአበባ እርሻና የኢንዱስትሪና የሆቴል መናፈሻ ከየት የመጣ መሬት ነው? ጭቁኑ ገበሬ በመናኛ ሣንቲም የካሣ ክፍያ እትብቱ ከተቀበረበት የአያት ቅድመ አያቶቹ ሥፍራ እየተነቀለ አይደለምን ለሀብታም የተሰጠውና እየተሰጠም ያለው? በየክልሉ ለህንድና ለቻይና ኩባንያዎች በነጻ ሊባል በሚችል እጅግ አነስተኛ ዋጋ የተቸበቸበውና እየተቸበቸበ ያለውስ መሬት ገበሬዎች እየተፈናቀሉ አይደለምን? ታዲያ የሚኒስትሮቹና የምክትል ሚኒስትሮቹ ውሸት ይህን ፀሐይ የሞቀው እውነት በምን አቅሙ ነው ሊሸፍነው የሚችለው?
“መሬት የሚሸጠውና የሚለወጠው በኢሕአዴግ ከርሰ መቃብር ላይ ነው” ሲሉ የነበሩትና የገበሬው መጨቆንና መራብ መጠማት የትግላቸው መነሻ እንደሆነ አዘውትረው ይሰብኩ የነበሩት የሕወሓት ታጋዮች ዛሬ ምን ነካቸውና ተገልብጠው በዚህ የዋህ ባላገር ላይ ሊዘምቱበት ቃጡ? ቤት ያፈራውን በፈቃዱ ወድዶ እየሰጠ ወይም እንደዬሁኔታዎች አስገዳጅነት በወያኔው ጉጅሌ በጉልበት እየተነጠቀ ካባና ቀሚስ ሆኖ እንዳይበርደውና እንዳይርበው ሸፋፍኖ ቤተ መንግሥት እንዲገቡ የረዳቸውን ገበሬ ጨረቃ ላይ ያስቀሩት ለምንድነው? የሚታየው ኢፍትሃዊ የመሬት ክፍፍልና የእራሽ መሬት እየጠበበ መሄድ ያመጣው ችግር አነሰና ያቺ ያለቺው መሬት በምን ምክንያት ነው ለባዕድ እየተሸጠ ምርቱም የሀገሪቱ አንጡራ ሀብትም ለውጪዎች የሚሸጠው? መንግሥት የሚባለው ይሄ የወያኔ የጅቦች መንጋ በምኑ እያሰበ ይሆን እንዲህ ያለ የዓለም መንግሥታትን የሚያስደምም የመንግሥት አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ የተከለው? ከግዛቱ አንዳች አንዳች እሚያህለውን መሬት እየገነደሰ ለጎረቤት ሀገራት ማደል፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከጭቁን ገበሬዎች እየቀማ ለውጭ ባለሀብቶች ለዚያውም ተጨማሪ ብድር ሳይቀር እየፈቀደና እየሰጠ ማከፋፈል፣ በነዳጅ ቁፋሮ ሰበብ በሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ጦርነት ማወጅና እንደዐይጥ መጨፍጨፍ… ምን የሚሉት የሕዝብ አስተዳደር ሣይንስ ነው? ከየትስ ተማሩት ይባላል?
በሪፖርተር ዜና ላይ እንደተመለከተው የ“ፌዴራል ኢትዮጵያ” መንግሥት (ፐ! አይ ቋንቋ! ‹ፌዴራል› ሲባል ተሰምቶ እነዚህ የማያፍሩ ጉዶች ይህን ክቡር ቃል አምጥተው አለቦታው ደነቀሩት፤ ለነገሩማ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ነጻነት ይሉስ የለም፡፡ ብቻ ይህም ከመጥፎ ኩረጃዎች አንዱ ነው [It is a mockery or parody of the real democracy which is said to be practiced in the so called civilized world.]  የግብርና ሚኒስቴር፣ “የውጭ ባለሀብቶች በግብርና ኢንቬስትመንት ላይ ለመሰማራት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወስደው እያለሙ እንጂ፣ መሬት ለመቀራመት ብለው ወደ ኢትዮጵያ አልገቡም” ሲል ማስታወቁ በእግረ መንገድ ሰውዬው የሃሳብ መንጠፍ ብቻ ሣይሆን የቋንቋ ችግርም እንዳለበት ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከማን ወሰዱ የሚለው ግልጽ ስለሆነ እሱን እንተወውና ከማንም ይሁን ከማን መሬቱን መውሰዳቸው በራሱ መቀራመት አይደለም ወይ? ይህን የተናገረው ሰው እስኪ ደግሞ ያጢነው፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ከጁፒተርና ከማርስ ወርዶ የኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ተንሳፍፎ – የገበሬዎችን መሬት ሳይነካ – ለምድረ ዐረብና ህንድ ተቃረጠ እንበል? የኛ ገበሬዎች ከመሬታቸው መፈናቀላቸውንና በፖሊስና በመከላከያ ኃይል ብዙ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ትስስር ካላቸው የመኖሪያና የእርሻ ቦታቸው እንዲወገዱ መደረጉን በአንደኛው አንጎላችን ይዘን በሌላኛው አንጎላችን ደግሞ የኢትዮጵያን የመሬት ወቅታዊ ሥሪት ስናስብ ከሕዝብ ብዛት የተነሣ ለአንድ ገበሬ የሚሰጠው የእርሻ መሬት ስፋት ስንት ነው ብለን እንጠይቅ፡፡ የአብዛኛው ገበሬ የእርሻ መሬት ከኩርማን ያነሰና እንኳንስ ለሽያጭ ሊተርፍ ራስን ለመቀለብ የማያስችል አነስተኛ ምርት የሚመረትበት ነው፡፡ ታዲያ የውጪዎቹ ባለሀብቶች ከየት የመጣ “ሰፋፊ መሬት” ነው የሚሰጣቸው? በምንም መንገድ ያግኙት ይህ ክስተት “የመሬት ቅርምት” ካልተባለ የትኛው ነው ሊባል የሚችል? ግብርና ሚኒስትሮች – እባካችሁን የቋንቋ ትምህርት ቤት ግቡ! አለበለዚያ “የሚሉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እየተባላችሁ የዝንታለም መዘባበቻ እንደሆናችሁ ትቀራላችሁ፡፡ ከደደቢት በረሃ ይዛችሁት የመጣችሁት ዘረኛና ግፈኛ አገዛዝን እንጂ የእርሻ መሬትን እንዳልሆነ ልትረዱ ይገባል – ተጋደልቲ አኽዋትና!! የሌላችሁን ነገር ነነገር ደግሞ አትሰጡም ወይም አትሸጡም፡፡ እየቸበቸባችሁት ያላችሁት ገበሬውን በማፈናቀልና ዜጎችን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ስደት በመዳረግ የምታግበሰብሱትን የሕዝብ መሬት ነው፡፡ ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል፤ ወያኔም ቀን ወጥቶለት ከጉድጓድ ወጣና መንግሥትም ሆነና የንጹሓን ዜጎችን መሬትና ሀብት ንብረት በጠራራ ፀሐይ እየዘረፈ፣ ባለመብቶችንም እየገደለ መሬታችንን ለባዕዳን ሲሳይ ያደርጋል፡፡
አቶ ተፈራ ደርበው የተባለ አጋሰስ ሆዳም (ሆዳም አጋሰስ? እኔንም አማርኛው ጠፋኝ ልጄ!) ደግሞ እንዲህ ይላል፤ “መሬት መቀራመት ኢትዮጵያን ጭራሽ አይመለከታትም”፡፡ ይሄም ሰውዬኣችን የቋንቋ ትምህርት ቤት ይግባና በእግረ መንገድም የሎጂክ ትምህርት በዚያው ያጥና፡፡ በል የተባለውን እንደበቀቀን ቃል በቃል እየደገመ ኅሊና ካለው ከኅሊናው ጋር እየተጋጨ የሰው መሣቂያና መሣለቂያ ከመሆን የሚድንበትን ብልሃት ይፈልግ፡፡ ዕድሜ ለቴክሎጂ ሕዝቡም ሆነ መላው ዓለም በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን አንድ በአንድ ያውቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈሳች በሴከንድ ውስጥ ዋሽንግቶንና ኒዮርክ ላይ ትሸታለችና ወያኔዎች እንደልማድና እንደተፈጥሮ ጠባያቸው ልፉ ብሏቸው እንጂ ማንንም ሊያታልሉ አይችሉም፡፡ ዋሹም አልዋሹም ለቅጣት መጥተዋልና እንደዮዲት ጉዲት፣ እንደግራኝ አህመድና እንደመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የመጡበትን ኃጢኣተኛና ተንኮለኛን የመቅጣት ተልእኮ ሣይጨርሱ ንቅንቅ አይሉም፤ “ማንም ሊያነቃንቃቸው አይቻለውም፣ ዘላለማዊያን ናቸው፤” ማለት ግን አይደለም – የቀን ጉዳይ እንጂ ድቡሽት ላይ ቤቱን የሠራው ወያኔ ይቅርና ስንትና ስንት ለሰማይ ለምድር የከበዱ ታላላቅና ኃያላን መንግሥታት ጊዜያቸው ሲደርስ አይሆኑ ሆነው ተንኮታኩተዋል፡፡ የላይኛውም በሉት የታችኛው እስኪያዝ ድረስ ነው፡፡ (ይህችን ሃሳቤን እንኳን ብዙ ሰው እንደሚቃወመኝ አውቃለሁ – የራሴ ብቻ ናትና እለፉኝ! መተላለፍ ተገቢ ነው፡፡ ካልተላለፍን ደግ አይደለም፡፡) በእግረ መንገድ ግን ወደፍቅርና መተሳሰብ መንገድ እንግባ እያልኩ እንደሆነ አፍ አውጥቼ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፤ ቀኑ የጨለመብን ፍቅር ስለጎደለንና አንዳችን ለአንዳችን የማንተዛዘን ድንጋይ ልቦች ስለሆንን ነው – ሁላችንም ባንሆን “ጥቂቶቻችን”፡፡ አቤት ፍርሀቴ! አንዳንድ ደመ ፍሉ ሰው ቱግ እንዳይልብኝ እኮ ተጨንቄ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የመሬት ቅርምቱ የገበሬውን የእርሻና የመኖሪያ ቦታዎች በመቀማትና ከንብረቱም ከኑሮውም ሳይሆን ሜዳ ላይ ከነቤተሰቦቹ በትኖ በማስቀረት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በከተሞችም በተለይም በአዲስ አበባና አካባቢዋ እጅግ ብዙ የሚዘገንን የመሬት ዘረፋ እየተካሄደ ነው፡፡ የአምሳና ዐርባ ዓመት ይዞታ ያለውን ሰው አንድ ወያኔ በጨበጣ ይመጣና ያፈናቅለዋል፡፡ ይህ ወያኔ፣ ከሆነ ቦታ ማዘዣ ሊይዝ ይችላል ወይም በፌዴራል ሊያስገድድም ይችላል፡፡ “ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ” በመሆኑ የፈለገውን ለማድረግ፣ ቀልቡ ያረፈበትን መሬት ከዕድለቢስ ምሥኪን ኢትዮጵያዊ ወገኑ ለመቀማት ብዙም አይቸገርም፡፡ ለድሃ መጣሁ የሚለው ወያኔ በሰውነቱ ውስጥ በተካሄደበት ኬሚካላዊ ለውጥ በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የለዬለት ፀረ-ድሃ ሆነና የማይፈጽመው ግፍና በደል የማናየውም የድሆች ብሶት የለም፡፡ ዱሮ በትግሉ ዘመን በዐይኔ ሂዱብኝ እንዳላለ፣ ዛሬ ወያኔ ስኳር ሲቀምስ ድሃ አልይ አለና ከጥቂቶች ጋር በሂልተንና ሼራተን አሼሼ ገዳሜውን ከአዳዲስ ባልንጀራዎቹ ከነአላሙዲንና አብነት ጋር ማጧጧፉን ቀጠለ፡፡ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት የሚሊዮኖች ሲዖል የጥቂቶች ግን ገነት ሆና ሌላው ቀርቶ ከሰባትና ስምንት ዓመታት በፊት ደህና ነዋሪ የነበሩ ዜጎች ዛሬ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ደረጃቸው ወርዶ የለዬላቸው ለማኞች ሆነዋል፡፡ የወያኔ መቶ ብር ምንዛሬ የደርግን አምስት ብርና የኃይለሥላሴን ሃምሳ ሣንቲም (ኧረ እንዲያውም ከዚያም በጣም ያንሳል) በሆነበት ሁኔታ የሦስትና አራት ሺህ የተጣራ ደሞዝ ተከፋዮች ይህ ገቢያቸው ከቤት ኪራይና ከጓያ ሽሮ እንዲሁም ከትራንስፖርት አላለፈም፤ እናም ይህ የወያኔዎች መሠረታዊው ድል በመሆኑ ሊኮሩበትና ሊኮፈሱበት ይገባል፡፡ ጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልቡ የሚወዳቸውና ጠብ እርግፍ የሚልላቸውም ለዚህ ድል ስላበቁት ነው፡፡ አዲስ አበቤ ስለሳቀና ‹እኝ› እያለ ጥርሱን ስላገጠጠ ብቻ እየኖረ ያለ ሕዝብ ከመሰለን ስህተት ነው፤ ብዙዎቻችን እያኗኗርን እንጂ እየኖርን አይደለንም፤ አሸር በአሸር በልቶ እንደከብት መኖርን መኖር ካላችሁትም በዚህ ደረጃ የምንኖር በብዛት አለን፤ የለየላቸው ያጡ የነጡ ደግሞ በሥውር የርሀብ ጦርነት አንጀታቸው እርስ በርሱ እየተፋተገ የመሞቻቸውን ጊዜ የሚጠብቁ በየጎዳናውና በየቤቱ ሞልተዋል፡፡ አንዳንድ ጣዕረሞቶች ደግሞ በተፈጥሯቸው አስቸጋሪ ከመሆናቸው የተነሣ የሟቹን የመሞቻ ቅጽበት ለመተንበይ ያስቸግራሉ፡፡ ለዚህም ነው -ለምሳሌ- ለ23 ዓመታት ያጣጣረን አንድ ሰው በየትኛዋ ደቂቃ እስትንፋሱ ልትወጣ እንደምትችል መገመት የሚያቅተን፤ ነግር ግን ይህ ሰው አልሞተም ብሎ መዋሸት አይቻልም፡፡ ሞቱን ሞቷል፤ ችግሩ ዕድሩ አልለፈፈም፤ ለቀስተኛውም አላወቀለትም፡፡ አይደለም እንዴ ጓዶች?
ወደኢትዮሚዲያ እንለፍና ከሚለው ነገር ድረገጹን ያልገበኘንና ያን ዜና ያላየን እንቋደስ፡፡
“Land for Sale” በሚል ርዕስ ሥር ባስነበበን በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ዜና ብዙ ቁም ነገሮች ተጠቅሰዋል፡፡ በምንጭነት የጠቀሰው አልጀዚራ በ“People and Power” ፕሮግራሙ ለሥርጭት ያበቃውን ሀገራችንን የሚመለከት ዝግጅት ነው፡፡ ከጊዜ ዕጥረት አኳያ ዋና ዋና ነጥቦችን ብቻ መርጬ ባጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
ይህ የዜና ዘገባ የሚነሣው ኢትዮጵያ አስደማሚ የኢኮኖሚ ዕድገት እያመጣች ያለች ሀገር መሆንዋን በመጥቀስ ነው፡፡ ወደዚያ ከገባን መውጫ የለንምና ዕድገታችን ተከድኖ ይብሰል፤ ወደ አንገብጋቢ የመሬት ሽያጭ ማለፉ ይሻላል፡፡
“… ነገር ግን” ይላል ይህ ዜና – ስለኢትዮጵያ አወንታዊ ነገሮችን ከጠቀሰ በኋላ – “ነገር ግን አሉታዊ ዜናዎችም ከዚህ መልካም [የሚመስል] ወሬ ጋር ተጫፍረው ማለፊያውን ዜና ሊያደበዝዙት ሲሞክሩ መታዘባችን አልቀረም፡፡ 87 ሚሊዮን ከሚሆነው የሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ የሚሆነው የትምህርት ዕድልን ካለማግኘት ጀምሮ እስከ የጤና አገልግሎት ሽፋን በበቂ አለመዳረስና በመሳሰሉት በርካታና የተለያዩ ችግሮች እየተሰቃዬ ነው፤ [የአላሙዲንን ሀብት ለአጣሙዲኖች በምናብ የሚያከፋፍለው] የሀገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ በዓመት ከ1500 ዶላር በታች ነው፡፡ ከ30 ሚሊዮን የሚበልጠው ሕዝብም ሥር በሰደደ ጠኔና ርሀብ እየማቀቀ ነው፡፡(ትንሽ ከፍ ሲል ስለአዲስ አበባ ርሀብ የተናገርኩትን እዚህ ላይ ያስታውሷል)፡፡ ከኢኮኖሚው ዕድገት አንጻር እየታዩ ያሉት በጎ ጅምሮች ተስፋ ሰጪነታቸው እንዳለ ሆኖ በቢዝነስና በህጎች ላይ ማሻሻያ ቢደረግ፣ የመንግሥት አግልግሎት ሰጪ ተቋማት በዘርፉ በሠለጠነና በቂ ዕውቀት በቀሰመ የተማረ የሰው ኃይል እየተመሩ የተቀላጠፈና ከሙስና የጸዳ ዘመናዊ አሠራር ቢከተሉ ሀገሪቱ የበለጠ ዕድገት ልታስመዘግብ በቻለች ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከመቶው እኩሌታውን ያህል የሚሸፍነው የግብርናው መስክ እየተነዳ ያለው ከቁጥጥር በወጣ የመሬት ቅርምት ነው፡፡ ይህን የመሬት ቅርምት የሚያካሂዱት ደግሞ መንግሥት የፈቀደላቸውና ሽያጩን ራሱ መንግሥት የሚፈጽምላቸው የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና የግል ኢንቬስተሮች ናቸው፡፡ የሚገዙበት ዋጋ ደግሞ በሊዝ ጨረታ (ሆኖ እጅግ አነስተኛ ገንዘብ) ነው፤ በዚህ ዓይነት የመሬት ሽያጭ በብዙ ሚሊዮን ጋሻ የሚገመት ለም የእርሻ መሬት ለውጪ ባለሀብቶች ይሸጣል፡፡ [የገበሬው መሬት በዚህ መልክ ተቸብችቦ ሊያልቅ የቀረው ጊዜ አንድ ሐሙስ ብቻ ነው፡፡ ህልምና ትርጉም እንደፈቺው ነው - ደግሞ፡፡]
ይህ የመሬት ሽያጭ በመንግሥት ዐይን እንደ ጥሩ ነገር ይታያል፡፡ በሚገኘው ገቢ የገጠሩን ሕዝብ ለማሻሻል የሚረዱ ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉ መሠረታዊ የልማት አውታሮችን ለመዘርጋት፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስና አዲስ ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ለማስገባት እንደሚውል የግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይገልጻል፡፡ …
ነገር ግን ኦክስፋም፣ ዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅትና የኦክላንድ ኢንስቲትዩትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይህን የመንግሥት የመሬት ሽያጭ ድርጊትና የኩባንያዎቹን የመሬት ቅርምት ለሀገሪቱ አደጋ እንደሚያስከትል እያስጠነቀቁ ናቸው፤ መንግሥት ግን ማንኛቸውንም ሊሰማቸው ፈቃደኛ አይደለም፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እንደሚሉት የመንግሥት ድርጊት የዓለም አቀፉን የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ ይጥሳል፡፡ ምክንያታቸውን ሲገልጹ መንግሥት በሚሊዮኖች ሄክታርና ጋሻ የሚገመት ለም መሬት ለገዢዎች ለማዘጋጀት ከየትም አያመጣውም፡፡ ሊያደርግ የሚችለው  በዝቅተኛ የካሣ ክፍያ ከገበሬው እየቀማ መሬት መሸጥና ዜጎቹን በኃይል እያፈናቀለ የትሚናቸውን ማባረር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከራሱ ዜጎች ይልቅ ለውጭ ሀገር ቅድሚያ መስጠቱን ያመለክታል፡፡ በዚህ ኢሰብኣዊ ድርጊት የሚፈናቀሉት በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ሰብኣዊ መብታቸው ይገፈፋል፤ ባህላቸውና የአኗኗር ዘይቤያቸው ለአደጋ ስለሚጋለጥ በሥነ ልቦናዊ ችግር ሊጠቁ ይችላሉ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለርሀብና ለበሽታ ስለሚጋለጡ ሁልጊዜም ዕርዳታ ጠባቂዎች ሆነው ሰው እጅ እያዩ ለመኖር ይገደዳሉ፡፡
ደሳለኝ ራህመቶ የሚባሉ የሥነ ሕዝብ ዕውቀት ባለቤት እንደሚሉት ተፈናቃይ ገበሬዎች በፍንቀላው ከሚያገኙት ጥቅም ይልቅ የሚደርስባቸው ጉዳት የከፋ ነው፡፡ እንደሳቸው አባባል ገበሬዎቹ መሬታቸው ይወሰድባቸዋል፤ ዘላኖቹ ኢንቬስተሮች መሬቱን ለእርሻ ወይም እነሱ ለሚፈልጉት ነገር ሲያዘጋጁ ሥፍራውን ስለሚመነጥሩትና ደኑን ስለሚያጠፉት የአካባቢያቸው የተፈትሮ ሀብት ይወድምባቸዋል (ቢመለሱ እንኳን አያገኙትም)፤ የተፈጥሮ ሚዛንም ይዛባል፤ መንግሥት እንደሚለው እነዚህ ኩባንያዎች ለአካባቢው መሠረታዊ ልማት ይጠቅማሉ ነው የሚለው፤ እነዚህ ጥቅሞች ግን በሰዎቹ ቸርነትና በጎ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር የኮንትራት ስምምነቱ ላይ አልተገለጹም፡፡ እነዚህ ኢንቬስተር ተብዬዎች ደግሞ የራሳቸውን ፍላጎት ከማሳካት ውጪ ለአካባቢው ልማትና ለገበሬዎች ደንታ ያላቸው አይመስሉም፡፡ በገዙት እርሻ ላይ እነሱ የሚፈልጉትን የእህል ዓይነት እንጂ የአካባቢው ሕዝብ ወይም ሀገሪቷ የምትፈልገውን ምርት ላይሆን ይችላል፡፡ ገበያቸውን የሚመርጡትም እነሱ ናቸው – ‹ይህን እዚያ ወይም ያንን እዚህ ሽጡ፤ እንዲህ ያለ ሰብልም አምርቱ› ብሎ የሚያስገድዳቸው አንድም የህግ አንቀጽ ወይም የስምምነት ሰነድ የለም፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ምርት አምርተው የትም ሊሸጡት ይችላሉ፡፡ እንዲያውም ለሀገር ውስጥ ገበያ ሣይሆን ለውጪ ገበያ ነው የአብዛኛው ምርታቸው ዒላማ(ታርጌት)፡፡ ለምሳሌ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከገበሬዎች ተነጥቆ የተሰጠው አንድ የሣዑዲ ኩባንያ በመሬቱ ላይ ሩዝ አብቅሎ ምርቱን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ነው እሚልከው፤ ሩዝ ደግሞ ከዚያ አካባቢ ሕዝብ የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ የለምና ለከብት ካልሆነ ለራሱ አይመገበውም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኩባያዎችና ባለቤቶቻቸው በዘርም በሃይማኖትም ላልተወለዱትና ላልተዛመዱት ሕዝብ እንዲጨነቁ አይጠበቅም፡፡ ገበሬው የገዛ መንግሥቱ ያላሰበለት ደግሞ ባዕዳኑ እንዲጨነቁለትና እንዲቆረቆሩለት አይጠበቅም፡፡ (“ኩባያዎች” አልኩ እንዴ? ኩባንያ በሉት እባካችሁ)
መንግሥት ከሚያራምዳቸው ፕሮግራሞቹ አንዱ የመንደር ምሥረታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደደርግ ዘመን የመንደር ምሥረታና የሠፈራ ፕሮግራም ሁሉ ጥናት ያልተደረገበትና ምንም ዝግጅት የሌለው በመሆኑ ከልማቱ ጥፋቱ ይበልጣል፡፡ ከትውልደ ትውልድ ጀምረው የኖሩበትን ቀዬ በአንድ አዳር ልቀቁና ውጡ ሲባሉ ዙሪያው ገደል ይሆንባቸዋል፡፡ መንግሥት ሠራሽ ወደሆነ አዲስ መንደርም ሄደው መልመድም ሆነ ሕይወትን እንደገና “ሀ” ብለው መጀመር ይቸግራቸዋል፡፡ ሰማይ ምድሩ ነው የሚደፋባቸው፡፡
እንደዚህ ያለ አሰቃቂ መንግሥት ወለድ መፈናቀል ከደረሰባቸው ወገኖች መካከል ጋምቤላ ውስጥ የአኙዋክና የኑዌር ጎሣዎች አባላት የሆኑ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ይገኙበታል፡፡ አቶ ሙት የሚባል አንድ አኙዋክ ተፈናቃይ፣ “የመንግሥታችን ተቃዋሚዎች ‹መሬት ቅርምት› በሚሉት ፈሊጥ አንድም ዜጋ አልተፈናቀለም፤ በማንም ያልተያዘ መሬት ነው ለኢንቬስተር በሊዝ የሸጥነው” የሚሉንን የወያኔ ባለሥልጣናት ለማሳጣት እንዲህ ይላል፤ በጥሞና አድምጡት፡፡
“ኢንቬስተሮቹ እንደመጡ ጓዛችሁን ሸክፉ ተባልን፡፡ እምቢ ብንላቸው ንብረታችንን፣ ከብቶቻችንን፣እህላችንንና ቤቶቻችንን ሁሉንም ድምጥማጡን እንደሚያጠፉት እናውቃለን፤ [መግደልና ማሳደድ ለነሱ ብርቃቸው አይደለም፤ በኛ በአኙዋኮች ላይ ደግሞ የለመዱት ተግባር ነው]፡፡ ማካካሻ ስጡን ብለን ብንጮኸም ሰሚ የለንም፡፡ ምክንያቱም ቦታው የኢንቬስተሮቹ እንጂ የናንተ አይደለም ብሎ መንግሥት ቁርጡን ነግሮናል፡፡ ይህ ቦታ ደግሞ አያት ቅድመ አያቶቻችን የኖሩበትና ለየትውልዶቻቸው ሲተላለፍ የኖረ ነው፡፡ በመንግሥት አቋም በጣም ፈራን፡፡ ተበሳጭተህ መሬቴን ተቀማሁ ብትል እሥር ቤት ትጣላለህ፡፡ ለምን ታሰርኩ ብለህ  ብትጠይቅ ይባስ ብለው ይገድሉሃል፡፡ [ጠያቂ የላቸውም፡፡ ሕግም የላቸውም፡፡] መሬቱን ተቀምተናል፤ ከአሁን በኋላ የኛ አይደለም፡፡ እኛንም በፈለጉ ጊዜ ሊገድሉን የሚችሉ [የውሻን ያህል እንኳን ክብር የሌለን] ነን፡፡”
ኢትዮጵያውያንም ሌሎች ጉዳዩ ያሳሰባቸው የዓለም ዜጎችም በዚህ ጉዳይ ቢጮሁ ቢጮሁ የወያኔው መንግሥት እንደልማዱ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ እንዲያውም ችግሩን አባብሶ ቀጥሎበታል፡፡ በኦክላንድ ኢንስቲትዩት የጥናት ዘገባ መሠረት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ እንኳን የወያኔው መንግሥት ለውጪ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በመጣያ ዋጋ የሸጠው የገበሬዎች መሬት አንድ ላይ ቢደመር የፈረንሣይን ሀገር ያክላል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ የፈረንሣይን የቆዳ ስፋት ከሁለት ዕጥፍ በላይ የሚሆን የእርሻ መሬት ከዚሁ ከፈረደበት ገበሬ እየተነጠቀ ሊሸጥ እንደሆነ እነዚሁ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ስለዚህ መሬቱም እኛ ኢትዮጵያውያንም እንዳወጣን በወያኔ ተቸብችበን እስክናልቅ በጉጉት መጠበቅና የመጨረሻውን ለማየት እንድንበቃ ዕድሜን ከፈጣሪ መለመን ነው የሚኖርብን፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን፡፡ አሜን፡፡ (ካህኑ እግዚኦ ሲሉ አሁን ከጎረቤት ቤ/ክርስቲያን ይሰማኛል፤ ቅዳሴ እየጨረሱ ነው ማለት ነው፡፡ እኛም በያለንበት እስኪ እግዚኦ እንበል፡፡ እግዚኦታ መጥፎ አይደለም፡፡ ሙስሊሙም፣ አይሁዱም፣ ክርስቲያኑም፣ ሁሉም እንደየእምነቱ ይጸልይ፤ እነዚህ ሰዎች በቀጥታ የተላኩት ከጥልሚያኮሱ ዓለም (from the underworld/netherworld) በመሆኑ እነሱን ለማስወገድ እንደግንቦት ሰባት እምነትና ውሳኔ እውነትም በተገኘው ዘዴ ሁሉ – ጸሎትንም ጨምሮ ማለቴ እንደሆነ ይሰመርልኝ – አስተሳሰባዊ ዘርማንዘራቸው ለትውልድ ብክለት ሳይተርፍ ወደመጡበት መመለስ ነው፡፡ ወደዚምባብዌ … ማነው ወደ ደደቢት ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚያስ ሊመለሱብን ይችላሉ፡፡ ማስወገድ ከምድረ ገጽ ነው፡፡ ማስወገድ ደግሞ ሥጋን አይደለም – መጥፎ አስተሳሰብን እንጂ፡፡ መጥፎ አስተሳሰብን ለማስወገድ መታጠቅ ከሚገባን የመሣሪያ ዓይነቶች አንዱና ዋናው ደግሞ ፍቅር ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች ፍቅርን ጨምሮ በሁሉም መሣሪያ እንረባረብባቸውና የሀገራችን የጋራ ባለቤቶች እንሁን፡፡ ለሀገርና ለራስ ኅልውና ሲባል በፍቅርም በሠይፍም መዋጋትን እነቅዱስ ዳዊትና ልጁ ሶሎሞን፣ እነሙሤም በተግባር አሳይተውናል፡፡ አሁንም በድጋሚ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10912/

Monday, February 3, 2014

አዲስ ዓመት ለጋራ ራዕይ – በአበራ ሽፈራው /ጀርመን/

በአበራ ሽፈራው /ጀርመን/

በፈረንጆቹ ወይም እንደ ጎርጎርያን አቆጣጠር 2013 ዓ.ም  በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው አለም ታላላቅ አሳዛኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ግጥመውን አልፏል፡: አንዳንዴም ይህ ዓመት ባልነበረ የሚያስብል ነበር :: እንኳን አለፈ ::
ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ብዙዎች ለእስር የተዳረጉበት፣ ፍርደገምድል ፍርዶች በፍርድ ቤቶች የታዩበት፣ የፖለቲካ እስረኞች በከፍተኛ ሁኔታ የተበራከቱበት፣ እስር ቤቶች በፖለቲካ አቋማቸውና አስተሳሰባቸው ብቻ በህወሓት ሰዎች አይን ውስጥ በገቡ የተሞሉበት ፣ የነጻው ፕሬስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በህወሓቶች ጥቃት የደረሰበት ፣ የአማራ ተወላጆች በዘረኞችና ግልጽ በወጣ የዘር ጥቃት በሚፈጽሙ በህወሃቶች ባለሟሎች እቅድ ማፈናቀል የተደረገበት በዚህም ምክንያት ብዙዎች ለመከራና ለችግር የተዳረጉበት፣ አጥፊው የህወሓት ማኔፌስቶም አሁንም ትግበራውን ይቀጥላል ማኔፌስቶው ሳይሆን ምስጊን የቤንሻንጉልና ጉምዝ ሰዎች በትግበራ ዙሪያ እንደደቡቡ በተጠና መልኩ ማፈናቀሉን ባለማድረጋቸውና ህወሓቶችን በአደባባይ ያጋለጠ ድርጊት በመሆኑ ለቅጣት ተዳረጉ፣ አዛዡ አሳሪ ታዛዡ ታሳሪ ሆነና ድራማው ተጠናቀቀ በዚሁ ክፉ ዓመት : : በተለይም የሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሃይማኖት ነጻነት ትግልን በሃይል ለመጨፍለቅ ታስቦ ብዙዎች በአደባባይ የተገደሉበት፣ የታሰሩበትና እጅግ አስከፊ ግፍ የተፈጸመበት ዓመት ነበር በአገራችን ኢትዮጵያ::
ይኸው 2013 የህወሓት ዘረኛ ቡድን የአገሪቷን ወታደራዊ ኃይል ለመቀራመት በድርጊቱ ጠንሳሽና መሃንዲስ በነበረው መለስ ዜናዊ እቅድና ራዕይ መሰረት ሁሉንም ወታደራዊ ሃይል በህወሓቶች ለማስያዝና የአፈናውን ሥርዓት ለማጠናከር ሲባል በየትኛውም የአገሪቷ ዘመናት ባልታየ መልኩ ከፍተኛ የጀነራልነት ማዕረጎችና ሌሎች ወታደራዊ ሥልጣኖችን 99% በሚባል መልኩ የህወሓትን የበላይነት ለማረጋገጥና ስርዓት የለቀቀውን አገርን የመምራት አቅም ማጣት ለማስጠበቅ ሲባል ምንም ወታደራዊ አቅምና ትምህርት ለሌላቸው ሰዎች ብዛት ያለው የጀነራልነት ማዕረጎችን በመስጠት በአለምና በአገሪቷ  ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሹመት ድግስ የተደገሰበት ዓመት በመሆን ተመዝግቧል ::
በዚሁ በ2013 የሰላማዊ ትግል አራማጅ ፓርቲዎች በአገር ውስጥ በተለይም የአንድነት ፓርቲ፣ የሰማያዊ ፓርቲና የመድረክ አመራሮችና አባሎቻቸው ለከፍተኛ ጥቃት የተጋለጡበት፣ በየምክንያቱ አባሎቻቸው ለእስር፣ ለድብደባና ለእስራት የተዳረጉበት ጊዜ በመሆን የሥርዓቱ አስቸጋሪነትን የተመለከትንበት ዓመት በመሆን አልፏል :: የተቃዋሚው ሃይል ከገዢው የማፍያ ቡድንም ጋር  ግልጽ የሆነ ትንቅንቅ ውስጥ የገባበትና የህወሓት ገዢ ቡድንም በከፍተኛ ትዝብት ላይ የወደቀበት ጊዜ በመሆን የተሰናበተን ዓመት ሲሆን በተቃዋሚው ላይ የደረሰው መከራ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሆነበት  ዓመት ለመሆን በቅቷል ::
አገራችንና ህዝቦቿ በእነዚህ ሙሰኞችና በዝባዦች እጅ ከወደቀችበት ጊዜ ጀምሮ ፍጹም ባልታየ መልኩ ጥቂቶች እየበሉና እየጠጡ የሚኖሩባት ሌሎች ወይም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለፍጹም የኑሮ ውድነት የተጋለጠበት ዓመት ከመሆኑም በላይ በኑሮው ውድነት ምክንያትም ህዝቡ ለከፍተኛ የኑሮ ምስቅልቅሎሽ ተዳርጎና ለከፍተኛ ስደትም በመዳረግ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚደርስበት የስደት መከራና ሞት ቀላል አልነበረምና አብዛኛው ህዝቡ ችግሩን ተጋፍጦ መፍትሄ የሚያመጣለት አጥቶ አምላክን በመማጸን ያሳለፈበት አመት በመሆን አልፏል :: ይሁንና ህወሓቶችና ባለሟሎቻቸው ግን በየምክንያቱ ጮማ እየቆረጡና ውስኪ እየተራጩ ዓመቱን ሲያሳልፉ መክረማቸውንና በተለያዩ አገራት ያሸሿቸው የገንዘብም መጠን ቀላል እንዳልሆነና ከሟቹ መሪያቸው ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሹማምንቶቻቸው ድረስ የአገሪቷን ገንዘብ ለመበዝበዛቸው የውጭ ሚዲያዎችና እራሱ ኢቲቪ ሳይቀር ተገዶ “ሙሰኞች ነን” ለማለት የሞከሩበት አመት ሆኖ ተመዝግቧል :: ይሁንና ከዚሁ ከሙስና ጋር ተያይዞ ሙሰኛ ጋኖችን ሳይሆን ሙሰኛ ገንቦዎችን በመስበር ሲቀልዱ የታዩበት ዓመት ነበር :: ከዚህም የተረዳነው የጠገቡ ሙሰኞች ያልጠገቡ ሙሰኞችን ሲያጠቁ ተመለከትን ::
በዚሁ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ህወሓት በታሪክ አጋጣሚ ከሱዳን ጋር ባለው የጥፋት ቁርኝት አገርን ለባእዳን አሳልፎ በመስጠት የሚታወቀው ሥርዓት ከኢትዮጵያ ድንበር ሰፊውን ግዛትና ለም የሆነውን የአገሪቷን መሬት ለሱዳን ለመስጠት ውሎችን ለመፈራረምና ለዘመናት ደም እየተከፈለበት የኖረን የአገሪቷን መሬት አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀበትና ህወሓት ምን አልባትም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያስብ ቡድን እንኳን ሆኖ ቢገኝ በአገሪቷ ታሪክ በክህደት የሚጠየቅበትን ሁኔታ ያስመዘገበበት አመት ሆኖ ከመመዝገቡም በላይ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከአሰብና ከሌሎች በህወሓት ምክንያት ደም ካፋሰሱ የኢትዮጵያ ድንበሮች በተጨማሪ አሁን ደግሞ በዚህ ዘመን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አገርን ለመሸጥ ሲደራደሩ የከረሙበት ዓመት በመሆን ተመዝግቧል ::
የብዙዎች የኢትዮጵያ ሱማሌዎችና የአፋር ህዝቦች ደምም በህወሓት ወታደሮች የፈሰሰበትና ህወሓቶች በሌሎች ዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግፍ የፈጸሙበትን ማስረጃ የቀረበበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውንና ማስፈጸማቸውን የሚያሳዩ ማስረጃዎች የተገኙበትና ያንንም ለማጠናከር ትልቅ ግልጽ ዘመቻ የተከፈተበት ዓመት በመሆን በአውሮፓዊቷ አገር በሲውዲን አገር እንቅስቃሴ የተጀመረበት ዓመት በመሆንና ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን ለማጠናከር እንቅስቃሴ የተጀመረበት ዓመት በመሆንም ይታወሳል 2013 ::
“አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ” እንዲሉ ዘረኛውና አንባገነኑ የህወሓት መሪ ለ21 ዓመታት ለብቻው ይዞት የነበረው የጭቆና ቀንበር ለዘለዓለም ወደዚች ምድር ላይመለስ በሞት በመሰናበቱ ምክንያት አገሪቷን ለከፍተኛ ችግርና አዳጋች ሁኔታ አጋልጧት እንደሄደና ህወሓትንም እርቃኑን አስቀርቶት ባዶ ቡድን መስርቶ የነበረ ለመሆኑ ማስረጃ መሆኑ እስኪታይ ድረስ ተተኪን ለመፍጠር እንኳን እንዳይቻል እያስፈራራ የፈጠረውና የገነባው ሥርዓት ለመሆኑ በግልጽ እስከሚታይ ድረስ በህወሃቶች መካከል ብቻ ሳይሆን በተለጣፊዎቹ የህወሃት ኢህአዴግ ፓርቲዎች ጭምር የዕርስ በርስ ትርምስ የተፈጠረበትና አገሪቷን የሚመሩ ግማሽ ደርዘን ሊጠጋ ትንሽ ቁጥር የቀረው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በመያዝ የተመዘገበችም አገር በመሆንና ኢትዮጵያውያንን በማስገረም ያለፈ ዓመት ሆኖ አልፏል ይኸው 2013 ጉደኛ ዓመት ::
ይኸው 2013 በአባይ ግድብ ሰበብ ከመላው ኢትዮጵያና ከመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኪስ የህወሓት ቀማኞች ገንዘብ የሰበሰቡበት፣ በግዳጅ የነጠቁበትና ገንዘባቸውን ለቀማኛ ቡድን ለመስጠት ያልፈለጉ በውጭው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የአባይን ግድብ እንዲገደብ ቢደግፉም በብዝበዛ፣ በሙስናና በመስረቅና የሃገርን ሃብት በውጭው ዓለም በሚገኙ ባንኮች በማስቀመጥ የሚታወቁትን የህወሓት የማፍያ ቡድንን ከአባይ በፊት ሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩ በመጠየቅ፣ መለስና ሌሎች የህወሓት ሰዎች በውጭ ያከማቿቸው ገንዘቦች አንድ አባይን አይደለም ብዙ አባይን ይገነባሉና አውጡና በአገራችሁ አውሉት እያሉና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸውን ሃሳቦች በማንሳትና በመቃወም በመላው ዓለም ህወሓት የቀለለበት ዓመት ነበር 2013 በእርግጥም ሕወሓት ቀድሞውንም ቢሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት የቀለለ ለመሆኑ እራሱ ህወሓትም ያውቀዋል ::
በዚሁ በ2013 በአገራችን በተለይም በጋምቤላ ክልል ሰፊ የመሬት መቀራመት የተፈጸመበትና ከፍተኛ ተቃውሞም በዚሁ ዙሪያ የተደረገበት ዓመት ከመሆኑም በላይ የጋምቤላ ነዋሪ ወገኖቻችንም በተወለዱበት፣ በአደጉበትና ተፈጥሮና ትውልድ ያስረከባቸውን መሬት በህወሓት ቀማኞች በአደባባይ በሃይል የተነጠቁበት ዓመት ነበር :: በሌሎች ክልሎች የገጠር ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በከተማ ቦታዎችም ዙሪያ ግልጽ ቅሚያ የተፈጸመበትና ህወሓትን ተው የሚለው ጠፍቶ ያሻውን ያደረገበት ዓመት ነበር ::
የህወሓት አንዱ የመበዝበዣ ተቋም የሆነው የመከላከያ ሚንስቴር መስሪያ ቤትና ተያያዥ መምሪያዎችና የወታደራዊ መዋቅሮች በአገሪቷ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአንድ ዘር ስር መውደቁ የታወቀ ቢሆንም የአገሪቷ ሃብት በዚሁ ተቋም በነዚሁ በህወሓት ጀነራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች እንደሚበዘበዝ ግልጽ እየሆነ ባለበትና ወቅትና ይህንንም ችግር ለማስቆም የተለያዩ አካላት ጥያቄ ማንሳት በጀመሩበት ወቅት ማንም ምንም አያመጣም ያሉ እስኪመስል ድረስ መከላከያ ኦዲት አይደረግም የሚል ሃሳብ መነሳቱና ጉዳዩ የህግ ከለላ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው የታየበትና ጉዳዩ በግልጽ እንደሚያሳየው ብዝበዛው በህግ እንዲደገፍ አዋጅ ያስነገሩበት ዓመትም ነበር በእርግጥም አይን ያወጣ ዝርፊያ ለመቀጠል ከፍተኛ መሰረት የተጣለበት ነበር ይህ ክፉ ዓመት:: አይ 2013 ጉደኛ ዓመት ::
የህዝቡን የፍትህና የነጻነትን ጥማት ይልቁንም ለመቀልበስና የህወሓትን ብዝበዛና ጭቆናን ለመቀጠል በታሰበ መልኩ “1 ለ 5″ የሚልን የአፈና መዋቅር ለመተግበር ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበትም ዓመትም ነበር::
በሌላ በኩል  በዚሁ አስከፊ ሥርዓት ምክንያት በዓረቡ ዓለም ተበትነው የሚኖሩና በተለይም በሳውዲ አረቢያ በልዩ ልዩ መንገድ ወጥተው ተቀጥረው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው ችግርና ሰቆቃ ምክንያት ብዙው ኢትዮጵያዊ በዓለም ህዝብ ፊት በዕንባ የተራጨበትና አምላክንም የተማጸነበት ዓመት ሆኖ ነበር :: በዚህ ምክንያት ብዙ ኢትዮጵያውያን ውስጣቸው ያዘነበት ዓመት ነበር::

ይህም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ህወሓትን ለመጋፈጥና በግልጽ መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጠበት፣ የሠላማዊ ትግል አራማጆችም ትግሉን በተለያዩ አቅጣጫዎች ያደረጉበትና የህወሓትን ማንነት በማሳወቅ ዕርቃኑን እንዲቀር ያደረጉበት ፣ የትጥቅ ትግል አራማጆችም ትግሉን በተለያየ አቅጣጫ በማድረግ ህወሓት ድንጋጤ ውስጥ እንዲገባና የሚይዘውና የሚጨብጠው እንዲያጣ በማድረግ ያደረጉት ትግልም ቀላል አልነበረም:: በዚህ ዙሪያ አርበኞች ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን ነጻነት ግንባርና ሌሎችም ያደረጉት የትጥቅ ትግልና ድል ቀላል አልነበረም:: ከዚህ በተጨማሪ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይልም ትግሉን ወደፊት ለመውሰድ የጣለው መሰረት በህወሓት መንደር ትልቅ ድንጋጤን ከመፍጠሩም በላይ በህወሓት ላይ ከፈጠረው ጫና የተነሳ ህወሓት ሳይወድ በግዱ የንደራደር ጥያቄንም እንዲያቀርብ ያስገደደው ሁኔታ ገጥሞታል ::

እነዚህ ከላይ ያየናቸው ሁኔታዎችና ሌሎች አሁን ያልጠቀስናቸው ሰፊ የአገራችን ችግሮች በዚሁ በ2013 በመፈጠራቸው ዓመቱ እጅግ አሳዛኝና መራራ አመት ነበር ለማለት ያስችላል :: ለዚህ ሁሉ ችግር ትልቁ ተጠያቂም ህወሓት እራሱ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም  :: 2014 አዲሱ ዓመት ግን ለዓመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ይህ ዘረኛ ቡድን የሚፈጽመውን ግፍ ለማስቆም በጋራ የምንቆምበትና በአገራችን ሁላችንንም በእኩልነት፣ በፍትህ፣ በነጻነት፣ በህግ የበላይነት ሥር ሁላችንም በህግ ፊት እኩል ሆነን የምንኖርባትን አገር ለመመስረትና ለዚህም የህዝብና የአገር ራዕይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለራሱ ሲል አቅሙ በቻለ ሁሉ ትግሉን እንዲቀላቀልና ህወሓትን በመደምሰስ በጋራ ሁላችንንም የምትወድ አገር  ልንመሰርትበት የምንችልበትን መሠረት የምንጥልበት ዓመት ሊሆን  ይገባናል  እላለሁ :: ቸር ይግጠመን ::
https://www.zehabesha.com/amharic/archives/11765

Good Bye Dogmatic Wreath

Welcome Social Harmony


index

When is the Ethiopian political class going to get rid of its dogmatic wreath?
A glance at the political discussion all through the active organized political players and stakeholders would suffice to find out that this is not the case. With this in mind to give social harmony a chance I have presented a model of harmony, which I was promoting during the last decade so that a touch of serenity and sovereignty would come to the latter. Say good bye to the bewildered spirit of the youth of the last generation and its dogmatic wreath to welcome the new youth with the new spirit of enlightenment and cultural development. Make 2015 the year of the enlightened youth for a bright future of peace and social harmony, free of the dogmatic past, making your choice as a sovereign individual to determine your own destiny. (Click here to read more)
http://www.goolgule.com/good-bye-dogmatic-wreath/

የ2014 የዓለም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ

ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

coup map

በያዝነው የአውሮጳውያን ዓመት ሊከሰቱ የሚችሉ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋዎች ይፋ ሆኑ፡፡ በርካታዎቹ በአፍሪካ አገራት ሲሆኑ አደጋው ካንዣበበባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ 25ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በአሜሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ጄይ ዑልፌልደር የተለያዩ የሒሳብ ስሌቶችን በመጠቀም የ2014ዓም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ትንበያ ከሆነ 40 አገራት ቀይ የአደጋ ምልክት በርቶባቸዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ መፈንቅለ መንግሥት እንዲሆን የሚመኙት ነገር ባይሆንም የመከሰቱ ጉዳይ ግን መነገር ያለበት ነው ይላሉ ምሁሩ፡፡
በተለያዩ የአሜሪካ አንጋፋ ጋዜጦች ላይ የተዘገበው ይኸው ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለማችን ላይ 40 አገራት ከፍተኛ የመፈንቅለ መንግሥት አደጋ ያነጣጠረባቸው መሆናቸውን በጥናቱ ተገልጾዋል፡፡ አብዛኛዎቹም ከአፍሪካ መሆናቸው አሁንም አህጉሪቱ ለበለጠ ቀውስ የተጋለጠች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
forecast-dot-2014በቀዳሚነት የመፈንቅለ መንግሥት የሚያሰጋቸው አገራት ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ማሊ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኒጀር፣ ጊኒ ቢሳው እና ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክና ደቡብ ሱዳን ናቸው፡፡ ከአውሮጳ ምንም አገር በዝርዝሩ ውስጥ ያልገባ ሲሆን ዩክሬይን አደጋው ጥላ ካጠላባቸው በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ ከወደ አሜሪካ ዩኳዶርና ሃይቲ ቀዩ የአደጋ ምልክት የታየባቸው ሲሆን ከእስያ ታላንድ፣ አፍጋኒስታን እና ፓኪስታንን ጨምሮ ስድስት አገራት የመፈንቅለ መንግሥት የቀይ ምልክት አደጋ ካለባቸው 40 አገራት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከ40ዎቹ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 25ኛ ላይ ትገኛለች፡፡ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ህወሃት/ኢህአዴግ ሥልጣኑን ለራሱ ታማኞች ብቻ በመከፋፈል እንዲያም ሲል በቤተሰብ ደረጃ በማውረድ እየሸነሸነው በመሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሰሞኑን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አዲስ አድማስ ሲዘግብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን እና የነጻው ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ገልጾ ነበር፡፡
አፋኝ ሕጎችን በማውጣትና ማንኛውንም ዓይነት የግለሰብ መብት በመንፈግ በአንጻሩ ሊኖር የማይችል የቡድን መብት አስከብራለሁ የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ በተመሳሳይ የሚወጡ መረጃዎችን በማጣጣል ዋጋ ቢስ ሲያደርግ መቆየቱን የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡ በተቀረው ደግሞ “ልማት፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ፣ … ” በማለት የለውጥ ሃሳብ ከመጣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይስተጓጎላሉ በሚል በሕዝቡ ዘንድ ማደናገሪያ በመፍጠር በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች “ጸረ ልማት” በማለት እንደሚወነጅላቸው ያማርራሉ፡፡ በምርጫ ማጭበርበርና ማንኛውንም ፖለቲካዊ ሆነ ማኅበራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በሙሉ ቁጥጥር ሥር ማዋል ኢህአዴግ በሥልጣን ለመቆየት የሚጠቀምባቸው ዓይነተኛ መንገዶቹ እንደሆኑ በስፋት ይጠቀሳል፡፡
ይህንን የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ የቀመሩት ምሁር ስሌታቸውን ለማቀናበር የተለያዩ መረጃዎችን መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአገራቱ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በቅኝ ግዛት የመያዝ ሁኔታ፣ የአገራቱ ዕድሜ፣ ከነጻነት በኋላ የኖሩበት ዓመታት፣ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የእርስበርስ ግጭት፣ የነጻ ምርጫ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በየቀጣናው ያለ የመፈንቅለ መንግሥት እንቅስቃሴ፣ ወዘተ የተወሰኑት ናቸው፡፡ ይህንን አያይዘውም የመፈንቅለ መንግሥት ትንበያ ማድረግ የግድ መፈንቅለ መንግሥት ይሆናል ማለት እንዳይደለ ነገር ግን አደጋውን ተመልክቶ አስፈላጊ እርምጃዎች በመውሰድ እንዳይሆን መከላከል ዓይነተኛ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (ካርታዎቹ የተወሰዱት ከጄይ ዑልፌልደር ብሎግ ነው)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የዛሬ ዓመት የአሜሪካንን የደኅንነት ምክርቤት ጠቅሶ ባወጣው ዜና በ2030 እኤአ ከሚከሽፉ መንግሥታት (failed states) መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዘግቦ ነበር፡፡ ዜናውን ከዚህ በታች በድጋሚ አትመነዋል፡፡

“በ2030 ከሚከሽፉ መንግሥታት አንዷ ኢትዮጵያ ነች”

ዘገባው የ15 አገራትን ዝርዝር አውጥቷል
የአሜሪካ የብሔራዊ የደኅንነት ምክርቤት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2030 የሚከሽፉ 15 መንግሥታትን (failed states) ዝርዝር አውጥቷል፡፡ “በግጭት መብዛትና በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ምክንያት” ይከሽፋሉ ተብለው ከተተነበዩት የአፍሪካ፣ የእስያና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡
እጅግ የነጠረ፣ ያልተዛባና የተጠና ዘገባ ለአሜሪካ የስለላ ተቋማት፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አውጪዎችና ለዓለምዓቀፍ ግንኙነት ተመራማሪዎች በማውጣት የታወቀው የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ምክርቤት ከተቋቋመ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ምክርቤቱ በሚያወጣቸው ዘገባዎች የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ የተለያዩ መ/ቤቶች ተጽዕኖ እንደማያደርጉበት የሚናገር ሲሆን፤ ዘገባዎቹንም ከአድልዎ እና ከአሜሪካ መንግሥት አቋም ነጻ በመሆን እንደሚያዘጋጃቸው ይናገራል፡፡
NICየም/ቤቱ ዘገባ በተለይ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ለመጪው ፕሬዚዳንት የወደፊቱን የዓለማችን መልክ ምን እንደሚመስል የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ አስተሳሰቦች እና ዓለምአቀፋዊ ዝንባሌዎች ላይ አቅጣጫ የሚጠቁም ትንበያ ያደርጋል፡፡ ለፕሬዚዳንቱ ዓለምአቀፋዊ የደኅንነት ዘገባ ያቀርባል፤ ለብሔራዊ የጸጥታ ምክርቤት እና ለአገር ውስጥ ደኅንነት መ/ቤት ምክር ያቀብላል፤ በአጠቃላይ የአሜሪካን የስለላና የደኅንነት ማኅበረሰብ ሊከተል በሚገባው ጉዳይ ላይ አቅጣጫ የሚያስይዝ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
በዚሁም መሠረት ባለፈው የታህሳስ ወር “በ2030 የዓለም አቅጣጫ፡ አማራጭ አገራት” በሚል ርዕስ አንድ ዳጎስ ያለ ጥናት አቅርቧል፡፡ ይኸው 160ገጽ ያለው ዘገባ የዛሬ 17ዓመት የዓለማችን ገጽታ ምን እንደሚመስል ከየአገራቱ በተወሰደ ጥናትና እዚያው በሚገኙ ተመራማሪዎች የሰበሰበውን ያካተተ ነው፡፡ ዓለማችን የምታዘነብልባቸው ቀዳሚ ሁኔታዎች አንዱ ሰዎች በራሳቸው አነሳሽነት ድህነትን ለመቀነስ፣ በትምህርት ለማደግ፣ በቴክኖሎጂና በህክምና ለመራቀቅ እንዲሁም በገቢም የመካከለኛው መደብ ላይ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቀሱት አንዱ አቅጣጫ ጠቋሚ ነው፡፡
ሌሎቹ ዓለምን አንድ አድርጎ በመዳፉ ሥር የሚገዛ ኃይል የማይነሳ መሆኑ ከሚታዩት ከፍተኛ ዝንባሌዎች ተጠቃሽ ሲሆን አሜሪካ ምንም እንኳ “የዓለም ፖሊስ” የመሆኗ ሁኔታ የሚቀንስ ቢሆንም የዓለምን አቅጣጫ መቆጣጠሯ ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ የዓለም የሕዝብ ቁጥር ከመጨመሩ አኳያ “እያረጁ” የሚሄዱ አገራት የኢኮኖሚ ዕድገታቸው እንደሚያሽቆለቁልና ከገጠር ወደከተማ ፍልሰት እንደሚጨምር፤ 60በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በከተሞች አካባቢ ኑሮውን እንደሚያደርግ ይተነብያል፡፡ በዚህም ምክንያት የውሃ፣ የምግብና የኃይል (ኤነርጂ) ፍላጎት ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያድግ ይናገራል፡፡ የቴክኖሎጂ ምጥቀትና የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎትም የዓለማችንን አቅጣጫ እንደሚቀይር ያስረዳል፡፡
የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት በስፋት እንደሚቀጥልና በበርካታ ፈርጆች ትብብርና ስምምነት እየፈጸሙ ሰፋ ያለ ዓለምአቀፋዊ ኅብረት እንደሚያደርጉ የሚናገረው ይህ ሪፖርት በየአገራቱ እየሰፋ የመጣው በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ክፍተት የማኅበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ይጠቁማል፡፡ ይህም ቀውስ በአንዳንድ አገራት ውስጥ እየሰፋ በመምጣት ለተባባሰ ግጭትና ክስረት እንደሚያጋልጥ የኑሮ ልዩነቱም የማኅበራዊ ቀውሱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያደርሰው ይተነትናል፡፡ የሃይማኖት ሚና እንደሚጨምር የጠቆመው ዘገባ ይህንኑ ተከትሎ መካረርና ግጭት እንዲሁም አሸባሪነት ለመስፋፋት ሃይማኖት ምክንያት እየሆነ እንደሚሄድ ይናገራል፡፡
በዘገባው ከተነገረው በተጻጻሪ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ወዲህ እስካሁን በ44 አገራት ጉዳይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጣልቃ በመግባት ጦርነት ያካሄደችው አሜሪካ የዓለም ኃያል ሆና እንደምትቀጥል በመናገር ሪፖርቱን የሚያጣጥሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንደማስረጃም አድርገው አሜሪካ በተለያዩ አገራት ያላትን 737 የወታደራዊ ተቋማት ይጠቅሳሉ፡፡ ስለሆነም ዘገባው የአሜሪካ የበላይነት የመቀነሱን ጉዳይ አንስቶ የተናገረውን አይቀበሉም፡፡
እኤአ በ2030 የሚክሽፉት 15ቱ መንግሥታት (ፎቶ: ጂአይ)
ዘገባው የዓለማችንን የወደፊት ሁኔታ ሲተነብይ በዋንኛነት ከጠቀሳቸው ጉዳዮች አንዱ በ2030 የሚከሽፉ መንግሥታትን ዝርዝር ሰጥቷል፡፡ “በግጭት መብዛትና በአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ምክንያት” የሚከሽፉ መንግሥታት ተብለው ከተጠቀሱት 15 አገራት መካከል ኢትዮጵያ እንዷ ስትሆን አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቻድ፣ ኒጀር፣ ማሊ፣ ኬኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ ማላዊ፣ ሃይቲና የመን የተቀሩት ናቸው፡፡
ይሁንና ይኸው ም/ቤት እኤአ በ2015 ፓኪስታን የምትከሽፍ አገር ትሆናለች በማለት ትንቢት ሰጥቶ ይኸው እስካሁን አለች በማለት ዘገባውን የሚያጣጥሉ ክፍሎች ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎቹ አገራት ለመክሸፋቸው በቂ ማስረጃ የለም በማለት የዘገባውን ጥቆማ ይቃረናሉ፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ ያለው የመክሸፍ ሁኔታ ሊዋጥለት የማይችለው ኢህአዴግ “ህዳሴ፣ ውዳሴ” ከማለት ይልቅ ይህንን ጉዳይ አጥብቆ ሊያስብበት እንደሚገባና የሥርዓት መበስበስ አመላካች የሆነውን “የመንግሥት ሌቦች” መበራከት መፍትሔ ሊያበጅለት እንደሚገባ ደጋፊዎቹና አመራሩ በየጊዜው የሚያነሱት ነጥብ ነው፡፡
በዚሁ የኢትዮጵያ እንደ አገር የመክሸፍ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው አሁን ካላቸው ተግባር አኳያ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአውሮጳ የሚገኙ የፖለቲካና ዓለምአቀፋዊ ግንኙነት ተመራማሪ “ችግሩ የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚውም ነው” ይላሉ፡፡ “በአገር ውስጥ ያለው ተቃዋሚ ከውስጥ የሥልጣን ሽኩቻና ከስብሰባ/ውይይት ጋጋታ ባለፈ መልኩ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ሊያደርግ የሚችል የተቀናጀና ውጤታማ ተግባር ሊፈጽሙ ይገባቸዋል” የሚሉት ምሁር በውጭ ያለውም “ከጊዜያዊና ጥቃቅን የራስ ክብር የመፈለግ አካሄድ በመላቀቅ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ጡንቻውን በወያኔ ላይ ማሳረፍ ይጠበቅበታል” ብለዋል፡፡ “የደኅንነት ተቋሙ ባወጣው ዘገባ ላይ በግልጽ እንደተነበየው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ የመጨመሩ ያህል በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ይህንኑ ለውጥ ማምጣት የሚችል የዘመኑ ቴክኖሎጂ ለአሉባልታና ተራ የፖለቲካ ወሬ ከመጠቀም ይልቅ አገር ለማዳን ተግባር ሊጠቀምበት ይገባል” በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡
የደኅንነት ምክርቤቱ ያወጣው ሙሉ ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡
http://www.goolgule.com/coup-forecasts-for-2014/